tgoop.com/Enatachn_mareyam/16648
Last Update:
†
† 🕊 ዘ ወ ረ ደ 🕊 †
[ የጾምን መግባት ምክንያት በማድረግ የተሰጠ ትምህርት ! ]
💖
[ ክፍል ሁለት ]
❝ እንኪያስ እጅግ የምወዳችሁ ምእመናን ሆይ ! ከኹሉም በፊት እነዚህን ነገሮች በስፋት እንነጋገርባቸው ዘንድ ፤ ዳግመኛም አንዳች የሚረባንን ነገር ይዘን ወደ ቤታችን እንመለስ ዘንድ ቃላችንን በታላቅ ትጋትና ጉጉት ሆናችሁ ትቀበሉት ዘንድ አሳስባችኋለሁ፡፡
ኹላችንም ወደዚህ ጉባኤ ስንመጣ እንዲሁና ያለ ዓላማ አይደለም፡፡ ወሬ ለማውራት ፣ ምን እንደተባለ እንኳን ሳንሰማ ለማጨብጨብ ፣ ከዚያም ምንም የሚረባ ነገርን ሳንይዝ ወደ ቤታችን ለመመለስ ወደዚህ ጉባኤ አልመጣንም፡፡ እኔ የመጣሁት ለነፍሳችሁ ድኅነት የሚጠቅም አንዳች ነገርን ለመናገር ነው ፤ እናንተም ስትመጡ በእኔ በባሪያው አድሮ እግዚአብሔር የሚናገረውን ነገር አድምጣችሁ ለመጠቀምና አንዳች የሚረባ ነገርን ይዛችሁ ወደ ቤታችሁ ለመመለስ ነው፡፡
ተመልከቱ ! ቤተክርስቲያን ማለት ቤተ ድኅነት ናት፡፡ ወደ እርሷ የሚመጡትም ለችግራቸው ተገቢውን መድኃኒት አግኝተው መሔድ አለባቸው፡፡ ተግባራዊ የኾነ ለውጥ ሳያመጡ ቃለ እግዚአብሔርን መማር ብቻ ምንም ጥቅም እንደሌለው ሲናገርም ንዑድ ክቡር የሚኾን ጳውሎስ እንዲህ ብሏል ፦
"በእግዚአብሔር ፊት የሚጸድቁት ሕግን የሚያደርጉት እንጂ ሕግን የሚሰሙ አይደሉም፡፡" [ሮሜ.፪፥፲፫]
በቃል መነገሩ ፣ በልብ መታሰቡ ፣ በቅዱሳት መጻሕፍት መዘገቡ ከፍ ከፍ ይበልና አምላካችን ክርስቶስም ሲያስተምር ፦
"በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም፡፡" ብሏል [ማቴ.፯፥፳፩] ስለዚህ ተወዳጆች ሆይ ! ቃሉን በመስማታችን ብቻ አንዳች የምንጠቀመው ነገር ስለሌለ የሰማነውን የምናደርግ እንጂ የምንሰማ ብቻ አንሁን፡፡ እንዲህ ከሆነም እምነታችን ሕይወት ያለው እምነት ይሆናል፡፡
በመኾኑም ስለ ጾም የሚሰጠውን ስብከት ለማዳመጥ እዝነ ልቦናችሁን ክፈቱ፡፡ ከትሕትና እና ዓይናፋር ሙሽሪት ጋር ለማነጻጸር ያህል ፦ ሙሽሪቱን በሰርግ አዳራሽ ኾነው የሚቀበሏት ሰዎች አስቀድመው ቤቱን ያስጌጡታል ፡ ይጠርጉታል፡፡ የቆሸሸ ልብስን የለበሰ ሰው ወደ ሰርጉ አዳራሽ እንዳይገባ ያደርጉታል፡፡ ወደ አዳራሹ መግባት የሚችለው የሰርግ ልብስ የለበሰ ሰው ብቻ ነው፡፡
እናንተም እንዲሁ ልታደርጉ ይገባችኋል ፦ ልቡናችሁን በማንጻት ፣ አብዝቶ ከመብላትና ራስን ካለመግዛት በመራቅ - የምግባር እናት ፣ የማስተዋልና የሌሎች ምግባራት ኹሉ ንግሥት የምትሆን ጾምን ደጀ ልቡናችሁን በመክፈት ልትቀበሏት ይገባችኋል፡፡ ይህን ያደረጋችሁ እንደሆነ ታላቅ ሐሴት ታደርጋላችሁ ፤ እርሷም ቁስለ ነፍሳችሁን ትፈውስላችኋለች፡፡
ሌላ ምሳሌ መስዬ ብነግራችሁ ፦ ሐኪሞች በህሙማን ሰውነት ውስጥ ያለውን ቆሻሻና መርዘኛ ፈሳሽን ማስወገድ ሲፈልጉ መጀመሪያ ሕሙማኑ ምግበ ሥጋን ከመውሰድ እንዲቆጠቡ ያደርጓቸዋል፡፡ ሕሙማኑ ለጊዜው ምግብን ከመብላት ካልተከለከሉ ግን ሐኪሞቹ የሚሰጡት መድኃኒት የተፈለገውን ያህል ውጤት አይሰጥም፡፡ እኛም የነፍስንና የሥጋን ቁስል የምትፈውሰውን ጾም ስንቀበላት ከዚህ በላይ ልንሆን ይገባናል ብዬ እነግራችኋለሁ፡፡ ድህነትን የምንሻ ከሆነ ልቡናችንን ንጹህና ንቁ በማድረግ ልንወስዳት ይገባናል ፤ እንዲህ ካልሆነ ግን ከጥቅሟ ይልቅ ጉዳቷ ያመዝናል፡፡ ❞
[ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ]
† † †
▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬
💖 🕊 💖
BY አብሰራ ገብርኤል ለማርያም
Share with your friend now:
tgoop.com/Enatachn_mareyam/16648