tgoop.com/Enatachn_mareyam/18172
Last Update:
🕊
† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ †
❖ እንኳን አደረሳችሁ ❖
❖ ሰኔ ፲፮ [ 16 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
🕊 † ቅዱስ አቡናፍር ገዳማዊ † 🕊
ጻድቁ ተወልዶ ያደገው በ፭ [5] ኛው መቶ ክ/ዘመን በምድረ ግብፅ ነው:: ወቅቱ ሥርዓተ መነኮሳት የሚጠበቅበት:አበው ባሕታውያን እንደ ሰማይ ከዋክብት በዝተው የደመቁበት ነበር:: ታላቁ አቡናፍርም ከክርስቲያን ወላጆቹ ተወልዶ: በሥርዓት አድጎ: መጻሕፍትንም ተምሮ ገና በወጣትነቱ መንኗል::
ሥርዓተ መነኮሳትን ከአባ ኤስድሮስ ታላቁ አጥንቶ ገዳሙንና መምሕሩን እየረዳ ለብዙ ዓመታት በጾምና በጸሎት ኑሯል:: መነኮሳቱ ስለ ትሕትናውና ስለ ታዛዥነቱ ፈጽመው ያከብሩት ነበር::
ከዕለታት በአንዱ ቀን አረጋውያን መነኮሳት ጭው ባለ በርሃ ስለሚኖሩ ባሕታውያን ሲጨዋወቱ: ሲያደንቁዋቸውም ሰማ:: እርሱ በዛ ወቅት ባሕታውያን በበርሃ መኖራቸውን አያውቅም ነበርና ሒዶ መምሕሩን አባ ኤስድሮስን ጠየቃቸው:: እርሳቸውም "አዎ ልጄ! ከዚሕ በጣም ርቅው: ንጽሕናቸውን ጠብቀው: ከሰውና ከኃጢአት ተይለው የሚኖሩ ገዳማውያን አሉ" አሉት::
ቅዱስ አቡናፍር "በዚሕ ካሉት መነኮሳትና በበርሃ ካሉት ማን ይበልጣል?" ቢላቸው "እነርሱ በጣም ይበልጣሉ:: ዓለም እንኩዋ ከነ ክብሯ የእግራቸውን ሰኮና አታህልም" አሉት:: ይሕንን የሰማው ቅዱስ አባ አቡናፍር ጊዜ አላጠፋም::
ከመምሕሩ ቡራኬ ተቀብሎ ወደ በርሃ ሔደ:: ለብዙ ቀናት ከተጉዋዘ በኋላ አንድ ባሕታዊ አግኝቶ አብሯቸው ተቀመጠ:: ከእርሳቸው ዘንድም ሥርዓተ ባሕታውያንን ተምሮ እንደገና ወደ ዋናው በርሃ ጉዞውን ቀጠለ::
ከብዙ ቀናት መንገድ በኋላም አንድ ሠፊ ሜዳ ላይ ደረሰ:: አካባቢው የውሃ ጠብታ የማይገኝበት: ይቅርና መጠለያ ዛፍ የሣር ዘር እንኩዋ የሌለበት ወይም በልሳነ አበው "ዋዕየ ፀሐይ የጸናበት: ልምላሜ ሣዕር የሌለበት: ነቅዐ ማይ የማይገኝበት" ቦታ ነበር:: በዚህ ቦታ ይቅርና የሰው ልጅ አራዊትም አይኖሩበትም::
ለአባ አቡናፍር ግን ተመራጭ ቦታ ነበር:: ቅዱሳኑን ይሕ አያሳስባቸውም:: ምክንያቱም ለእነርሱ ምግባቸውም: ልብሳቸውም ፍቅረ ክርስቶስ ነውና:: አባ አቡናፍር ወደ ፈጣሪ ጸለዩ:: በእግዚአብሔር ቸርነት ከጎናቸው አንዲት ዘንባባ [በቀልት] በቀለች:: ከእግራቸው ሥርም ጽሩይ ማይ [ንጹሕ ምንጭ] ፈለቀች::
ጻድቁ ተጋድሏቸውን ቀጠሉ:: ዓመታት አለፉ:: ልብሳቸውን ፀሐይና ብርድ ጨርሶት ቅጠል ለበሱ:: በዚያ ቦታም የሰው ዘርን ሳያዩ ለ፷ [60] ዓመታት በተጋድሎ ኖሩ:: የሚያርፉበት ጊዜ ሲደርስ እግዚአብሔር አባ በፍኑትዮስን [የባሕታውያንን ዜና የጻፈ አባት ነው] ላከላቸው::
ቃለ እግዚአብሔርን እየተጨዋወቱ ሳለ የአባ አቡናፍር አካሉ ተለወጠ:: እንደ እሳትም ነደደ:: አባ በፍኑትዮስም ደነገጠ:: ታላቁ ገዳማዊ ግን እጆቻቸውን ዘርግተው ጸለዩ: ሰገዱና አማተቡ:: ነፍሳቸውም ከሥጋቸው በፍቅር ተለየች:: ቅዱሳን መላዕክትም በዝማሬና በማኅሌት አሳረጉዋት:: የሚገርመው ደግሞ አባ በፍኑትዮስ ይሕን ሲያይ ቆይቶ ዘወር ቢል ዛፏ ወድቃለች: ቅርንጯም ደርቃለች::
ዳግመኛ ይህች ዕለት የቅዱሳን አበው ባሕታውያን መታሠቢያ ናት::
ከሰው [ ከዓለም ] ርቀው: ንጽሕ ጠብቀው: ዕጸበ ገዳሙን: ግርማ አራዊቱን: ጸብዐ አጋንንትን ታግሠው የኖሩ: ስማቸውን የምናውቀውንም ሆነ የማናውቃቸውን እንድናከብራቸው ቤተ-ክርስቲያን ሥርዓትና በዓል ሠርታለች::
አምላካችን ከአበው ባሕታውያን ጸጋ በረከት ይክፈለን::
🕊
[ † ሰኔ ፲፮ [ 16 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]
፩. አባ አቡናፍር ገዳማዊ [ስም አጠራሩ የከበረ:
ሽምግልናው ያማረ አባት]
፪. አበው ቅዱሳን ባሕታውያን [ ዛሬ የሁሉም ቅዱሳን ባሕታውያን [በተለይም የስውራኑ] ዓመታዊ በዓል ነው::
- ከሰው: ከዓለምና ከኃጢአት ርቀው
- ንጽሕ ጠብቀው
- ዕጸበ ገዳሙን
- ድምጸ አራዊቱን
- ግርማ ሌሊቱን
- የሌሊቱን ቁር
- የመዓልቱን ሐሩር
- ረሐቡን: ጽሙን: መራቆቱን . . . ሁሉ
ስለ ፍቅረ-ክርስቶስ ሲሉ ታግሠውታልና::
"ዛሬም በየበርሃው የወደቁ: ስለ ዓለም ምሕረትን
የሚማጸኑ አሉ::"
አምላካቸው በረከታቸውን ያድለን።
፫. የእግዚአብሔር መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ከግብጽ እንዲመለስ የነገረበት [ተዝካረ ሚጠታ ለእግዝእትነ ማርያም]
፬. አፄ ይኩኖ አምላክ [ንጉሠ ኢትዮዽያ]
[ † ወርኃዊ በዓላት ]
፩፡ ኪዳነ ምሕረት ማርያም
፪፡ ቅድስት ኤልሳቤጥ
፫፡ አባ ዳንኤል ገዳማዊ
፬፡ ቅዱስ አኖሬዎስ ንጉሠ ሮሜ
፭፡ አባ ዮሐንስ ወንጌሉ ዘወርቅ
፮፡ ቅዱስ ሐርቤ ንጉሠ ኢትዮጵያ
" . . . ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ: ከዚሕም በላይ በእሥራትና በወኅኒ ተፈተኑ . . . ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ: እየተጨነቁ: የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ:: ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ: በዋሻና በምድር ጉድጉዋድ ተቅበዘበዙ:: ዕብ.፲፩፥፴፮] (11:36) "
† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †
[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]
† † †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖 🕊 💖
BY አብሰራ ገብርኤል ለማርያም
Share with your friend now:
tgoop.com/Enatachn_mareyam/18172