tgoop.com/Enatachn_mareyam/16251
Last Update:
🕊
[ † እንኳን ለጻድቃን ቅዱሳን አቡነ አረጋዊ እና አባ አርከሌድስ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። † ]
† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ! †
🕊 † አቡነ አረጋዊ ዘደብረ ዳሞ † 🕊
† ጻድቁ ገድላቸውን የፈጸሙት በኢትዮዽያ ቢሆንም ሃገረ ሙላዳቸው የጥንቱ የሮም ግዛት የሆነችው ታናሽ እስያ ናት:: አቡነ አረጋዊ ከዘጠኙ [ ተስዓቱ ] ቅዱሳን አንዱ ናቸው:: ዘጠኙ ቅዱሳን ተወልደው ያደጉት ምንም በአንድ የሮም ግዛት ሥር ቢሆንም መነሻ ቦታቸው ግን የተለያየ ነው::
ሁሉንም አንድ ያደረጋቸው መንፈስ ቅዱስ በኪነ ጥበቡ ነው:: በምክንያት ደረጃ እንግለጸው ከተባለ ደግሞ የአንድነታቸው ምሥጢር :-
፩. የቀናች ሃይማኖታቸው ተዋሕዶ:
፪. ዓላማ [ የእግዚአብሔር መንግስት ] እና
፫. ገዳማዊ ሕይወት ነው::
አቡነ አረጋዊን ጨምሮ ሁሉም ቅዱሳን ዘራቸው ከቤተ መንግስት ነው:: እነርሱ ግን ምድራዊውን ክብር ንቀው ሰማያዊውን ክብር ገንዘብ ማድረግን መርጠዋል:: አስቀድመው ቅዱሳት መጻሕፍትን ያጠኑት አበው በተለያየ ጊዜ እየመነኑ ከሮም ግዛት ወደ ግብጽ በርሃዎች ወርደዋል::
በምናኔ ቅድሚያውን አባ ዸንጠሌዎንና አቡነ አረጋዊ ይይዛሉ:: ዘመኑ የተዋሕዶ አማኞች የሚሰደዱበት ፭ኛው መቶ ክ/ዘመን ነበርና እምነትን ላለመለወጥ ዘጠኙ ቅዱሳን ስደትን መረጡ::
በወቅቱ ደግሞ ለስደት መጠለያ የምትሆንና ከኢትዮዽያ የተሻለች ሃገር አልነበረችም:: ስለዚህም በ፬፻፸ [470] ዎቹ ዓ/ም አልዓሜዳ በኢትዮዽያ ነግሦ ሳለ ቅዱሳኑ በአረጋዊ መሪነት መጡ::
ንጉሡም ሲጀመር የእግዚአብሔር እንግዳ ስለሆኑ: ሲቀጥል ደግሞ ቅድስናቸውን ተመልክቶ መልካም አቀባበልን አደረገላቸው:: ማረፊያ ትሆናቸውም ዘንድ አክሱም ውስጥ አንዲት ቦታን ወስኖ ሰጣቸው:: ይህች ቦታ ቤተ ቀጢን ትባላለች:: አቡነ አረጋዊና ፰ቱ ቅዱሳን ወደ ሃገራችን እንደገቡ የመጀመሪያ ሥራቸው ቋንቋን መማር ነበር::
ልሳነ ግዕዝን በወጉ ተምረው እዛው አክሱም አካባቢ ሥራቸውን አንድ አሉ:: በወቅቱ በአቡነ ሰላማ: በአብርሃ ወአጽብሐና በአቡነ ሙሴ ቀዳማዊ የተቀጣጠለው ክርስትና በተወሰነ መንገድ ተቀዛቅዞ ነበርና እነ አቡነ አረጋዊ እንደገና አቀጣጠሉት::
ሕዝቡን በራሱ ልሳን ለክርስትና ይነቃቃ ዘንድ ሰበኩት:: የካደውን እየመለሱ: የቀዘቀዘውን እያሟሟቁ ለዓመታት ወንጌልን ሰበኩ:: ቀጣዩ ሥራቸው ደግሞ መጻሕፍትን መተርጐም ሆነ::
ከሃገራቸው ያመጧቸውን ቅዱሳት መጻሕፍት ተከፋፍለው ወደ ግዕዝ ልሳን ተረጐሟቸው:: በዚህም ለሃገራችን ትልቁን ውለታ ዋሉ:: ይህ ሁሉ ሲሆን እነ አቡነ አረጋዊ የሚመገቡትም ሆነ የሚጸልዩት በማሕበር ነበር:: በመካከላቸውም ፍጹም ፍቅር ነበር:: ጸጋ እግዚአብሔር አልተለያቸውም::
የነ አቡነ አረጋዊ ቀጣዩ ተግባራቸው ደግሞ ገዳማዊ ሕይወትን ማስፋፋት ሆነ:: ይህንን ለማድረግ ግን የግድ መለያየት አስፈለጋቸው:: እያንዳንዱም መንፈስ ቅዱስ ወደ መራው ቦታ ሔደ::
- ዸንጠሌዎን በጾማዕት :
- ገሪማ በመደራ :
- ሊቃኖስ በቆናጽል :
- አባ ይምዓታ በገርዓልታ :
- ጽሕማ በጸድያ :
- ሌሎችም በሌላ ቦታ ገዳማትን መሠረቱ::
- አባ አረጋዊ ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ምርጫቸው ዳሞ [እዛው ትግራይ] ሆነ::
በሃገራችን ስም አጠራራቸው ከከበረ አባቶች አንዱ እኒህ ጻድቅ ናቸው:: ጻድቁ የተወለዱት በ፭ኛው መቶ ክ/ዘ አጋማሽ አካባቢ ሲሆን ወላጆቻቸው ንጉሥ ይስሐቅና ቅድስት እድና ይባላሉ:: የተለወለዱበት አካባቢም ሮም ነው::
ስማቸው ብዙ ዓይነት ነው:: ወላጆቻቸው " ዘሚካኤል" ሲሏቸው በበርሃ "ገብረ አምላክ" ተብለዋል:: በኢትዮዽያ ደግሞ "አረጋዊ" ይባላሉ:: አቡነ አረጋዊ ምንም የንጉሥ ልጅ ቢሆኑም በልጅነታቸው መጻሕፍትን ተምረው ነበርና ጠፍተው ገዳም ገቡ::
በዚያም በገዳመ ዳውናስ [ግብጽ] የታላቁ ቅዱስ ዻኩሚስ ደቀ መዝሙር ሆነው ከነ አባ ቴዎድሮስ ጋር ሥርዓተ መነኮሳትን ተምረዋል:: ከመነኮሱ ከዓመታት በሁዋላም ወደ ሃገራቸው ሮም ተመልሰው በማስተማር ፯ ያህል የቤተ መንግስት ሰዎችን ወደ ምናኔ ማርከዋል::
"የት ልሒድ" ብለው ሲያስቡም ቅዱስ መልአክ በክንፉ ጭኖ ወስዶ ኢትዮዽያን አሳያቸው:: ተመልሰውም ለ፰ ባልንጀሮቻቸው "ሃገርስ ባሳየሁዋችሁ! ሐዋርያ ሳያስተምራት በሕጉ በሥርዓቱ ጸንታ የምትኖር" ብለው ከ፰ቱ ጋር ወደ ኢትዮዽያ መጡ::
በዚህ ጊዜም እናታቸው ቅድስት እድናና ደቀ መዝሙራቸው አባ ማትያስ አብረው ነበሩ:: ወደ ሃገራችን የመጡ በ፬፻፸ [470]ዎቹ አካባቢ ሲሆን አልዓሜዳ በክብር ተቀብሏቸዋል:: በቤተ ቀጢን [አክሱም] ተቀምጠውም መጻሕፍትን እየተረጐሙ: ወንጌልን እየሰበኩ ቆይተዋል::
ለሥራ በተለያዩ ጊዜም አቡነ አረጋዊ በዓት ፍለጋ ብዙ ደክመዋል:: በመጨረሻ ግን ደብረ ዳሞን [ደብረ ሃሌ ሉያን] አይተው ወደዷት:: የሚወጡበት ቢያጡም ጅራቱ ፷ [60] ክንድ የሚያህል ዘንዶ ተሸክሞ ከላይ አድርሷቸዋል::
እንደ ወጡም "ሃሌ ሉያ ለአብ: ሃሌ ሉያ ለወልድ: ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ" ብለው ቢያመሰግኑ ከሰማይ ሕብስት ወርዶላቸው ተመግበዋል:: በዚህም ቦታዋ "ደብረ ሃሌ ሉያ" ተብላለች:: ጻድቁ ቦታውን ከገደሙ በሁዋላ ከተለያየ ቦታ መጥተው 6ሺ ያህል ሰዎች በእጃቸው መንኩሰዋል::
ምናኔን በማስፋፋታቸውና ሥርዓቱን በማስተማራቸውም "አቡሆሙ ለመነኮሳት ዘኢትዮዽያ - የኢትዮዽያ መነኮሳት አባት" ይባላሉ:: አቡነ አረጋዊ በሕይወታቸው ከተጋድሎ ባሻገር በወንጌል አገልግሎትና መጻሕፍትን በማዘጋጀትም ደክመዋል::
ቅዱስ ያሬድና አፄ ገብረ መስቀልም ወዳጆቻቸው ነበሩ:: በተራራው ግርጌ ያለችውን ኪዳነ ምሕረትን ለሴቶች ሲገድሟት ቀዳሚዋ መነኮስ እናታቸው ንግስት እድና ሁናለች::
ጻድቁ ንጹሕ ሕይወታቸውን ፈጽመው በተወለዱ በ99 ዓመታቸው በገዳሙ በስተ ምሥራቅ አካባቢ ተሰውረው ብሔረ ሕያዋን ገብተዋል:: ጌታም ፲፭ [15] ትውልድን የሚያስምር የምሕረት ቃል ኪዳን ሰጥቷቸዋል:: ዛሬ ጻድቁ የተወለዱበት ቀን ነው::
🕊 † አባ አርከሌድስ † 🕊
† በዚህ ስም የሚጠሩ ቅዱሳን በግብጽም በሃገራችንም አሉ:: ዋናውና በብዙ መጻሕፍት ዜናቸው የተጻፈላቸው ግን ዛሬ የምናከብራቸው ናቸው:: አባ አርከሌድስ የነበሩት በዘመነ ጻድቃን ሲሆን ሃገረ ሙላዳቸው ሮም ናት::
ወላጆቻቸው ክርስቲያን: በዚያውም ላይ ባለ ጠጐች ነበሩ:: አባታቸው ደግሞ መስፍነ ሃገር ነበር:: ቅዱሱን ወልደው: በሕግ በሥርዓት አሳድገዋል:: ለአካለ መጠን አባ አርከሌድስ ሲደርሱ ግን አባታቸው ሞተ::
መዋዕለ ሐዘናቸው ከተፈጸመ በሁዋላም እናት አባ አርከሌድስን ጠርታ:- "ልጄ! ሒድና የአባትህን ሹመት እጅ አድርግ" አለችው:: ለመንገድ የሚያስፈልገውን ሁሉ አሰናድታ: አገልጋዮችንና ብዙ ወርቅ (ለሿሚው አካል የሚሰጥ) ጨምራም ልጇን ሸኘች::
ቅዱስ አርከሌድስም ከእናታቸው ተለይተው በአገልጋዮች ተከበው ወደ መርከብ ገቡ:: በባሕር መካከል ሳሉ ግን ታላቅ ማዕበል ተነስቶ መርከቡን በታተነው:: በመርከቡ የነበረው ሰው ሁሉ ሲያልቅ አባ አርከሌድስ ግን በስባሪ ላይ ተንጠልጥለው ተረፉ::
BY አብሰራ ገብርኤል ለማርያም
Share with your friend now:
tgoop.com/Enatachn_mareyam/16251