tgoop.com/Enatachn_mareyam/18042
Last Update:
🕊
[ † እንኳን ለጻድቅና ሰማዕት አባ ቴዎድሮስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን። † ]
† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †
🕊 † አባ ቴዎድሮስ † 🕊
† አባ ቴዎድሮስ በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን የነበረ ግብፃዊ አባት ነው:: ተወልዶ ባደገባት የእስክንድርያ ከተማ ብሉያትንና ሐዲሳት በወቅቱ ከነበሩ አበው ሊቃውንት ተምሯል:: ጊዜው ምንም መናፍቃን የበዙበት ቢሆን በዛው ልክ እነ ቅዱስ እለ እስክንድሮስና ቅዱስ አትናቴዎስን የመሰሉ ቅዱሳን ሊቃውንት ነበሩና ከነሱ የሚገባውን ወስዷል::
አባ ቴዎድሮስ "አባ" ያሰኘው ሥራው:- ሲጀመር ገና በወጣትነቱ ድንግልናንና ምንኩስናን በመምረጡ ነበር:: ምንም እንኳ ሐብት ከእውቀት ጋር ቢስማማለትም ይሕ እርሱን ከምናኔ ሊያስቀረው አልቻለም:: ከከተማ ወጥቶ: በዓት ወስኖ በጾምና በጸሎት ተወሰነ::
በ፫፻፵ [340] ዎቹ ዓ/ም አካባቢ ግን በምዕመናን ላይ ከባድ ችግር ደረሰ:: የወቅቱ ነገሥታት በስመ ክርስቲያን አርዮሳውያን ነበሩና ሕዝቡን ማስገደድ: አንዳንዴም የአርዮስን እምነት ያልተቀበለውን ማስገደል ጀመሩ:: በዚህ ምክንያትም ታላቁ የኦርቶዶክስ ጠበቃ ቅዱስ አትናቴዎስን ከመንበሩ አሳደዱት:: በምትኩም አርዮሳዊ ሰው ዻዻስ ተብሎ ተሾመ:: ይህን ጊዜ ነው እንግዲህ እውነተኛ እረኛ ያስፈለገው::
በበዓቱ የነበረው አባ ቴዎድሮስ አላቅማማም:: ቤተ ክርስቲያን ትፈልገዋለችና መጻሕፍትን ገልጾ ከቦታ ቦታ እየተዘዋወረ ምዕመናንን ያጸናቸው ጀመር:: መናፍቃኑን ተከራክሮ ምላሽ በማሳጣት ሕዝቡን ከኑፋቄ በመጠበቅ የሠራው ሥራ ሐዋርያዊ ቢያሰኘውም ለአርዮሳዊው ዻዻስ [ጊዮርጊስ ይባላል] ሊዋጥለት አልቻለም:: በቁጣ ወታደሮችን ልኮ አባ ቴዎድሮስን ተቆጣው:: እንዳያስተምርም ገሰጸው:: አባ ቴዎድሮስ ግን እሺ ባለማለቱ ግርፋት ታዘዘበት::
ወታደሮች እየተፈራረቁ ሲገርፉት ረድኤተ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበርና ከዛ ሁሉ ግርፋት አንዲቷም አካሉ ላይ አላረፈችም:: በዚህ የተበሳጨው አርዮሳዊ ዻዻስ የአባ ቴዎድሮስን እጅና እግር ከፈረስ ጋሪ በኋላ አስረው በኮረኮንች መንገድ ላይ በፍጥነት እንዲያሮጧቸው አዘዘ::
ፈረሶቹ መሮጥ ሲጀምሩ የአባ ቴዎድሮስ አካሉ ይላላጥ ጀመር:: ትንሽ ቆይቶ ግን እጆቹ ተቆረጡ:: በኋላም ራሱ ከአንገቱ ተለይታ መንገድ ላይ ወደቀች:: አካሉ በሙሉ መሬት ላይ ተበታተነ:: እግዚአብሔር ቅድስት ነፍሱን ተቀብሎ አሳረጋት::
† ለቅዱሱም ፫ [ 3 ] አክሊል ከሰማይ ወርዶለታል :-
፩. ስለ ፍጹም ምናኔውና ድንግልናው
፪. ስለ ሐዋርያዊ የወንጌል አገልግሎቱ
፫. ስለ ሃይማኖቱ ደሙን አፍስሷልና
"እምአባልከ ተመቲራ ለእንተ ሠረረት ርዕስ:
እግዚአብሔር አስተቄጸላ በአክሊል ሠላስ" እንዳለ መጽሐፍ::
ምዕመናን ሥጋውን ሰብስበው በዝማሬና በማኅሌት በክብር ቀብረውታል::
† አምላካችን ከቅዱሱ በረከት ይክፈለን::
🕊
[ † ሰኔ ፮ [ 6 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]
፩. ቅዱስ አባ ቴዎድሮስ ሰማዕት
፪. አባ ገብረ ክርስቶስ
፫. ፵ "40" ሰማዕታት
[ † ወርሐዊ በዓላት ]
፩. ቅድስት ደብረ ቁስቋም
፪. አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን
፫. አባታችን ኖኅና እናታችን ሐይከል
፬. ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ
፭. ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
፮. ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ
፯. ቅድስት ሰሎሜ
፰. አባ አርከ ሥሉስ
፱. አባ ጽጌ ድንግል
፲. ቅድስት አርሴማ ድንግል
† " መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ:: ሩጫውን ጨርሻለሁ:: ሃይማኖቴን ጠብቄአለሁ:: ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል:: ይህንም ጻድቅ: ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያሰረክባል:: ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም:: " † [፪ጢሞ.፬፥፯] (4:7)
† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †
[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]
† † †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖 🕊 💖
BY አብሰራ ገብርኤል ለማርያም
Share with your friend now:
tgoop.com/Enatachn_mareyam/18042