tgoop.com/Enatachn_mareyam/16606
Last Update:
🕊
[ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን። ]
✞ እንኩዋን ለዐቢይ ጾም በሰላም አደረሳችሁ ✞
🕊 💖 🕊
[ ዐቢይ ጾም " የጌታ ጾም " ]
🍒
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በአዋጅ ምዕመናን እንዲጾሟቸው የሠራቻቸው ፯ [ 7 ] አጽዋማት አሏት:: " ጾም " ማለት "መከልከል" ነው::
የምንከለከለው ደግሞ ከኃጢአትና ከክፋት ሲሆን አንድም ሰውነትን ወደዚያ ከሚወስዱ መባልዕት መከልከልን ይመለከታል::
ጾም ለክፉ ሥራ ከሚያነሣሱ የምግብ ዓይነቶች መከልከል ወይም ለተወሰነ ጊዜና ሰዓት ሰውነት ከሚፈልጋቸው ነገሮች ሁሉ መወሰን [ መታቀብ ] ማለት ነው፡፡ ለሰውነት የሚያምረውንና የሚያስጎመዠውን ነገር ሁሉ ስለ ፍቅረ እግዚአብሔር ብሎ መተው ነው፡፡
ጾም ከመንፈሳዊ ተጋድሎዎች አንዱ ነው፡፡ ለሥጋም መንፈሳዊ ልጓም ነው፡፡ ጸዋሚ ሰው ፈቃደ ሥጋውን እየገታ ነፍሱን የሚያለማምድበት ስንቅ ነው፡፡ "ጾም ቁስለ ነፍስን የምትፈውስ ፤ ኃይለ ፍትወትን የምታደክም ፤ የበጎ ምግባራት ሁሉ መጀመሪያ ፤ ከእግዚአብሔር ጸጋን የምታሰጥ ፤ የወንጌል ሥራ መጀመሪያ ፤ የጽሙዳን ክብራቸው ፤ የድንግልና የንጽሕና ጌጣቸው ፤ የንጽሕና መገለጫ ፤ የጸሎት ምክንያት እናት ፤ የዕንባ መገኛ መፍለቂያዋ ፤ አርምሞን የምታስተምር ፤ ለበጎ ሥራ ሁሉ የምታነቃቃ ፣ ሰውነትን በእግዚአብሔር ፊት በማዋረድ ትሕትናን ገንዘብ ለማድረግ የምትረዳ መድኃኒተ ነፍስ ናት፡፡" [ማር ይስሐቅ አንቀጽ ፬፥፮]
ጾም ተድላ ሥጋን የምታጠፋ ፥ የሥጋን ጾር የምታደክም ፥ ቁስለ ነፍስን የምታደርቅ ፥ ለጎልማሶች ጸጥታንና ዕርጋታን የምታስተምር ፥ ከግብረ እንስሳዊ የምትከለክል ፥ ሰው መላእክትን መስሎ የሚኖርባትና ኃይል መንፈሳዊን የሚጎናጸፍባት ደገኛ መሣሪያ ናት፡፡ ከኃጢአት ፆር ከፍትወት አንዱንም አንዱን ድል ለመንሳት ለማጥፋት ፥ የዲያብሎስን ረቂቅ ፍላጻ ለመመከት በጾም መድከም የሥራ ሁሉ መጀመሪያ እንደሆነች የታወቀ ነው፡፡ ጾም ምህረት መለመኛ ፥ የንስሐ መገለጫ ፥ ከመከራ የሚሠወሩባት ፥ ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር አስታርቃ ርስት መንግሥተ ሰማያት የምታስገባ "ኆኅተ ጽድቅ - የጽድቅ በር" ሆና የተሰጠች ቀዳማዊት ሕግ ናት፡፡
🕊 💖 🕊
[ ዐቢይ ጾም [ ጾመ እግዚእ ] ]
ከ፯ [7] ቱ አጽዋማት አንዱ የሆነው ይህ ጾም
፩. ዐቢይ [ ታላቁ ] ጾም
፪. የጌታ ጾም
፫. ጾመ ሑዳድ
፬. የድል ጾም
፭. የካሳ ጾም
፮. አርባ ጾም
፯. የፍቅር ጾም . . .
በሚሉ መጠሪያዎችም ይታወቃል::
የጾሙ መግቢያ የመጀመሪያ ሳምንት ደግሞ =
፩. ጾመ ሕርቃል
፪. ጾመ በረከት ዘሐዋርያት
፫. ሰሙነ ዘወረደም ይባላል::
የጾሙ የመጀመሪያው ሳምንት [ዘወረደ] የሚጾመው እስከ ፲፪ [ 12 ] ሰዓት ሲሆን ከቅድስት [ ከ፪ [ 2 ] ኛው ሳምንት እስከ ተጽኢኖ [ የኒቆዲሞስ ዓርብ ] ድረስ ደግሞ እስከ ፲፩ [ 11 ] ሰዓት ይጾማል::
በሰሙነ ሕማማት ግን የምንጾመው "እስከ ይሠርቅ ኮከብ" [ እስከ ምሽት ፩ [ 1 ] ሰዓት ] ድረስ ይሆናል::
ነገር ግን ሁሉም እንደ መጠኑ ነውና ከመምሕረ ንስሃ ጋር ሊጨዋወቱት ይገባል:: በዓቢይ ጾም ለቻለ ቂጣ በጨው እየበላ : ውሃ እየተጐነጨ ሊጾም ይገባል:: በእነዚህ ፶፭ [ 55 ] ቀናትም ከዕለተ ሆሳዕና በቀር ከበሮ አይጐሰምም:: ጸናጽል አይጸነጸልም:: ተድላ ደስታም አይደረግም::
አብዝቶ መብላት : ሳቅ ማብዛትና ጌጥን ማብዛትም እንዲሁ አይገባም:: ለቻለ ደግሞ በሌሊት ሰዓታቱን ፡ በነግህ ኪዳንና ስብሐተ ነግሁን : በመዓልት ቅዳሴውን : በሰርክ [ ምሽት ] ደግሞ ምሕላውን ሊሳተፍ ይገባል::
በእነዚህ ፶፭ [ 55 ] ቀናት ፈቃደ ሥጋ ሊደክም : ፈቃደ ነፍስ ልትሰለጥን ግድ ነውና:: ከሌላው ጊዜ በተሻለ ወቅቱ ምጽዋትና ጸሎት የሚደረግበት ነው:: በዚያውም ላይ ነገሮችን እያመቻቹ በእነዚህ ዕለታት ቅዱስ ቃሉን መስማት [ማንበብ] ይገባል:: በትዳር ውስጥ ላሉም መኝታን መለየት ግድ ነው::
ጾሙን የሰላም : የፍቅር : የምሕረት : የፀጋ : የበረከት ያድርግልን:: ጾሞ ለማበርከትም ያብቃን፡፡
" አሁንስ ይላል እግዚአብሔር በፍጹም ልባችሁ በጾምም በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ:: ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ:: አምላካችሁም እግዚአብሔር ቸርና መሐሪ: ቁጣው የዘገየ: ምሕረቱም የበዛ: ለክፋትም የተጸጸተ ነውና ወደ እርሱ ተመለሱ:: " [ትን. ኢዩኤል.፪፥፲፪ (2:12) ]
ወስብሐት ለእግዚአብሔር : ወለወላዲቱ ድንግል : ወለመስቀሉ ክቡር !
[ ይቆየን ! ]
† † †
💖 🕊 💖
BY አብሰራ ገብርኤል ለማርያም
Share with your friend now:
tgoop.com/Enatachn_mareyam/16606