tgoop.com/IbnuMunewor/7919
Last Update:
ግዕዝ ለምን?
~
ግዕዝን የማስተማር አስፈላጊነቱ ምንድነው? በተደጋጋሚ የሚነሱ ማሳመኛ ነጥቦችን እንመልከት (ከአንድ ፖስት ላይ የወሰድኳቸው ናቸው)።
1/ "አብዝሃኞቹ በብራና ላይ የተፃፉ የኢትዮጲያ ሃገር በቀል የሆኑ እውቀቶች የተሰናዱባቸው ድርሳናት የተፃፉት በግእዝ ቋንቋ ነው።"
መልስ፦
ሀ - ሃገር በቀል የሆኑ እውቀቶች ምንድን ናቸው? በግዕዝ ድርሳናት ውስጥ ብቻ የሚገኙ ህዝብ የማያውቃቸው ሃገር በቀል እውቀቶች አሉ? እና እስከዛሬ ለምን ዝም አላችሁ? እውነቱን ለመናገር በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህፃናትን ለማዘጋጀት የሚጠይቁ ያልተጠኑ የግዕዝ ድርሳናት የሉም።
ለ - የምትሉት እውነት ከሆነ ይህንን የመመራመር እና ህያው ወደሆነ ቋንቋ የመተርጎሙ ኃላፊነት የምሁራን እንጂ የህፃናት አይደለም። በከፍተኛ ተቋማት የሚሰራ እንጂ ለአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች የሚሰጥ አይደለም። ስለዚህ እነዚህን ህፃናትን እንዲያስተምሩ ከየገዳማቱ ልታመጧቸው የምታስቧቸውን ቄሶችና ዲያቆናት የጥናት አሰራር ስልጠና ስጧቸውና እዚያው ጨርሱ።
2/ "alternative medicines የሚባሉት የኢትዮጲያ ባህላዊ ህክምና የተመሠጠረባቸው የብራና ሰነዶችና ድርሳናት የተፃፉት በግእዝ ነው።"
መልስ፦
ሀ - ይህም ውሸት ነው። ግዕዙ ላይ ዋጋ ያለው የህክምና እውቀት ቢኖር መሪጌታዎች በድግምትና መተት ማስታወቂያ ባላጥለቀለቁን ነበር።
ለ - እውነት ነው ቢባል እንኳ ይህንን የማጥናት ኃላፊነቱ የህፃናት ሳይሆን የጤና ጥበቃ ሚንስቴር ነው።
3/ "በብራና ላይ ተፅፈው የተቀመጡ ሃገር በቀል የስነ ህዋና የስነ ፈለክ ወርጅናሌ ሃሳቦች የተፃፉት በግእዝ ነው።"
መልስ፦
ኧረ እየታፈረ! በዚህ ዘመን እንዲህ ዓይነት ህፃናት የሚያሳምን ውሸት መዋሸት ለምን? ሳይንሳዊ ውጤቶች ካሉ ለምን እስከዛሬ ደበቃችኋቸው? እውነትስ ቢሆን ይህንን የማጥናት ኃላፊነቱ የህፃናት ሳይሆን የኢትዮጵያ የህዋ ሳይንስ ማዕከልኮ ነው።
4/ በእንግሊዝና በአሜሪካ ሙዚየሞች ውስጥ ከኢትዮጲያ ተዘርፈው የተወሰዱ ( በተለይ ከመቅደላ የተዘረፉት) ለቁጥር የሚታክቱ የብራና ላይ መፅሃፍት የተፃፉት በግእዝ ነው ፤
መልስ፦
ለቁጥር የሚታክቱ? ይህም ውሸት ነው። ቢኖር እንኳ ከገድላትና ዜና መዋዕል አይዘልም። ጥቂት ከተገኘ አንድ ተቋም ጥናቱን ለጨርሰው ይችላል።
5/ "ለዘመናዊ ቴክኖሎጂ መነሻ የሆኑ አንዳንድ እሳቤዎች ከኢትዮጲያ የግእዙ የስነ ቁጥር (mathematics) ፅንሰ ሃሳብ እንደተወሰዱ ይነገራል። "
በግዕዝ የተደበቀ ህክምና፣ ህዋ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ የምትሉትን ቀልድ ተውት። የማይካደው ነገር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በሃገር ምስረታ ላይ፣ የፅህፈት ስራን በማዳበር ላይ (መነሻው ከኦርቶዶክስ በፊት ቢሆንም) ትልቅ አስተዋጽዖ አላት። ይህንን መካድ አይቻልም። ታሪክ ግን ታሪክ ነው። ሙገሳ ሙገሳውን እየመረጡ መውሰድ አይቻልም። በሃገሪቱ ታሪክ ላይ ጉልህ ሚና ያላት ተቋም አዎንታዊ ነጥቦችን ብቻ እየመረጡ ማስተጋባት ሐቀኛ የታሪክ አዘጋገብ አይደለም። ስለዚህ ለሃገሪቱ ኋላቀርነት፣ ህዝቦች ላይ ለደረሱ ጭቆናና ብዝበዛ፣ ለደረሱ ውድመቶችና ፍጅቶች ድርሻ እንዳላት ማመን ይገባል። ታሪክ ጣፈጠም መረረ እውነተኛ ክስተቶችን የምንዘግብበት እንጂ እንደ ብፌ ደስ ያሰኘንን እየመረጥን የምናነሳበት አይደለም።
እቅጩን ስንነጋገር ግዕዝን ማስተማር ምንም ዓይነት የህክምናም የቴክኖሎጂም የሌላ ዘመናዊ ስልጣኔ እድገትም ሆነ የተደበቀ እውቀት አያመጣም። የህዝብ ለህዝብ ትስስርም አይጨምርም። የሃገርን ሃብት ምንም እሴት በማይጨምር ነገር ከማባከን ዉጭ ለኢኮኖሚ እድገት ምንም አይነት አስተዋፅዖ የለውም። ሌላው ቀርቶ የረባ ሃይማኖታዊ ትርፍም አያመጣም። ይልቁንም ነፍጥ ያነሱ ተዋጊዎችን ልባቸውን ለማማለል ይውል ካልሆነ በስተቀር እንዲህ አይነት የጉልበት ፖሊሲ ጥላቻ ነው የሚያመጣው። ይልቁንም ላይሳካ ነገር እንዲህ አይነት የረባ ዋጋ የሌለው ቋንቋ ለመመለስ አጉል ከመዳከር የሃገር ውስጥ ቋንቋዎችን ወይም ለሚሰደዱ ዜጎቻችን የሚጠቅሙ የውጭ ቋንቋዎችን ማስተማር ነው የሚሻለው።
=
የቴሌግራም ቻናል፡-
https://www.tgoop.com/IbnuMunewor
https://www.tgoop.com/IbnuMunewor
BY Ibnu Munewor (ኢብኑ ሙነወር)


Share with your friend now:
tgoop.com/IbnuMunewor/7919