tgoop.com/Dreyob/6802
Last Update:
የሃሳብ፣ የሰውና የቦታ ተጽእኖ !
“ያንንኑ ተግባር እየደጋገምክ የተለየን ውጤት አትጠብቅ”
ባለፈው አመት ውጤታቸውን ያልወደድናቸውና የተጸጸትንባቸው ሁኔታዎች ካሉ በዚህ አመት ሁኔታውን ለመለወጥ እንደምንፈልግ ጥርጥር የለውም፡፡ ሁኔታው እንዲለወጥ ደግሞ አደራረጋችንን መለወጥ የግድ ነው፡፡ አደራረግን መለወጥ ማለት ለጸጸት የዳረገንን ተግባርና እንከተለው የነበረውን መንገድ ለማቆም መወሰን ማለት ነው፡፡
ያንኑ ተግባር እያደረግን የተለየ ውጤት ማግኘት የማይቻል ስለሆነ ማለት ነው፡፡ ያንኑ ሃሳብም እያሰብን የተለየ ፍሬ ማፍራትም የማይሆን ነገር ነው፡፡
አደራረግን ለመለወጥ፣ ማረፍንና መለስ ብሎ ሕይወትን ማየትን የሚጠይቅ ጉዳይ ነው፡፡ አደራረግን በመለወጥ አላስፈላጊ ውጤትና የጸጸት ስሜትን ያመጣብንን ሁኔታ ለመቀየር ከፈለግን የሚከተሉትን ደረጃዎች መጠቀም እንችላል፡-
1. አስተሳሰብን መለወጥ
“አንድ ነገር የሚፈጠረው ሁለት ጊዜ ነው - በመጀመሪያ በሃሳብ ውስጥ፣ ከዚያም በገሃዱ አለም”፡፡
የተዛባ ሕይወት መነሻው የተዛባ አስተሳሰብ ነው፡፡ ስለዚህ በሕይወታችን ያየናቸው ጤና ቢስ ነገሮች በሙሉ በመጀመሪያ የተፈጠሩት ሃሳባችን ውስጥ ነው፡፡ ለዚህ ሁኔታ የሚዳርገንን አስተሳሰብ ለማግኘት፣ “ለዚህ ስህተት የሚያነሳሳኝ የማስተናግደው ሃሳብ ምንድን ነው?” የሚለውን ጥያቄ መመለስ የግድ ነው፡፡
2. አጉል ወዳጅነትን መለወጥ
“የአምስቱ የቅርብ ወዳጆህ ጭማቂ ነህ”፡፡
በክፉውም ሆነ በመልካሙ ጎን በሰዎች ላይ ተጽእኖ ከማምጣትና በሰዎች ተጽእኖ ስር ከመውደቅ የሕይወት ሂደት አናመልጥም፡፡ ባለፈው አመት እንድንጸጸት ላደረገን ተግባርና ሁኔታ አንዱ ተጠያቂ ምናልባት የሰዎች አጉል ተጽእኖ ነው፡፡ ያንን ለማግኘት፣ “ለዚህ ስህተት የሚያነሳሳኝ የማስተናግደው ሰው ማን ነው?” የሚለውን ጥያቄ መመለስ የግድ ነው፡፡ ከዚም ምን አይነት እርምጃ መውሰድ እንዳለብን አጥብቀን እናስብበት፡፡
3. የምንሄድባቸውን ስፍራዎች እንለውጥ
“ሰው የሚመስለው አካባቢውን ነው”፡፡
የምንውልበት አካባቢ በተግባራችንና በውሳኔያችን ላይ ትልቅ ጫና አለው፡፡ ባለፈው አመት ለተጸጸትንባቸው ስህተቶች መጠቀሚያ የሚሆነውን ስፍራ ለማግኘት፣ “ለዚህ ስህተት የሚያነሳሳኝ የምስተናገድበት ቦታ የት ነው?” የሚለውን ጥያቄ መመለስ የግድ ነው፡፡ አንዳንድ ደካማ ጎኖቻችን ጉልበት የሚያገኙበት ስፍራ አላቸው፡፡ እነዚህን ስፍራዎች በመለየት ትክክለኛውንና ቁርጠኛ ውሳኔ በማስተላለፍ ወደፊት እንቀጥል፡፡
https://www.tgoop.com/Dreyob
https://m.youtube.com/user/naeleyob623
https://www.facebook.com/Dr-Eyob-Mamo-1\050816404958639/
BY Dr. Eyob Mamo

Share with your friend now:
tgoop.com/Dreyob/6802