tgoop.com/Addis_Tv/3834
Last Update:
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም በፈቃዳቸው ከኃላፊነታቸው ለቀቁ።
አየር መንገዱ ባወጣው መግለጫ አቶ ተወልደ በፈቃዳቸው ከኃላፊነት መልቀቃቸውን አስታውቋል።
አየር መንገዱ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፥ አቶ ተወልደ ላለፉት ስድስት ወራት ህክምናቸውን በአሜሪካ ሲከታተሉ መቆየታቸውን አስታውሷል፡፡
አቶ ተወልደ ገብረማርያም በጤና እክል ምክንያት የአየር መንገዱ ዋና አስፈጻሚ ሆነው መቀጠል እንደማይችሉ በመግለጽ ለስራ አመራር ቦርዱ የስራ መልቀቂያ ጥያቄ ማቅረባቸው ተገልጿል፡፡
በዚህ መሰረት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የስራ አመራር ቦርድ በዛሬው ዕለት ባካሄደው ስብሰባው አቶ ተወልደ ያቀረቡትን የስራ መልቀቂያ ጥያቄ መቀበሉን አስታውቋል፡፡
የስራ አመራር ቦርዱ በአቶ ተወልደ ገብረማርያም ምትክ ለአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጸሚ በቅርቡ እንደሚመድብም ነው የተገለፀው።
አየር መንገዱ በመግለጫው አቶ ተወልደ ከአንድ አስርት ዓመታት በላይ ተቋሙን በመሩበት ወቅት ከፍተኛ ስኬት ያስመዘገቡ መሆናቸውን አመልክቷል።
በእርሳቸው አመራር አየር መንገዱ በሁሉም መለከያ የተለየ ስኬት ማስመዝገቡን በመጠቆም ዓመታዊ ገቢው ከ1 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ተነስቶ አሁን ላይ ከ4 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር መብለጡን ጠቁሟል።
33 የነበሩት የአውሮፕላን ቁጥሮችም ወደ 130 ማደጋቸውን እና በዓመት የሚያስተናግደው የመንገደኞች ቁጥር ከ3 ሚሊየን ወደ 12 ሚሊየን ከፍ ማለቱን አስታውቋል።
በአጠቃላይ በእርሳቸው አመራር አየር መንገዱ በአራት እጥፍ አድጓል ያለው መግለጫው፥ 700 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ዋጋ ያወጡ ቁልፍ መሰረተ ልማቶችን አየር መንገዱ የገነባው በእርሳቸው አመራር መሆኑን በመግለፅም፥ በአፍሪካ ትልቅ የሚባል ሆቴል፣ የካርጎ ተርሚናል፣ የአቭዬሽን አካዳሚ እና የበረራ ሲሙሌተሮች መገንባታቸውን ለአብነት ጠቅሷል።
መግለጫው አክሎም የስራ አመራር ቦርዱ፣ ከፍተኛ አመራሮች እና ሰራተኞች በአጠቃላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቤተሰብ ለዚህ አስተዋፅኦዋቸው ከፍ ያለ ምስጋና እንዳላቸው በመግለፅ መልካም ጤናን ተመኝቷል።
@Addis_Tv
BY አዲስ ቲቪ Adiss Tv AMN

Share with your friend now:
tgoop.com/Addis_Tv/3834