tgoop.com/Enatachn_mareyam/18331
Last Update:
🕊
[ † እንኩዋን ለቅዱሳን ነገሥታት "ማርቆስ እና ቴዎድሮስ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ † ]
ማንኛውም ሰው
¤ ቢጾም ቢጸልይ
¤ መልካም ቢሠራ
¤ ለእግዚአብሔር ቢገዛ
¤ አልፎም ቢመንን ይደነቃል:: ይሕንን ሥራ ንጉሥ ሆነው ስለ ሠሩትስ ምን እንላለን? ማድነቅ የሚለው ቃል የሚገልጸው አይመስለኝም::
¤ ወርቅና ብር በእግር እየተረገጠ
¤ የሚበላውና የሚጠጣው ተትረፍርፎ ሳለ
¤ አገር ምድሩ እየሰገደላቸው
¤ ሁሉ በእጃቸው
¤ ሁሉም በደጃቸው ሳለ...
ይህንን ሁሉ ስለ ክርስቶስ ፍቅር የተውትን ጻድቃን ነገሥታት የክብር ክብር ይገባቸዋል:: ከእነዚህ መካከል ዛሬ የሚከበሩትን ፪ [2] ቱን እናዘክር::
🕊 † ቅዱስ ማርቆስ ንጉሠ ሮም † 🕊
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይህንን ቅዱስ ጻድቅ: የዋህ: ንጹሕና ገዳማዊ ብላ ትጠራዋለች:: ሮም እንደ ዛሬ ጠባብ ከተማ ሳትሆን ዓለምን በክንዷ ሥር ቀጥቅጣ የምትገዛ ኃያል ሃገር ነበረች:: ቅዱስ ማርቆስ የልዑላኑ ቤተሰብ ነውና በሮም ተወልዶ በእመቤታችን ቤተ መቅደስ ውስጥ አድጉዋል::
የየዕለት ሙያው ጾምና ጸሎት: መጻሕፍትንም መመልከት ነበር:: ነባሩ ንጉሥ ሲሞት መሣፍንቱ ቅዱስ ማርቆስን በድንግልናው ገና ወጣት ሳለ በዚያች ታላቅ ሃገር ላይ አነገሡት:: ንጉሥ ቢሆንም ሙሉውን ሌሊት በእመቤታችን ፊት ሲጸልይና ሲያለቅስ ያነጋ ነበር::
ስለ ፍቅርም ድንግል ማርያም ተገልጻ "ምን ላደርግልህ ትወዳለህ?" አለችው:: ቅዱስ ማርቆስም "ለሕዝቡ ፍቅር አንድነትን ሰላምን ስጪልኝ:: እኔ በማስተዳድርበት ቦታ ሁሉ ጠብ ክርክር ይጥፋልኝ:: ፍቅር ይንገስልኝ" ሲል መለሰላት:: ድንግል እመቤታችንም "እንደ ቃልህ ይሁን" ብላ አጋንንት ወደ ሃገሩ እንዳይገቡ ከለከለችለት:: በዚህም ቅዱስ ማርቆስ ከነገሠ ጀምሮ ለ5 ዓመታት ጠብ ክርክር: ክፋትና ችግር አልነበረም:: ሁሉም ተፋቅሮን ያጸና ነበር እንጂ::
ከ ፭ [5] ዓመታት በሁዋላ ግን ሕዝቡና ሹማምንቱ ተሠብስበው አንድ ነገርን መከሩ:: ቅዱስ ማርቆስን አጋብተው ለብዙ ጊዜ እንዲመራቸው ማለት ነው:: ምክንያቱም አኗኗሩ እንደ መነኮሳት ነውና ጠፍቶ እንዳይሔድ በመስጋታቸው ነው:: ከዚያም የሕዝቡ አለቆች ተመርጠው ሃሳባቸውን አቀረቡለት:: እርሱ ግን ጭንቅ ሆነበት:: ጭራሹኑ እንዲህ ዓይነት ሃሳብ መጥቶበት አያውቅም::
"እስኪ በጸሎት ላስብበት" ብሎ መለሳቸው:: እነርሱ ግን ወደውታልና ድጋሚ ተሰብስበው ሌላ ነገርን መከሩ:: እርሱ ሳያውቅ መልካም ሴት መርጠው: ሥርዓተ ተክሊል አዘጋጅተው: ድግሱንም አዘጋጅተው በግድም ቢሆን ሊያጋቡት ቆረጡ:: ቅዱስ ማርቆስ የተደረገውን ሁሉ ፈጣሪ ገልጦለት በጣም ደነገጠ::
ፈጥኖ ወደ እመ ብርሃን ስዕል ቀርቦ አለቀሰ:: "እመቤቴ! እኔ ካንቺ ጋር እንጂ ከዚህ ዓለም ጋር መኖር አልችልም" አላት:: እመ ብርሃን ከሰማይ ወደ እርሱ ወርዳ "የምነግርህን ስማኝ:: በሌሊት ተነስተህ ወደ ማሳይህ በርሃ ሒድ" ብላው ተሠወረች:: ቅዱስ ማርቆስ ደስ እያለው የንግሥና ልብሱን ጥሎ: ቆሻሻ ጨርቅ ለብሶ በሌሊት ከቤተ መንግስቱ ወጣ::
ወደ ሁዋላ አልተመለከተም:: እመቤታችን እየመራችው ደብረ ቶርማቅ የሚባል በርሃ ውስጥ ባሕር ተከፍሎለት ገባ:: ሕዝቡ መልካም እረኛ መሪን አጥቷልና በሮም ከተማ ታላቅ ለቅሶና ሐዘን ተደረገ:: ቅዱስ ማርቆስ ግን በደብረ ቶርማቅ በጾም: በጸሎትና በተጋድሎ ማንንም ሳያይ ለ፷ [60] ዓመታት ኖረ::
በዚህች ቀንም ዐርፎ ወደ ወደደው ክርስቶስ ሒዷል:: ሥጋውን የሚቀብር አልነበረምና ከሰማይ ፲፪ [12] ቱ ሊቃነ መላእክትና ፲፪ [12] ቱ ሐዋርያት ወረዱ:: በዝማሬ ሲገንዙትም በድኑ ከመሬት ፭ [5] ክንድ ከፍ ብሎ ተንሳፈፈ:: መላእክቱና ሐዋርያቱም በማሕሌት እዚያው ደብረ ቶርማቅ ውስጥ ቀብረውታል::
🕊 † ቅዱስ ቴዎድሮስ ንጉሠ ኢትዮዽያ † 🕊
በሃገራችን ታሪክ በጣም ተወዳጅ ከነበሩ ነገሥታት ጻድቁ ቴዎድሮስ ቅድሚያውን ይወስዳል:: በርግጥ በርካቶቻችን የምናውቀው ስለ ሃገሩ ፍቅር ራሱን የሰዋውን ዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስን ፲፰፻፵፭-፲፰፷ [1845-1860] ነው:: በበጎ ሥራውና በቅድስና ሕይወቱ የተመሠከረለት ግን ዛሬ የምናስበው ቀዳማዊው ነው::
ቀዳማዊ ዐፄ ቴዎድሮስ የደጉ ዐፄ-ዳዊት [ግማደ-መስቀሉን ያመጡት] እና የተባረከችው ሚስታቸው ፅዮን ሞገሳ ልጅና የጻድቁ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ታላቅ ወንድም ነው::
በኢትዮዽያ ለ፫ [3] ዓመታት ከ፲፫፻፺፮-፲፫፻፺፱ [ከ1396-1399] ብቻ ነግሦ እያለ እንደ ንጉሥ ሳይሆን
¤ ከጠዋት እስከ ማታ ድሃ እንዳይበደል: ፍርድ እንዳይጉዋደል ይታትር የነበር:
¤ ጾምና ጸሎትን የሚያዘወትር:
¤ ወገቡን ታጥቆ ነዳያንን የሚያበላ:
¤ ለአብያተ ክርስቲያናትም የሚጨነቅ ደግ ሰው ነበር::
ስለዚህም በሕዝቡ እጅግ ተወዳጅ ነበር:: በነገሠ በ፫ [3] ዓመቱ ዐርፎ በዝማሬና በለቅሦ ሥጋውን ተሸክመው ሲሔዱ ወንዝ ተከፍሎላቸዋል:: ከመቃብሩም ላይ ጸበል ፈልቁዋል::
ቸር አምላክ መልካም መሪ ለሃገራችን: በጐ እረኛንም ለነፍሳችን ያድለን:: ከቅዱሳን ነገሥታቱም ጸጋ በረከትን ይክፈለን::
[ † ሰኔ ፳፱ [ 29 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]
፩. ቅዱስ ማርቆስ ንጉሠ ሮም [ጻድቅ: ንጹሕና ገዳማዊ]
፪. ቅዱስ ቴዎድሮስ ጻድቅ [ንጉሠ ኢትዮዽያ]
፫. ቅዱስ ዓምደ ሚካኤል ኢትዮዽያዊ [ፍልሠቱ]
፬. ፯ቱ "7ቱ" ቅዱሳን መስተጋድላን [አባ አብሲዳ: አባ ኮቶሎስ: አባ አርድማ: አባ ኒኮላስ: አባ ሙሴ: አባ እሴይ: አባ ብሶይ]
፭. ቅዱሳን አባ ሖር: አባ ብሶይ: አባ ሖርሳና እናታቸው ቅድስት ይድራ [ሰማዕታት]
[ † ወርኀዊ በዓላት ]
፩. የፈጣሪያችንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት
፪. ቅድስት አርሴማ ድንግል
፫. ቅዱስ ዼጥሮስ ተፍጻሜተ ሰማዕት
፬. ቅዱስ ማርቆስ ዘቶርማቅ
፭. ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ኢትዮዽያዊት
፮. ቅዱስ ዘርዐ ክርስቶስ [ጻድቅና ሰማዕት]
" አቤቱ በኃይልህ ንጉሥ ደስ ይለዋል:: በማዳንህ እጅግ ሐሴትን ያደርጋል:: የልቡን ፈቃድ ሰጠኸው:: የከንፈሩንም ልመና አልከለከልኸውም:: በበጐ በረከት ደርሰህለታልና:: ከከበረ ዕንቁ የሆነ ዘውድን በራሱ ላይ አኖርህ:: ሕይወትን ለመነህ ሰጠኸውም:: ለረጅም ዘመን ለዘለዓለሙ:: በማዳንህ ክብሩ ታላቅ ነው:: [መዝ.፳፥፩-፭] (20:1-5)
† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †
[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]
† † †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖 🕊 💖
BY አብሰራ ገብርኤል ለማርያም
Share with your friend now:
tgoop.com/Enatachn_mareyam/18331