tgoop.com/Enatachn_mareyam/16300
Last Update:
🕊
† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ †
† ጥር ፲፯ [ 17 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት †
† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ! †
🕊 † አበዊነ መክሲሞስ ወዱማቴዎስ † 🕊
- እኒህ ቅዱሳን የሥጋ ወንድማማቾች ሲሆኑ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ እጅግ ተወዳጅ አባቶች ናቸው:: ስንጠራቸውም "አበዊነ ቅዱሳን: ወክቡራን: ሮማውያን: መስተጋድላን: ወከዋክብት ብሩሃን" ብለን ነው::
- ይኸውም "እንደ ንጋት ኮከብ የምታበሩ: ተጋዳይ: ቅዱሳንና ክቡራን የሆናችሁ ሮማውያን አባቶቻችን" ማለት ነው:: ሃገረ ሙላዳቸው ሮም ሁና አባታቸው ንጉሥ ለውንድዮስ ይባላል::
- ይህ ንጉሥ ሮምን በምታክል ታላቅ ሃገር በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ነግሦ ሳለ መልካም ሰው ሆኖ ተገኝቷል:: ከመልካም ሚስቱ [ንግሥቲቱ] ከወለዳቸው መካከልም ፪ቱ ከዋክብት ይጠቀሳሉ:: ፪ቱ ቅዱሳን በአጭር የጊዜ ልዩነት የተወለዱ በመሆናቸው እንደ መንትያ ይቆጠራሉ::
- ንጉሡ ለውንድዮስም ከእግዚአብሔር ዘንድ ላገኛቸው ልጆቹ ስም ሲያወጣ ታላቁን መክሲሞስ: ታናሹን ደግሞ ዱማቴዎስ ብሎታል:: ቅዱሳኑ በንጉሥ አባታቸው መልካም ፈቃድ ክርስትናን ተምረዋል::
- ምንም እንኳ የንጉሥ ልጆች እና ልዑላን ቢሆኑም ተቀማጥለው አላደጉም:: ምቾት ብዙዎችን አጥፍቷልና:: ይህንን የተረዳ አባታቸው ሞገስን በፈጣሪያቸው ዘንድ እንዲያገኙ እንዲህ በበጐ ጐዳና አሳደጋቸው::
- ቅዱሳን መክሲሞስና ዱማቴዎስ ካደጉና ለአካለ መጠን ከደረሱ በኋላ ቅዱሳት መጻሕፍትን ለማንበብ ይተጉ ነበር:: በተለይ ዜና ቅዱሳንን ከማንበብ አይጠግቡም ነበር:: እግዚአብሔርንም በፍቅር እያመለኩ በጾምና በጸሎት ይገዙለት ነበር::
- ቅዱሳኑንም ለየት የሚያደርጋቸው አንዱ ይሔው ነው:: ወርቅና ብር በፊታቸው ፈሶ: በእግራቸው እየረገጡት: አገሩና ምድሩ እየሰገደላቸው: የላመ የጣመ ምግብ እየቀረበላቸው: የሞቀ የደመቀ መኝታ እየተነጠፈላቸው . . . ሁሉንም ስለ ፍቅረ ክርስቶስ መናቃቸው ይደነቃል::
- እነርሱ በክርስቶስ ፍቅር ሆነው የዚህን ዓለም ጣዕም ንቀዋልና የአባታቸውን ቤተ መንግስት ሊተዉ አሰቡ:: አሳባቸው ደግሞ በመመካከር ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ መሪነት: እንደ አንድ ልብ መካሪ: እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ እንዲሉ አበው በጌታ መሪነት ነው::
- ወደ በርሃ ሔደው ለፈጣሪ ለመገዛት ሲያስቡ መውጫ መንገዳቸውን ይሹ ነበርና አንድ ጐዳና ተገለጠላቸው:: ከዚያም ለንጉሥ አባታቸው ሔደው "አባ! እኛ ወደ ኒቅያ [ ታናሽ እስያ ] ሔደን መባረክ እንፈልጋለን" ሲሉ ጠየቁት::
- ወቅቱ ቦታዋ ስለ ፫፻፲፰ [ 318ቱ ] ቅዱሳን ሊቃውንት ሞገስን ያገኘችበት ጊዜ ነበር:: አባታቸውም መንፈሳዊ ሰው ነበርና ደስ እያለው ፈቀደላቸው:: ብዙ ወርቅን ሰጥቶ: ሸልሞ ከብዙ ሠራዊት ጋር ሸኛቸው::
- ቅዱሳኑ መክሲሞስና ዱማቴዎስም ለጥቂት ጊዜ በኒቅያ ሲጸልዩና ሲባረኩ ሰነበቱ:: ቀጥለውም የአባታቸውን ሰራዊት ሰብስበው "እኛ ሱባኤ ልንይዝ ስለ ሆነ እንመጣለን" የሚል ደብዳቤን ሰጥተው ወደ ሮም ሸኟቸው::
- ወታደሮችን ከሸኙ በኋላ ቅዱሳኑ በአካባቢው ወደ ሚገኝ አንድ ገዳም ሒደው ለአንድ ደግ መናኝ ምሥጢራቸውን ገለጹለት:: ልክ የንጉሡ ለውንድዮስ ልጆች መሆናቸውን ሲያውቅ 'አመንኩሰን' ያሉትን እንቢ አላቸው::
- "ለምን?" ሲሉት "ደጉን አባታችሁን ማሳዘን አልፈልግም:: ግን ፈቃዳችሁ እንዲፈጸምላችሁ ወደ ሶርያ ዝለቁ:: በዚያ አባ አጋብዮስ የሚባል ጻድቅ ገዳማዊ ሰው ታገኛላችሁ" ብሎ ወደ ሶርያ አሰናበታቸው::
- በምድረ ሮም: በተለይም በቤተ መንግስቱ አካባቢ የ፪ቱ ልዑላን መጥፋት [ መሰወር ] ሲሰማ ታላቅ ሐዘንና ለቅሶ ተደረገ:: ንጉሡ አባታቸው በወታደሮቹ ዓለምን ቢያካልልም ሊያገኛቸው አልቻለም:: እርሱ ፈጽሞ ሲያዝን እናታቸው ፈጽማ መጽናናትን እንቢ አለች::
- መክሲሞስና ዱማቴዎስ ግን ምድረ ሶርያ ገብትው የጻድቁ አባ አጋብዮስ ደቀ መዛሙርት ሆኑ:: በእርሱም ዘንድ ለምናኔ የሚያስፈልጉ በጐ ምግባራትንና ትሩፋትን ከተማሩ በኋላ ፪ቱንም አመነኮሳቸው:: በዚያ ቦታም እየታዘዙ: ፈጣሪን እያመለኩ: በጾም: በጸሎትና በትህትና ኖሩ::
- አንድ ቀን ግን አባ አጋብዮስ ጠርቶ " ልጆቼ ! ተባረኩ ! በእናንተ ምክንያት ደስ ብሎኛልና:: በዚህች ሌሊት የመነኮሳት ሁሉ አለቃ ታላቁ ቅዱስ መቃርዮስ በራዕ ተገልጦ: ልጆች እንዲሆኑኝ ስጠኝ ብሎኛልና እኔ ሳርፍ ወደ ግብጽ ገዳመ አስቄጥስ እንድትሔዱ" አላቸው::
- አባ አጋብዮስ ካረፈ በኋላ ግን እንደ ትዕዛዙ አልሔዱም:: ውዳሴ ከንቱን ይፈሩ ነበርና:: በዚያው በምድረ ሶርያ ግን በጥቂት ጊዜ: ገና በወጣትነት ከብቃት መዓርግ ስለ ደረሱ በርካታ ተአምራትን ሠሩ:: በሰው ዘንድም ፍጹም ተወዳጅ ሆኑ::
- ስም አጠራራቸውም ሶርያን መላት:: በዘመኑ በአካባቢው አንድ ግዙፍ ዘንዶ ተነስቶ ሰውንም እንስሶችንም ፈጃቸው:: ሕዝቡም ሒደው በቅዱሳኑ ፊት አለቀሱ:: ያን ጊዜ ቅዱስ መክሲሞስ [ ትልቁ ] ክርታስ አውጥቶ "አንተ ዘንዶ ይህ ክርታስ ወደ አንተ ሲደርስ ከማደሪያህ ውጣ: ሙት: ወፎችም ይብሉህ" ሲል ጻፈበት::
- "ሒዳችሁ በበሩ ጣሉት" አላቸው:: አንድ ደፋር ሰው ተነስቶ ሰዎች ሁሉ እያዩት ወስዶ በዘንዶው መውጫ ላይ ጣለው:: በቅጽበትም ዘንዶው ወጥቶ ሞተ:: አሞሮችም ተሰብስበው በሉት:: ከዚህ ድንቅ ተአምር የተነሳ ሕዝቡ የቅዱሳኑን አምላክ አከበረ::
- ከዚህ በተረፈም በቅዱሳኑ ስም ታላላቅ ተአምራት ተደረጉ:: ርኩሳት መናፍስት ሁሉ ስማቸውን እየሰሙ ይሸሹ ነበርና:: ድውያን እነሱ በሌሉበት ስማቸው ሲጠራላቸው ይፈወሱ ነበር:: የአካባቢው ሰው ስማቸውን እየጠራ: በእነርሱም እየተማጸነ ከመከራው ሁሉ ይድን ነበርና ለሕዝበ ክርስቲያኑ ሞገስ ሆኑ::
- መርከበኞች ደግሞ ከማዕበል ለመዳን የቅዱሳኑን ስም በጀልባዎቻቸው ላይ ይጽፉ ነበር:: አንድ ቀን ግን የንጉሡ ለውንድዮስ ባለሟል ይህንን ጽሑፍ ተመልክቶ ስለ ጠረጠረ መርከበኛውን በንጉሡ ፊት አቀረበው::
ንጉሡም መርከበኛውን "የጻፍከው የማንን ስም ነው?" ቢለው "በሶርያ የሚገኙ ፪ ወንድማማች ቅዱሳን ስም ነው" አለው:: ልጆቹ እንደ ሆኑ ገምቶ በመርከበኛው መሪነት ንግሥቲቱንና ሴት ልጁን ላካቸው:: እነርሱ በሐዘን ተሰብረው ነበርና::
- ወደ ሶርያ ወርደው ባገኟቸው ጊዜም ከናፍቆትና ደስታ የተነሳ ታላቅ ጩኸትን እየጮሁ አለቀሱ:: "እንሒድ ወደ ሮም" ሲሏቸው ግን ቅዱሳኑ "የለም! እኛ የክርስቶስ ነን" ብለው እንቢ ስላሏቸው እያዘኑ ተመለሱ:: ንጉሡ ግን ይህንን ሲሰማ ደስ አለው:: "እነርሱ የዚህን ዓለም ኃላፊነት ተረድተዋል" ሲልም አወደሳቸው::
- በኋላ ግን "የሮሜ ሊቀ ዻዻሳት መሆን አለባችሁ" የሚል ነገር ሲሰማ ቅዱሳን መክሲሞስና ዱማቴዎስ ከሶርያ ወጥተው ወደ ግብጽ ወረዱ:: የከታላቁ ቅዱስ መቃርስ ዘንድ ደርሰውም ልጆቹ እንዲሆኑ ለመኑት::
" ልጆቼ ! በርሃ አይከብዳችሁም ? " ቢላቸው " ግዴለም ! " አሉት:: በዚያም ከተራራው ሥር በዓት ሠርቶላቸው ለ ፫ ዓመታት በአርምሞ ቆዩ:: አንድ ቀንም ቅዱሳኑ እየጸለዩ ከአፋቸው የወጣ የብርሃን ምሰሶ ከመንበረ ጸባኦት ሲደርስ አይቶ ታላቁ መቃርስ አደነቀ::
- በ፭ኛው መቶ ክ/ዘመን መጀመሪያ አካባቢም ጥር ፲፬ ቀን ታላቁ ቅዱስ መክሲሞስ ዐረፈ:: በዕለቱም የሰማይ ቅዱሳን ሁሉ ወርደው እየዘመሩ ወሰዱት:: ከ፫ ቀን በኋላ ደግሞ ቅዱስ ዱማቴዎስ ዐረፈ::
BY አብሰራ ገብርኤል ለማርያም
Share with your friend now:
tgoop.com/Enatachn_mareyam/16300