tgoop.com/Enatachn_mareyam/18124
Last Update:
🕊
[ እንኳን ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል እና ለቅዱሳኑ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፣ አደረሰን። ]
† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †
🕊
በዚህች ቀን ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤልን ጨምሮ ቅዱስ ላሊበላ: ቅድስት አፎምያና ቅዱስ ባሕራን ቀሲስ ይከበራሉ::
💖
🕊 † ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት † 🕊
ቅዱስ ሚካኤል በጥንተ ተፈጥሮ በኢዮር: ኃይላት በተባሉት ነገደ መላእክት ተሹሞ ነበር:: ሳጥናኤል በካደ ጊዜ እግዚአብሔር ባወቀ : አንድም በትሕትናውና ደግነቱ በ፺፱ኙ ነገደ መላእክት ላይ ሁሉ ተሹሟል::
ከፍጥረት ወገን ከእመቤታችን ቀጥሎ የቅዱስ ሚካኤልን ያሕል ክብርና ርሕሩሕ የለም:: በምልጃውም: በረዳትነቱም የታወቀ መልአክ ነው:: መጽሐፍ "መልአከ ምክሩ ለእግዚአብሔር" ይለዋል:: "ወስሙ መስተሣሕልም" ይለዋል:: ቂም የሌለው: ለምሕረት የሚፋጠን: ደግ መልአክ ነውና::
በብሉይ ኪዳን በመከራ ለነበሩ ቅዱሳን ሁሉ ሞገስ: ረዳትና አዳኝ ቢሆናቸው "መጋቤ ብሉይ" ተሰኝቷል:: እሥራኤልን ፵ ዘመን በበርሃ መርቷል: መግቧልም:: ቅዱስ መጽሐፍ ስለ እርሱ ብዙ ይላል:: [ዘፍ.፵፰፥፲፮, ኢያ. ፭፥፲፫, መሳ. ፲፫፥፲፯, ዳን. ፲፥፳፩, ፲፪፥፩, መዝ. ፴፫፥፯, ራዕይ. ፲፪፥፯] ደስ የሚለው ደግሞ ርሕሩሑ መልአክ ከእመቤታችን ጋር ልዩ ፍቅር አለው:: ከእናቷ ማሕጸን ጀምሮ እስከ ዛሬ እነሆ አብሯት አለ:: ደስ ብሎት ይታዘዛታል:: ማማለድ ሲፈልግም "እመቤቴ ሆይ! ቅደሚ" ይላታል:: ወደ እሳት መጋረጃ አብረው ገብተው ለዓለም ምሕረትን: በረከትን ያወርዳሉ::
ቅዱስ ሚካኤልን በዚሕች ዕለት ስለ እነዚህ ነገሮች እናከብረዋለን:-
፩. በመላእክት ሁሉ ላይ አለቃ ሆኖ መሾሙን
፪. ቅድስት አፎምያን መርዳቱን
፫. ቅዳሴ ቤቱን [ ግብፅ ውስጥ ]
፬. ቅዱስ ባሕራንን መጎብኘቱን
፭. ቅዱስ ላሊበላን ወደ ሰማያት ማሳረጉን
፮. ለፍጥረታት ሁሉ ምሕረት የሚጠይቅበት ዕለት ነውና
††† ሊቀ መላእክት በክንፈ ረድኤቱ ከክፉ ሁሉ ይጠብቀን::
🕊 † ቅዱስ ላል ይበላ ንጉሥ † 🕊
† በ፲፪ [12] ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ ላይ በሃገራችን የነገሠው ቅዱስ ላሊበላ:-
- በብሥራተ መልአክ ተወልዷል
- ቅዱሳት መጻሕፍትን ገና በልጅነቱ አጥንቷል
- የንጉሥ ዘር ቢሆንም በጾምና ጸሎት: በትሕርምት አድጓል
- በወንድሙ ቢገረፍም ቂም አልነበረውም
- ስለ ወዳጆቹ ፍቅር መርዝ ጠጥቷል
- በዙፋን ላይ የኢትዮዽያ ንጉሥ ሆኖ ቢቀመጥም እርሱስ አኗኗሩ ገዳማዊ ነበር
- ከተባረከች ሚስቱ ቅድስት መስቀል ክብራ ጋር አንዲት ማዕድ ብቻ በቀን ይቀምሱ ነበር:: ለዛውም ለምለሙን ለነዳያን ሰጥተው እነርሱ የሚበሉት የእንጀራውን ቅርፍት [ጠርዝ] ብቻ ነበር::
በአካለ ሥጋ ወደ ሰማያት ተነጥቆ ብዙ ምሥጢራትን አይቷል
- በምሳሌውም ሃገረ ሮሃን [ላስታን] ገንብቷል
- ዛሬም ድረስ ምስጢር የሆኑት ፍልፍል አብያተ መቃድስ የእጆቹ ሥራዎች ናቸው::
ሥራውን ከፈጸመ በኋላ መንግሥቱን ለቅዱስ ነአኩቶ ለአብ አውርሶ: በመንኖ ጥሪትና በቅድስና ኑሮ በዚሕች ቀን አርፏል:: ጌታችን ስምህን ያከበረ: ዝክርህን የዘከረ: ከቤትህ ያደረውን: ከርስተ መንግስተ ሰማያት አካፍለዋለሁ ሲል ቃል ኪዳን ገብቶለታል::
††† በረከቱን: ክብሩን ያድለን::
🕊 † ቅድስት አፎምያ † 🕊
ከቅዱስ አስተራኒቆስ ጋር በተቀደሰ ትዳር የኖረች
- ምጽዋትን ያዘወተረች
- በፍቅረ ቅዱሳን የጸናች
- ንጽሕናዋን ጠብቃ ሰይጣንን ያሳፈረች ደግ እናት ናት:: ዛሬ የቅዱስ ሚካኤልን ስዕል ታቅፋ: በትእምርተ መስቀልም አማትባ አርፋለች: ቅዱሱ መልአክም ወደ ገነት አሳርጓታል::
🕊 † ቅዱስ ባሕራን ቀሲስ † 🕊
የደጋግ ክርስቲያኖች ግን የድሆች ልጅ:
- በሕጻንነቱ በግፍ ወደ ባሕር የተጣለ:
- በእግዚአብሔር ጥበብ አድጎ የግፈኛውን ንብረት የወረሰ:
- በመልካም ትዳር በቅስና ያገለገለ:
- ምጽዋትን ያዘወተረ: አብያተ ክርስቲያናትን ያሳነጸ ደግ ክርስቲያን ነው::
- በዚህች ቀን አርፎ ቅዱስ ሚካኤል ወዳጁ በዕረፍተ ገነት አኑሮታል::
† አምላካችን እግዚአብሔር ከቅዱሳኑ በረከት ይክፈለን:: አሜን:: †
🕊
[ † ሰኔ ፲፪ [ 12 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]
፩. ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት
፪. ቅዱስ ላሊበላ ጻድቅ [ንጉሠ ኢትዮዽያ]
፫. ቅድስት አፎምያና ባለቤቷ ቅዱስ አስተራኒቆስ
፬. ቅዱስ ባሕራን ቀሲስ
፭. ቅዱስ እለ እስክንድሮስ ሊቅ
፮. አባ ዮስጦስ ሊቀ ዻዻሳት [የሐዋርያው ቅዱስ ማርቆስ ደቀ መዝሙር]
፯. አባ ቄርሎስ ሊቀ ዻዻሳት
[ † ወርሐዊ በዓላት ]
፩. ቅዱስ ማቴዎስ ሐዋርያ
፪. ቅዱስ ድሜጥሮስ
፫. ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ
፬. ቅዱስ ቴዎድሮስ ምሥራቃዊ [ሰማዕት]
፭. ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
፮. አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ
† ❝ በሰማይም ሰልፍ ሆነ:: ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ:: ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ:: አልቻላቸውምም:: ከዚያም ወዲያ በሰማይ ሥፍራ አልተገኘላቸውም:: ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ወደ ምድር ተጣለ:: ❞ † [ራዕይ.፲፪፥፯] (12:7)
† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †
[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]
† † †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖 🕊 💖
BY አብሰራ ገብርኤል ለማርያም
Share with your friend now:
tgoop.com/Enatachn_mareyam/18124