tgoop.com/Enatachn_mareyam/16670
Last Update:
🕊
✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞
[ ✞ እንኩዋን ለጻድቁ "አቡነ ክፍለ ማርያም" እና ለሰማዕቱ ቅዱስ "ፊልሞን መዓንዝር" ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞ ]
🕊 ✞ አቡነ ክፍለ-ማርያም ✞ 🕊
ኢትዮዽያዊው ጻድቅ አቡነ ክፍለ-ማርያም በሐዋርያዊ አገልግሎቱ የተመሠከረለት: ለበርካታ ዓመታት በጾምና በጸሎት በአቱን አጽንቶ የኖረ: ከቅድስናው የተነሳ መላዕክት ሰማያዊ ኅብስት ይመግቡት: ውሃም ከአለት ላይ ይፈልቅለት የነበረ አባት ነው::
በዘመኑም ረሃብ ነበርና እርሷ ሳታውቀው እናቱን በረሃብ ጠውልጋ ቢያያት በጣም በማዘኑ እንዲባርከው ከቀረበለት የሰንበት ቁርስ ለእናቱ አድልቶ ብዙ ሰጣት:: በዚሕ ምክንያት መልዐኩም ሰማያዊ ኅብስቱን አስቀረበት: ምንጩም ደረቀች::
ጥፋቱ የገባው አባ ክፍለ-ማርያም ለ፲፩ [11] ዓመታት ንስሃ ገብቶ እግዚአብሔር መልሶለታል:: ከብዙ የገድል ዓመታት በሁዋላም በዚህች ቀን ተሠውሯል::
🕊 ✞ ቅዱስ ፊልሞን ሰማዕት ✞ 🕊
ይህን ቅዱስ "ፊልሞን መዓንዝር" ብሎ መጥራቱ የተለመደ ነው:: እርሱ በቀደመ ሕይወቱ አዝማሪ [ዘፋኝ] ነበርና:: ዘፋኝነት [አዝማሪነት] ደግሞ በክርስትና ከተከለከሉ ተግባራት አንዱና ዋነኛው በመሆኑ ዘፈን [ሙዚቃ] መስማትም ሆነ ማድመጡ ኃጢአት ነው::
ነገር ግን ሁሉ እንዲድን የሚፈቅድ ጌታችን ጥሪውን ወደ ሁሉም ሰው በየጊዜው ይልካል:: ቅዱስ ፊልሞንም የክርስቶስ ጥሪ የደረሰው በከንቱ የዘፋኝነት [የአዝማሪነት] ኑሮ ውስጥ ሳለ ነው:: ነገሩ እንዲህ ነው :-
በ፫ [3] ኛው ክ/ዘ መጨረሻ [በ፪፻፺ [290] ዎቹ] አርያኖስ የሚባል ሹም በግብጽ [እንዴናው] ክርስቲያኖችን ጨፈጨፈ:: ባለማወቅም ክርስቶስን የሚያመልኩ ሚሊየኖችን በሰይፍ በላቸው:: ከዚህ ድርጊቱ መልስ ደግሞ በጣዖቱ [አዽሎን] ፊት እያስዘፈነ ከንቱነትን ይሰዋ : ይዝናናም ነበር::
ከዘፋኞቹ መካከል ደግሞ ይህ ፊልሞን አንዱ ሆኖ ለዘመናት በፊቱ ተጫወተለት:: አንድ ቀን ግን እንዲህ ሆነ:: አስቃሎን የሚባል ቅዱስ ክርስቲያን ለጣዖት እንዲሰዋ ታዘዘ::
ይህ አስቃሎን [አብላንዮስም ይባላል] ወንድሙን ፊልሞንን ያድነው ዘንድ ተጠበበ:: ወደ ፊልሞን ሒዶ "እኔ ገንዘብ እሰጥሃለሁ:: የእኔን ልብስ ለብሰህ : እኔን መስለህ ለጣዖት ሰዋልኝ" አለው:: አስቃሎን ይህንን ያለው ለጥበቡ ሲሆን ፊልሞን ግን "ገንዘብ ካገኘሁ" ብሎ የባልንጀራውን ልብስ ተሸፋፍኖ ወደ ጣዖቱ ፊት ቀረበ::
ያን ጊዜ ተሸፍኖ መስዋዕት ማቅረብ ክልክል ነውና ሹሙ አርያኖስ ግለጡት ሲል አዘዘ:: ቢገልጡት ፊልሞን ሁኖ ተገኘ:: መኮንኑ ገርሞት "ምን እያደረክ ነው?" ቢለው "እኔ ክርስቲያን ነኝ" ሲል አሰምቶ ተናገረ::
ለጊዜው ሁሉም እየቀለደ መስሏቸው ነበር:: ፊልሞን ግን ይህንን ያለው ከልቡ ነው:: ምክንያት በቅዱስ አስቃሎን ልብስ ተመስሎ መንፈስ ቅዱስ ልቡን ለውጦለት ነበር:: ተገልጦ ቀና ሲልም ቅዱሳን መላእክት ከበውት አይቶ ልቡ ጸንቶለታል::
ሹሙ አርያኖስም የቀልዱን እንዳልሆነ ሲያውቅ "ታብዳለህ?" ቢለው ፊልሞን "ምን አብዳለሁ! ዛሬ ገና ከእብደቴ ሁሉ ዳንሁ እንጂ" ሲል መልሶለታል:: አሕዛብ ሁሉ እያዩም በዚያች ቅጽበት መንፈስ ቅዱስ በደመና አምሳል ወርዶ አጥምቆታል::
በሆነው ሁሉ የተበሳጨው ሹሙም ቅዱስ ፊልሞንን ከክርስቶስ ፍቅር ይለየው ዘንድ ደበደበው : ገረፈው : ጥርሱን አረገፈው : ደሙንም መሬት ላይ አፈሰሰው:: በዚህ ሁሉ ግን ጸና:: ቅዱስ አስቃሎንም ፈጥኖ መጥቶ በመከራው መሰለው::
በመጨረሻም ፪ [2] ቱም ቅዱሳን በቀስት ተነድፈው ይገደሉ ዘንድ ተፈረደባቸው:: ነገር ግን ለእነሱ የተወረወረ ቀስት መንገዱን ስቶ የሹሙን [የአርያኖስን] ዐይን በማጥፋቱ ወታደሮቹ በንዴት ፪ [2] ቱንም ሰይፈው ገድለዋቸዋል::
ዐይኑ የጠፋበት አርያኖስም ስቃዩ ሲበዛበትና ከሚያመልካቸው የረከሱ ጣዖታት መፍትሔ ሲያጣ ከቅዱሳኑ ደም ተቀባ:: ዐይኑም ፈጥኖ በራለት:: በዚህም ምክንያት ምድራዊ ሹመቱን : ሃብት ንብረቱን : ትዳርና ቤቱን : ጣዖት አምልኮውን ትቶ በክርስቶስ አምኖ ለሰማዕትነት በቅቷል::
አምላከ ቅዱሳን በወዳጆቹ አማላጅነት የምናስተውልበትን አዕምሮ አይንሳን:: በረከታቸውንም ያድለን::
🕊
[ † የካቲት ፳ [ 20 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]
፩. አቡነ ክፍለ-ማርያም ዘዲባጋ [የተሰወረበት]
፪. አቡነ ገብረ-መርዐዊ ዘአግዶ [ኢትዮዽያዊ]
፫. ቅዱስ ፊልሞን መዐንዝር [ከአዝማሪነት በክርስቶስ አምኖ ለሰማዕትነት የበቃ ቅዱስ ሰው]
፬. ቅዱስ አስቃሎን አናጉንስጢስ [ሰማዕት]
፭. ቅዱስ ዼጥሮስ ሊቀ ዻዻሳት [የታላቁ ሐዋርያዊ አትናቴዎስ ደቀ መዝሙር]
[ † ወርኀዊ በዓላት ]
፩. ቅዱስ ቴዎድሮስ ሊቀ ሠራዊት (ሰማዕት)
፪. ቅዱስ ዮሐንስ ሐፂር
፫. ቅዱስ አክሎግ ቀሲስ
፬. ቅዱስ አፄ ካሌብ ጻድቅ
፭. አባ አሞንዮስ ዘሃገረ ቶና
፮. ቅድስት ሳድዥ የዋሒት
" ስትጦሙም እንደ ግብዞች አትጠውልጉ . . . አንተ ግን ስትጦም በስውር ላለው አባትህ እንጂ እንደ ጦመኛ ለሰዎች እንዳትታይ ራስህን ተቀባ: ፊትህንም ታጠብ:: በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ያስረክብሃል:: " [ማቴ.፮፥፲፮]
† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †
[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]
† † †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖 🕊 💖
BY አብሰራ ገብርኤል ለማርያም
Share with your friend now:
tgoop.com/Enatachn_mareyam/16670