tgoop.com/Islam_and_Science/5739
Last Update:
📖 #የመራም_ማስታወሻ
ክፍል ~ ➍
✍ ፀሀፊ ☞አሚር ሰይድ
እኔና ታናሽ እህቴ እንደዚህ እንድንሆን ተከባብረን እንድናድግ ያደረገን ግን አንድ ሚስጥር አለ.... ልጆች አድገው ነገ ለሚኖራቸው ማንነት ቤተሰብ ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳል፡፡ ኡሚ ይሄን ጠንቅቃ ስላወቀች ለነገ መልካም ሰውነት ዛሬ ላይ እኛን በመልካም ለመገንባት ደክማለች፡፡ ኡሚ እርስበርሳችን እንድንዋደድ እንዳንጣላ ሁሌም ትነግረናለች፡፡ እኔ የሪም ታላቅ ብሆንም እውቀት በእድሜ እንደማይለካ እኔ ተሳስቼ ሪም ልክ ልትሆን እንደምትችል ..እዉነት መሆኑን ካመንሽበት ደግሞ ከእሷ ትልቅ መሆንሽን አይተሽ ሳይሆን ለእዉነት ቅድሚያ መስጠት አለብሽ ብላ ትነግረናለች፡፡
ሪምንም ታላቅሽን አክብሪያት የምትልሽን ስሚያት የማያግባባችሁ ነገር ላይ ተወወያዩ ብላ ትመክረናለች ይሄ ልባችን ላይ እንደ ማህተም ያረፈ ምክሯ ነው እህቴ ጋር በመተዛዘን እንድንኖር ያደረገን ፡፡ በተግባር ደግሞ ተአምር ቢፈጠር ተለያይተን አንበላም፡፡ በተለይ ደግሞ ህፃናት የሚወዳቸው ጣፍጭ ምግቦችን ለሪም አስቀምጨላት ልብላ ብላት እንኩዋን እናቴ በጭራሽ አትፈቅድልኝም፤ ምክንያቱም ራስወዳድነት ወይም ስስት መነሻው ይሄ ነው ትላለች፡፡ እኔ የራሴን ቀድሜ ከጨረስኩ ሪም ስትበላ ልቀና ወይም ደግሞ ሰርቄም ልበላባት ስለምችል ሁሌም አንድ ላይ ነው የምትሰጠን፡፡ እኛም በዛው ለምዶብናል ሰው ቤት ቢሆን እንኩዋን እህቴን ብለን ይዘን እንሄዳለን ተካፍለን እንበላለን እንጂ ብቻችንን በጭራሽ አንበላም፡፡
ኡሚ ለብቻ መብላት ፍቅር እንዳይኖረን አድርጎ ስግብግብና ራስወዳድ ያደርጋል ...ብቻውን መብላት የለመደ ሰው ሰው ጋር ሲቀርብ የሚሻሙት የሱ የሆነን የቀነሱበት ይመስለዋል ትላለች፡፡ እንደዚህ ሆነን በማደጋችን በጣም ነው የምንዋደደው ሪም ለኔ ሁሉ ነገሬ ናት ሁሌም አብረን ነን አንለያይም ስታለቅስ አብሪያት አለቅሳለሁ ስትደሰት ደግሞ ከእሷ በላይ እኔ እደሰታለሁ፡፡ እሷም ያለኔ አይሆንላትም የትም ሁና መራምስ ትላለች፡፡ ኡሚ ቁርአን ቤት ከመሄዳችን በፊት እዛው ቤታችን ቁርአንን ለመሀፈዝ እንድረዳን አሊፍ ባ ታ.. ለይተን እንድንሀፍዝ አድርጋ ሀርፎቹንም አሳውቃናለች፡፡
የሰዉ ባህሪ በአስተዳደጉ ይወሰናል ይባል የለ ባህሪ ፀባያችንም ለጎረቤት ለሰፈር ምስጉን የምንባል ልጆች ነን
አባቢ ልጆቹን ናፍቂ ሚስቱን አፍቃሪ እና ቤቱን አክባሪ ነው፡፡ ከስራ ሰአት ውጭ ያለውን ጊዜውን ከልጆቹና ሚስቱጋር ያሳልፍል፡፡ እኛን ለማጫወት ሲል ፈረስ፣በሬ እየሆነ ያጫውተናል በግራና ቀኝ ትከሻው ላይ እንደ ጦጣ ተንጠላጥለን አቅፎ ያጫውተናል፡፡ ቤታችን ውስጥ ፍፁም ሰላምና ፍቅር የሰፈነበት የሚያስቀና ቤተሰባዊ ትስስር አለን፡፡ እኔና ሪም ከእህትነትም በተጨማሪ ጓደኛሞች ነን፡፡ ሪምን በሁለት ክፍል እበልጣታለሁ፡፡ እኔ 4ተኛ ክፍል ስሆን ሪም 2ተኛ ክፍል ነች፡፡ የቤት ስራ የማሰራት የማስጠናት እኔ ነኝ፡፡ እኔን ደግሞ ኡሚ ታስረዳኛለች፡፡
የእናቴ ማህፀን ሁለት የምትወዳዱ እህታማቾች እስኪ አንድ ወንድም እነሆ ብሎ ጀሊሉ ወስኖ ....አልሀምዱሊላህ እኔና ሪም ወንድም ተወለደልን! ኡሚ የጠፋውን ወንድሟን በማስታወስ ፈይሰል ብላ ስም አወጣችለት፡፡
ፈይሲ በመልክ አባቢ ጋር ይመሳሰላሉ፡፡ አባቢን የሚያውቁ ሰወች ፈይሲን ባዩ ጊዜ "ትንሹ ዩሱፍ" ብለው ይጠሩታል፡፡ አባቢ ከመቸውም ጊዜ በላይ ደስታው እጥፍ ድርብ ሁኗል፡፡ ፈይሲ ሲወለድ የእርዚቅ መክፈቻ ቁልፍ ይዞ የተወለደ ይመስላል፡፡ሂወታችን በበለጠ ተሻሻለ፡፡ አባቢ አውራ ጎዳናን ለቆ ጥቁር አባይ የከባድ መኪና ሹፌር ሆነ እሰከ ጅብቲ ድረስ ስለሚሄድ አበሉ ከደመወዙ በላይ ነው፡፡ ገቢያችን ከመሻሻሉ በተጨማሪ ደግሞ ከምንኖርበት የመንግስት ቤት ተላቀን የግል ቤታችንን ለመገንባት በማህበር የተደራጅት ቦታ ተሰጠን፡፡ በዚህ ጊዜ ፈይሰል የ2 አመት ልጅ ነበር፡፡አባቢ ልጆቹን ከኪራይ ቤት አውጥቶ በራሱ ቤት አንቀባሮ ለማሳደግ ከወትሮው በበለጠ ጠንክሮ ይሰራል፡፡ የቤቱን ግንባታ ተጀመረ፡፡ ፈይሲ ብዙ ለውጥን ይዞ መጣ፡፡ እማ በፈይሰል ውስጥ ሶስት ማንነትን ማየት ችላለች፤ ወንድሟን፣ ባሏን እና ልጇን ታይበታለች፡፡
አባቢ ለስራ ከሄደበት እስኪመለስ ድረስ በጣም ይናፍቀናል፡፡ እማ ልጆቹንና ቤቱን በመንከባከብ ትቆያለች፡፡ አባቢ ይመጣል ከተባለ ሙሉ ቀን ቤት ውለን ስንጠባበቀው ብንውል ደስተኛ ነን፡፡ አባቢ ወደ ቤት ሲመለስ ስጦታ ይዞልን የመምጣት ልምድ አለው፡፡ አባቢ ለቤተሰቡ ቅድሚያ ይሰጣል፡፡ ለልጆቹ ፍቅር ሰቶ ለሚስቱ ምቾትን መፍጠር ይችልበታል፡፡ ለቤተሰቦቹ ሲል ይሞታል፡፡ ሀላፊነቱን አይዘነጋም፡፡
ፈይሲ ሶስት አመት ሞላው እኔም 7ተኛ ክፍል ሪም ደግሞ 5ኛ ክፍል ደረስን፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር ሁኔታወች መዘበራረቅ ጀመሩ ...ዱንያ አንድ ቀን ወይ አንድ አመት ወይ አንድ ወር ወይም የተወሰኑ አመታት ደስታን ትለግስና ጀሊሉ እንዳለዉ ዱንያ የትንኝ ክንፍ ያህል ለኔ ቦታ የለትም ብሎ እንደነገረን የቀናት የወራት ወይም የአመታት ...ልፈትንም ካለ እስከ እለተ ሞት ድረስ የሀዘን ድር መጣል ይችላል ..
የሚያምር ሰዉ የሚቀናበት የኔንም ትዳር እንደነመራም ቤተሰቦች አድርግልኝ ተብሎ ዱአ የሚያደርጉበት ጎጆ የዱንያ ፈተና እየተከታለ እየመጣ የእናት እና አባቴን ኢማን መፈታተን ኢማናቸዉን ከልባቸዉ ላይ መቦጨቅ ጀመረ...የሀዘን እና የዱንያ ፈተናዎች ሊጀምሩ ተንደርድረዉ ሊመጡ እያሽኮበኮቡ ነዉ...
በእናትና አባቴ በጣም የሚቀናበት ትዳር ከከፍታ ቦታ ላይ እንደ ወደቀ ጠርሙስ መፈረካከስ የጀመረዉ.. ምን ይሆን ምክንያቱ??
#ክፍል ➎
ይቀጥላል......
www.tgoop.com/IslamisUniverstiy_public_group
www.tgoop.com/IslamisUniverstiy_public_group
BY ISLAMIC SCHOOL
Share with your friend now:
tgoop.com/Islam_and_Science/5739