tgoop.com/IbnuMunewor/7776
Last Update:
ለወገን መቆርቆራችን የእውነት ነው ወይ?
~
አንድ የፉላኒ ብሄር ሰው ከኢግቦ ብሄር ሰው ጋር ቢጣላ ብዙ ፉላኒዎች ከፉላኒው፣ ኢግቦዎች ደግሞ ከኢግቦው ወግነው ይነሳሉ። አጥፊው ማነው የሚለውን ሳያጣሩ ማለት ነው። ይሄ ቋንቋና ብሄር እያየ ቆንጨራ የሚያነሳ መንጋ ግን ጎዳና ላይ የወደቀ ወገኑን ቤቱ ወስዶ አያስጠልልም። ለተራበ ወገኑ ቁራሽ አይጥልም። ዶላር እየላከ ታጣቂ የሚያስታጥቀው ዲያስፖራ አስተባብሮ ሰፈሩ ላይ ትምህርት ቤት፣ ጤና ተቋም አይገነባም።
የአብዛኞቻችን ለወገን መቆርቆር ትርጓሜ ጥቃት ሲደርስ ሌላውን ማውገዝ ላይ ያተኮረ ነው። በርግጥ ይሄ የመቆርቆር አንድ ገፅ ነው። ነገር ግን እውነት ለወገን የምንቆረቆር ከሆነ
- በፍርፋሪ እምነቱን የሚቀይረውን እንድረስለት።
- በሺርክና በቢድዐ የተወረረውን እንታደገው።
- በዘረኝነት የሚባላውን ከዚህ ገዳይ በሽታ እንዲድን እንስራ።
- ሁለ ነገሩን እያቃወሰ ካለው የጫት ሱስ እንዲወጣ እንታገል።
- ለዘመድ፣ ለጎረቤት ለችግራቸው እንድረስ።
- ነገ ጤናማ ትውልድ ይሆኑ ዘንድ ለልጆቻችን የተሻለ አስተዳደግ እንስጣቸው።
ሁላችንም ለለውጥ አስተዋፅዖ ማድረግ እንችላለን። ከራሳችን፣ ከቤታችን እንጀምር። እንደ ቤተሰብ ሰውኛ ባህሪ እንዲኖረን እንስራ። ማህበረሰብ የቤተሰብ ድምር ውጤት ነውና አቅልለን አንየው። "ሮም ባንድ ቀን አልተሰራችም።"
በተረፈ እርሱ ቦርጭ ተሸክሞ እየተጓዘ ለተቸገሩ ወገኖቹ መድሃኒት የማይገዛ፣ ሳይቸግረው ወላጅ ቤተሰቡን ዞሮ የማያይ፣ የወገኑ በሺርክ፣ በሱስ መወረር የማይቆረቁረው ሁላ የግለሰቦችን ግጭት ሁሉ ወደ ብሄር እየተረጎመ አቧራ ቢያስነሳ ከሰውነት ተራ መውጣቱን ነው የሚያሳየው። ለፍትህ ቦታ ሳይሰጡ ምድብ እያዩ መሰለፍማ በጫካው ዓለም ያለ የእንስሳት ህግ ነው። ይልቅ ከፍ ብለን እንገኝ። ሰው መሆን ነውንጂ ሰው መምሰልማ ማንን ያቅታል?!
=
የቴሌግራም ቻናል፡-
https://www.tgoop.com/IbnuMunewor
https://www.tgoop.com/IbnuMunewor
BY Ibnu Munewor (ኢብኑ ሙነወር)


Share with your friend now:
tgoop.com/IbnuMunewor/7776