tgoop.com/HISCULHEROFETHIOPIA/5728
Last Update:
ቅዱስ ጴጥሮስ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” የሚለውን የትንሣኤውን ጌታ ድምጽ ከሰማ ፣ የተጠራጠረው ቶማስ እጁን በጎኖቹ አግብቶ “ጌታዬ አምላኬ” ብሎ ሲያምን ከተመለከተ በኋላ “ዓሣ ላጠምድ እሄዳለሁ” ብሎ ሲናገር እናገኘዋለን።(ዮሐ 21፥3) ክርስቶስ ተላልፎ በተሰጠበት በሐሙስ ምሽት ከእሳት ዳር ተቀምጦ ያደረገውን ሊረሳውና ራሱን ይቅር ሊል ስላልቻለ፣ ጌታው ቀድሞ የሰጠውን የወንጌል መረብ ተወና የዓሣውን መረብ ጨብጦ ወደ ገሊላ ባሕር ሮጠ።(ማቴ 4፥19) በኃጢአት ምክንያት የተሰማው ኃፍረትና መሸማቀቅ ሐዋርያነቱን ትቶ በድሮ ማንነቱ ውስጥ ራሱን እንዲደብቅ አደረገው። የካደን ማን ለምስክርነት ይፈልገዋል በሚል ዓይነት ስሜት ለወንድሞቹ “ዓሣ ላጠምድ እሄዳለሁ” አላቸው።
ደስ የሚለው ነገር ግን ይህን አስቀድሞ የሚያውቅ ይቅር ባይ አምላኩ ጴጥሮስን “በገሊላ ቀድሞት ነበር”። በበደሉ ተሸማቆ የተወውን ሐዋርያነት ሥልጣን በፍቅሩ መማለጃነት መልሶ ሊሰጠው፣ አይገባኝም ብሎ ያስቀመጠውን የወንጌል መረብ ዳግመኛ ሊያሲዘው በገሊላ ባሕር ዳር ቀደመው። እኛም አንድ ኃጢአት ይኖረናል። መርሳት ያልቻልነው፣ ንስሐ እንኳን ብንገባበት ራሳችንን ይቅር ለማለት የተቸገርንበት፣ “ከዚህ በኋላማ...” እያሰኘ የድሮ መረብ አስይዞ ወደ ገሊላ የሚመልስ አንድ በደል ይኖረናል። ነገር ግን ጌታ ለቅዱስ ጴጥሮስ እንዳደረገው ለእኛም እንዲሁ ያደርጋል። ከባሕሩ ዳር ይጠብቀናል፣ “ትወደኛለህ” ብሎ ይጠይቀናል፣ ከዚያ በማይለወጥ ፍቅሩ ወልውሎ ሰንግሎ አፍረን ወደ ሸሸነው መንፈሳዊነት ይመልሰናል።
ጌታችን በገሊላ ይቀድመናል!
BY ኢትዮጵያ
Share with your friend now:
tgoop.com/HISCULHEROFETHIOPIA/5728