tgoop.com/Enatachn_mareyam/18019
Last Update:
🕊
✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞
❖ ሰኔ - ፬ - ❖
[ ✞ እንኩዋን ለታላቁዋ ሰማዕት "ቅድስት ሶፍያ" እና ለቅዱስ "ዮሐንስ ዘሐራቅሊ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞ ]
† 🕊 ሶፍያ [ SOPHIA ] 🕊 †
ሶፍያ [ "ያ" የሚለው ላልቶ ይነበብ ] በቀደመው ዘመን በነበሩ ክርስቲያኖች ዘንድ ተወዳጅ ስም ነበር:: ዛሬ ብዙ አሕዛብ ሲጠሩበት ብንሰማም ትርጉሙ "ጥበበ ክርስቶስ" የሚል ነው:: በዚህ ስም የሚጠሩ አያሌ ቅዱሳት አንስት ሲኖሩ አንዷ ዛሬ ትከበራለች::
† 🕊 ቅድስት ሶፍያ ተጋዳሊት 🕊 †
ቅድስቷ የተወለደችው በምሥራቅ ሮም ግዛት ውስጥ በ ፫ [3] ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: ዘመኑ የጭንቅ : የመከራ በመሆኑ ሕዝቡ በስደት ይኖር ነበር::
የቅድስት ሶፍያ ወላጆች ክርስቲያኖች ናቸውና በመልካሙ መንገድ በንጽሕና አሳድገዋታል:: ባለጠጐች በመሆናቸው አገልጋይ ቀጥረውላት : ያማረ ቤት ሰርተውላት በዚያ ትኖር ነበር:: ሁሉ ያላት ብትሆንም ሁሉን ንቃ በጾምና በጸሎት ትኖር ነበር::
ለዐቅመ ሔዋን በደረሰች ጊዜ ወላጆቿ ለከተማው መኮንን [ገዢ] ሊድሯት መሆኑን አወቀች:: ወደ ቤቷ ገብታ ፻ [100] ጊዜ ሰገደች:: ወደ ፈጣሪዋም ጸለየች:- "ጌታየ ሆይ! የዚህን ዓለም ቀንበር አታሸክመኝ:: አልችለውምና:: ያንተው ቀንበር ግን የፍቅር ነውና እችለዋለሁ" አለች::
አገልጋዩዋን ጠርታ ብዙ ወይን አጠጥታት ልብስ ተቀያየሩ:: በሌሊትም ወጥታ ወደ በርሃ ሔደች:: ዓላማዋ ምናኔ ቢሆንም የእግዚአብሔር ፈቃዱ ግን ሌላ ነበር:: በመንገድ ብዙ ክርስቲያኖች በመከራ ብዛት ሲሰደዱ አገኘቻቸው:: እርሷ ስደትን አልመረጠችም::
እያጠያየቀች "ሰው በላ" ከተባለው አረመኔ ንጉሥ ዲዮቅልጢያኖስ ደረሰች:: በንጉሡ ፊት ቀርባ "እኔ ክርስቲያን ነኝ" አለችው:: ንጉሡ ከመልኩዋ ማማርና ከድፍረቷ የተነሳ አደነቀ::
ሊያባብላት: ሊያስፈራራትም ሞከረ:: ግን አልተሳካለትም:: ወታደሮቹ መሬት ላይ ጥለው ጦር ባለው የብረት ዘንግ ደብድበዋታልና ደም አካባቢውን አለበሰው:: መሬት ለመሬት እየጐተቱ እሥር ቤት ውስጥ ጣሏት:: ቅዱስ ገብርኤል መጥቶ ፈውሷት ሔደ::
አንዴ በእሳት: አንዴም በስለት: ሌላ ጊዜም በግርፋት አሰቃዩዋት:: ከሃይማኖቷ ግን ሊያነቃንቁዋት አልቻሉም:: በመጨረሻ አንገቷን እንድትሰየፍ ንጉሡ አዘዘ:: ወታደሮቹም ፈጸሙት:: ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወርዶ ቅድስት ሶፍያን በክብር አሳረጋት:: "ስምሽን የጠራ: መታሰቢያሽን ያደረገ ምሕረትን ያገኛል" አላት::
† 🕊 ቅዱስ ዮሐንስ ዘሐራቅሊ 🕊 †
ቅዱሱ የነበረው በተመሳሳይ በዘመነ ሰማዕታት ነው:: አባቱ ዘካርያስ: እናቱ ኤልሳቤጥ: እርሱ ደግሞ ዮሐንስ ይባላል:: የሚገርም መንፈሳዊ ግጥጥሞሽ ነው:: የቅዱሱ ወላጆች የሃገረ ሐራቅሊ አስተዳዳሪዎች ሲሆኑ የተመሰከረላቸው ደጐች ነበሩ::
ዘካርያስ አርፎ ዮሐንስ በመንበሩ የተቀመጠው ገና በ ፳ [20] ዓመቱ ነበር:: በወቅቱ ከ፪ [2] አንዱን መምረጥ ነበረበት::
፩. ለጣኦት ሰግዶ በምድራዊ ክብሩ መቀጠል
፪. ወይ ደግሞ በክርስትናው መሞት
ቅዱስ ዮሐንስ ግን ልቡ በክርስቶስ ፍቅር የተሞላ ነውና ፪ [2] ከባባድ ነገሮችን ፈጸመ:: በመጀመሪያ በአካባቢው ያሉ ጣዖት ቤቶችን አወደመ:: ቀጥሎ ወደ ንጉሡ ሔዶ በመኩዋንንቱ ፊት "ክርስቶስን የተውክ ሰነፍ" ብሎ ገሠጸው::
ከዚህ በኋላ በቅዱሱ ላይ የተፈጸመው መከራ የሚነገር አይደለም:: ያላደረጉት ነገር አልነበረም:: እሳቱ: ስለቱ: ሰይፉ: መንኮራኩሩ . . . ከሁሉ የከፋው ግን ቆዳውን ገፈው በእሳት ጠብሰውታል:: እርሱ ግን ስለ ሃይማኖቱ ይሕንን ሁሉ ታግሶ በዚህች ቅን አንገቱን ተሰይፏል::
አምላካችን እግዚአብሔር ግፍዐ ሰማዕታትን አስቦ እኛን ከሚመጣው መከራ ሁሉ ይሰውረን:: ከበረከታቸውም ይክፈለን::
🕊
[ † ሰኔ ፬ [ 4 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]
፩. ቅድስት ሶፍያ ተጋዳሊት ወሰማዕት
፪. ቅዱስ ዮሐንስ ዘሐራቅሊ [ሰማዕት]
፫. ቅዱስ ሳኑሲ ሰማዕት
፬. ቅድስት ማርያ ሰማዕት
፭. ቅዱስ አርቃድዮስና ባልንጀሮቹ [ሰማዕታት
፮. ቅዱስ አሞን ሰማዕት
[ † ወርኃዊ በዓላት ]
፩፡ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ
፪፡ ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ
" እንግዲሕ አትፍሯቸው:: የማይገለጥ የተከደነ: የማይታወቅም የተሠወረ ምንም የለምና:: በጨለማ የምነግራችሁን በብርሃን ተናገሩ:: በጀሮም የምትሰሙትን በሰገነት ላይ ስበኩ:: ሥጋንም የሚገድሉትን: ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ:: ይልቅስ ነፍስንም: ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ:: " [ማቴ.፲፥፳፮] (10:26)
† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †
[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]
† † †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖 🕊 💖
BY አብሰራ ገብርኤል ለማርያም
Share with your friend now:
tgoop.com/Enatachn_mareyam/18019