tgoop.com/Islam_and_Science/5736
Last Update:
📖 #የመራም_ማስታወሻ
ክፍል ~ ➌
✍ ፀሀፊ ☞አሚር ሰይድ
እማ ስራ በጀመረች በሶስተኛ ወሯ ያላሰበችው ነገር ከፊት ለፊቷ ተጋረጠባት፡፡
እማ ከአያቷ ጋር ቁርስ በልታ ወደ ስራ ለመሄድ ስትዘጋጅ አያቷ አስሟ ተነሳባትና አፈናት፡፡ አስም እንዳለባት ብታውቅም ከደሴ ወደ ኮምቦልቻ ከመጡ በኃላ ግን አሟት አያውቅም ነበር፡፡ እማ በድንጋጤ ደርቃ ቀረች አይኗ እያየ ሞት መቶ አያቷንም ወሰደባት፡፡ ሰማይ እላይዋ ላይ የተደፍባት መሰላት፡፡ የእማ ድርብርብ ሀዘን በቅደም ተከተል እየመጣ ጠነከርኩ ስትል ጥንካሬዋን የሚፈታተን ሙሲባ እግር በእግር ይከተላት ይዟል፡፡
ሂወት እጅጉን ከበዳት... በብቸኝነት ለመኖር ተገደደች፤ ሰው እንዳትቀርብ የኔ የምትላቸውን ሰወች የሞት ጥላ በላይዋ እያንዣበበ የሚነጥቃት እሰኪመስላት ድረስ ሰው መቅረብ አስፈራት፡፡ እማ በብቸኝነቷ ታዋቂ ሆነች ..የአንጀቷን የምትነግረዉ የሀሳብ ማዕበሏን የሚገድብ የሴት ጓደኛ እንኳ ምንም የላትም ብቸኝነት ጌጤ ነዉ ብላ እራሷን ያሳመነችዉ ይመስለኛል.....ወደ ስራ ስትሄድም ሆነ ስትመጣ ብቻዋን ነዉ... ከስራ ባልደረቦቿ ጋርም ከሰላምታ በዘለለ የጠበቀ ግንኙነት አልነበራትም፡፡
ይሄን ብቸኝነቷን የታዘበው ዩሱፍ ሊቀርባት ወሰነ፡፡ ዩሱፍ እማ የመሰራበት መስሪያ ቤት በሹፍርና ሙያ ነው የተቀጠረው፡፡ የድርጅቱን ሰርቪስ መኪና ስለሚይዝ የሁሉንም ሰራተኛ መውረጃ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ዩሱፍ በባህሪው ሰው አክባሪ የተቸገረን መርዳት የሚወድ አይነት ሰው ነው፡፡ ከጥበቃ እስከ ስራ አስኪያጅ ድረስ ተወዳጅነትን ያተረፈ ምስጉን በጣም ጥሩ ሰው ነው፡፡ ሰወች ሁሉ በመልካም ያነሱታል ተጫዋችና ቀልደኛ ነው፡፡ ዩሱፍ ሁሌም እማን ይከታተላታል የምትወርድበትን ቦታ ስለማያውቅ ሰፈሯንም አወቀ በስራ ሰአት አልፎ አልፎ ቢሮ እየሄደ ያወራታል፡፡ የሻይ ሰአት ቢኖራቸውም እማ ያን ሰአት አትጠቀምበትም በአንድፊቱ ለምሳ ነው የምትወጣው፡፡ አሁን ግን የሱፍ በተለያየ ዘዴ እየፈጠረ ይዟት ይወጣል፡፡ ቅርርባቸው እየጠነከረ ሲመጣ እማ ያሳለፈችዉ ብቸኝነት ስለሆነ እማ የመጀመሪያ ያወቀችዉ ሰዉ ስለሆነ ለየሱፍ የልቧን አንድ ክፍል ለእሱ የሰጠችዉ ይመስል የሱፍን ሳታወራ ስቀር ይናፍቃት ጀመር...የሱፍም እነደዚሁ እማን ካላወራት ትናፍቀዉ ጀመረ.... ሁለቱም የመሀባዉ ስፍራ ተገጣጠመና ይነፋፈቁ ጀመር፡፡
ዩሱፍ ቀድሞ እማን የቀረባት ለትዳር አስቧት መሆኑን አይክድም፤ ኡሚ ስትቀርበው ለመልካምነቱ እጅ ሰጠች እሷም አፈቀረችው፡፡ እናም ይሄን ግንኙነት ወደሌላ ሳይሄድ ከትዳር በፊት ከአላህ ድንበር ዉጭ ሳያልፉ ፈጣሪ የከለከለዉን ተከልክለዉ በመቀራረብ ብዛት መሳሳት መኖሩን ሳላወቁ ይሄን ያማረ ፍቅር ወደ ትዳር ቀይረው በፍቅር ደስተኛ ሁነው አንድ ጎጆ ቀልሰዉ አብረዉ መኖር ጀመሩ፡፡
ዩሱፍ ማን ነዉ? ብላችሁ እያሰባችሁ መሰለኝ...ዩሱፍ ማለት የኔ አባቴ ነው፡፡ አባቢ ብየ እጠራዋለሁ በጣም መልከመልካም ጥሩ የሚያስብ በሰፈር በስራ ቦታ በጥሩነቱ የተመሰከረለት ነዉ አባቢ ..... ተጋብተው መኖር ከጀመሩ 6 ወራትን እንዳስቆጠሩ እኔ ተፀነስኩ፡፡
እማ ዘመድ ስለሌላት ብዙ ልጅ ወልዳ ዘር እንዲበዛላት ትፈልጋለች የሁሌም ዱአዋ አላህዋ ዘር የለኝም ዘሬን አብዛልኝ ነዉ ፡፡ አባቢ ኡሚ በማርገዟ ምክንያት ደስታዎ ወደር አልነበረውም መሬት አይንካሽ ማለት ነው የቀረው በጣም ይንከባከባታል፡፡ ኡሚም ትቀብጥበታለች የአባቢና የኡሚ ፍቅራቸው ጎረቤትን ያስቀናል፡፡ እማ ምንም የኔ የምትለው ዘመድ አልነበራትም እኔን ስትወልድ ማን እንደሚያርሳት ስታስብ ይጨንቃት ነበር፡፡
አሁን ግን ጎረቤቶቿ ጋር ስለተቀራረበች እና ማህበራዊ ኑሮ የሚችሉ ስለሆነ አይዞሽ አለንልሽ በየተራ እናርስሻለን ብለው አበሸሯት፡፡ እናትና አባቴ የሚኖሩት የመንግስት ቤት ተከራይተው ነው፡፡ ሁለት ክፍል ቤት ሰርቪስ እና የጋራ ውሀ እና የጋራ መፀዳጃ ያለው የመንግስት ቤት ነዉ ፡፡
መቼም እርግዝና ላይ ሴቶች የሚያምራቸዉ ነገር አለ...እናም አንድ ቀን እማ የበቆሎ ቂጣ አማረኝ አለችና ጎረቤቷ አሚናየ የሚባሉ አሮጊት አሉ መሀን ናቸው የቀን ስራ እየሰሩ ሂወትን ይገፋሉ፡፡ ለአላህ ብሎ የነየተ ሸህ ይማም በነፃ ሰርቪስ ውስጥ እዲኖሩ ፈቅዶላቸው ነው የሚኖሩት፡፡ ኡሚ በሆዷ ያሰበችዉ የበቆሎ ዱቄት ማግኘትን እንጂ በሆዷ መጥፎ ነገር አስባ አይደለም እናም አሚናየ ቤት ሂዳ
......የጤፍ ዱቄት በበቆሎ ቀይሩኝ ስትላቸው በጣም ተቆጡ በድህነታቸው እየቀለደችባቸው መሰላቸውና" ከመቸ ጀምሮ ነው ዩሱፍ በቆሎ የሚበላው?? ምነው የኔ በቆሎ መብላት ላንች ደነቀሽ??" አሏት፡፡ እንደዚህ ሲቆጡ ስታይ ኡሚ ደነገጠችና" እሽ ይቅርታ" ብላ ወደ ቤቷ ተመለሰች፡፡ እሳቸው ግን ተናደው ስለነበር " እንዴት በድህነቴ ትቀልዳለች??" ብለው ለጎረቤት ሲነግሩ " አረ እርጉዝ ናት አምሯት ይሆናል" ብለው ነገሯቸው፡፡
እሳቸውም ምጣድ ሙሉ ቂጣ ጋግረው " ልጄ ይቅር በይኝ ሳላውቅ አስደነገጥኩሽ" ብለው ቂጣውን ሰጧት፡፡ ከሰጧት ቡሀላ እማማ አሚናት አዉፍ በይኝ ሲሏት
...አረ እማማ እኔ ቂም አልያዝኩም አለቻቸዉ፡፡ ከዛ ጊዜ በኃላ ግንኙነታቸው የእናትና ልጅ ሆነ "የሚያምርሽን ንገሪኝ እንዳትደብቂኝ እቀየምሻለሁ" ይሏታል፡፡ እማም እንደ እናቷ ነበር የምታያቸው የሚያምራትን ደስ ያላትን ምንም ሳትፈራ እንደ እናት ትጠይቃቸዋለች
....አሚናየም እሺ እያሉ በደስታ እያረጉላት እንደ ልጅ ይንከባከቧታል
መቼም ጊዜዉ ደረሰና አልሀምዱሊላህ ወደዚህ ምድር ተቀላቀልኩ....እኔ ስወለድ ኡሚ "ኒእማ" ብላ ስም አወጣችልኝ፡፡ አባቢ ደግሞ ትርጉሙ ምን እንደሆነ ባላውቅም "መራም" ብሎ ስም አወጣልኝ፡፡ እናም ስሜ "መራም" ሆኖ ፀደቀ፡፡
እኔ ከተወለድኩ በኃላ እኔን የሚንከባከበኝ ስላልነበረ እማ ስራዋን ለማቆም ተገደደች፡፡ ለኔ ስትል ስራዋን ትታ ከስራዋ ሁሉ በላጭ እኔን አድርጋ መረጠች፡፡ አባቢ እኔን ተንከባክባ ለማሳደግ ስትል ስራ በማቆሟ በጣም ተደሰተ፡፡ ቤት ሲገባ ሚስቱና ልጁ ቤቱን በፍቅር አሙቀው ይጠብቁታል፡፡ አባቢ ከስራ ወደ ቤቱ እስኪመለስ በጣም እንናፍቀዋለን፡፡ ከስራ እንደወጣ ቀጥታ ወደ ቤት መጥቶ ያጫውተናል ሽር ሽር ይወስደናል፡፡ ቤታችን በፍቅር የተሞላና ደስተኛ ቤተሰቦች ሆነን መኖር ጀመርን፡፡
እማ ስራ ትታ ቤት መዋል ስለጀመረች በአንድ ልጅ መድከሜ ካልቀረ ብላ ሁለተኛ አረገዘች፡፡ እኔም አመት ሞልቶኝ ቁሜ ለመሄድ በአቅሜ መፍጨርጨር ጀምሬያለሁ፡፡ ለማዳ በመሆኔ የያዘ ቢይዘኝ ያቀፈ ቢያቅፈኝ ለቅሶ አላውቅም፡፡ በዚህ ባህሪየ ሁሉም ጎረቤቶቻችን ይወዱኛል፡፡ እንዳገኘ አንጠልጥለውኝ ይዞራሉ፡፡ከዛ ሁሉ ሰው ግን አሚናየን በጣም እወዳቸዋለሁ፡፡ ገና በልጅ አንደበቴ እየተኮላተፍኩ አሚናየ ብለው ሲጠሩዋቸው እኔም " እማማዬ" ብየ ጠራኃቸው ከዛ ጊዜ ጀምሮ ሁሉም ሰው እማማዬ ብሎ መጥራት ጀመረ፡፡ እሳቸውም በጣም ነው የሚወዱኝ ከሳቸው ቤት ምግብ ውጭ ሌላ አልበላም ብየ ሳስቸግራት ኡሚ በሳቸው ምግብ እየሰራች በሳቸው ሰሀን አድርጋ እማማየ ቤት ታስቀምጥልኝ ነበር፡፡
እኔም የእማማዬ ምግብ እየመሰለኝ ግጥም አድርጌ እበላለሁ፡፡እማማዬ ወደ ቤታቸው እስኪመጡ ድረስ በርበር እያየሁ እጠብቃለሁ፡፡ ከመጡ በኃላ ግን ኡሚን ትቻት እሳቸው ጋር ልጫወት እሄዳለሁ፡፡ኡሚ" ደክሟቸዋል ነይ ከኔ ጋር ተጫወች" ብትለኝም አልሰማትም፡፡ እማማዬም ሲመጡ እኔን ካላዩ ቤታቸው ሳይገቡ ወደኛ ቤት መተው ደህንነቴን ያረጋግጣሉ፡፡👇👇
BY ISLAMIC SCHOOL
Share with your friend now:
tgoop.com/Islam_and_Science/5736