Telegram Web
".... ዐይኖችን በሚፈጥር ፊት ምራቃቸውን ተፉበት። ዳግመኛም ፊቱን በጥፊ መቱት። ኪሩቤል ፊቱን ከማየት የተነሣ በእሳት አክናፍ የሚሠወሩት ያልበደላቸውን እሱን አይሁድ ፊቱን ጸፉት፤ ፊቱ እንደ መንፈስ ቅዱስ፣ እንደ አባቱ ሲሆን በሥጋው ፊቱን ጸፉት፤ ከፊቱ ግርማ የተነሣ ፍጥረቱ ሁሉ የሚርዱለት፣ የሚንቀጠቀጡለት የፈጣሪያቸውን ፊቱን ጸፉት። መዠመሪያ በመመታቱና የሾኽ አክሊል በመሸዳጀቱ ራሱ የቆሰለ ከመሆኑ በላይ የያዘውን በትር ከእጁ ተቀብለው ራሱን መቱት።
ነገር ግን የሾኽ አክሊልን በመቀዳጀቱ በምድራችን ላይ የበቀሉትን አሜከላና እሾኽ እርግማንን አጠፋልን። ራሱንም በዘንግ በመመታቱ የታላቁን እባብ ሰባቱን እራሶቹን ዐሥሩ ቀንዶቹን አጠፋልን።"

         የኅሙስ ድርሳነ ማኅየዊ
❖ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ❖

"አዳምን የፈጠሩ እጆች በመስቀል ቀኖት ተቸነከሩ ፡ ወዮ ፤ በገነት የተመላለሱ እግሮች በመስቀል ቀኖት ተቸነከሩ ፡ ወዮ ፤ በአዳም ፊት የህይወት መንፈስን እፍ ያለ አፍ ከሃሞት ጋራ የተቀላቀለ የኮመጠጠ መፃፃን ጠጣ ፡ ወዮ ፤ የወልድን መከራውን የሚናገር ምን አፍ ነው? ምን ከንፈር ነው? ምን አንደበት ነው? የፍቅር ጌታ ሕማማት በተነገረ ጊዜ ልብ ይለያል ፡ ህሊናም ይመታል ፡ ነፍስም ትንቀጠቀጣለች ፡ ስጋም ይደክማል፡፡ የማይሞተው ሞተ ፡ ሞትን ይሽረው ዘንድ ሞተ ፡ ሙታንን ያድናቸው ዘንድ ሞተ ፤ የምትወዱት ሰወች ፈፅሞ አልቅሱለት ፤ ወየው ወየው ወየው አማኑኤል አምላካችን፡፡ ወየው ወየው ወየው መድሃኒታችን ኢየሱስ ፤ ወየው ወየው ወየው ንጉሳችን ክርስቶስ ፤ ወየው ወየው ወየው ፃድቃን ከእንጨት አወረዱት ስጋውንም ለመገነዝ ከርቤ የሚባል የጣፈጠ ሽቱንና ንፁህ በፍታን አመጡ፡፡ ሞተም ተቀበረም ፤ ሙስና ሳይኖርበት ከሙታን ተለይቶ ፈፅሞ ተነሳ ፤ ከሃጢአት ቀንበርም ነፃ አደረገን ፤ በዚያች ስጋ በመለኮት ሃይል ወደ ሰማይ ወደ ቀደመ አኗኗሩ አረገ፡፡"
#በመቃብር_አደረ

"ዳግመኛም ይህ ሥጋ ከመለኮቱ ሳይለይ በመቃብር አደረ ነፍሱም ከመለኮት ሳትለይ በገሀነም ተግዘው ለነበሩ ነፍሳት ድኅነትን ታበስር ዘንድ፤ ነፃም ታደርጋቸው ዘንድ ወደ ሲኦል ወረደች።"

ሃይማኖተ አበው ዘአትናቴዎስ
"ድንግል ሆይ በኃጢአት ፍትወት የተፀነስሽ አይደለም፤ በሕግ በሆነ ሩካቤ ከሐና ከኢያቄም ተወለድሽ እንጂ።"
አባ ሕርያቆስ
እንኳን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም በዓለ ልደት አደረሰን 🙏🙏🙏
"ሰይጣንም የአንቺን ምስጋና ወሬ ሲሰማ በብስጭት ጥርሱን ያፏጫል፤ የምስጋናሽ ወሬ በእርሱ ዘንድ መራጃ ነውና እራሱን ይቆርጠዋል፡፡ ከስምሽ አጠራር የተነሣ መብረቅ በኃይል ሲጮህ እንደ ሰማ ሁሉ ይደነግጣል፡፡ አንቺ ከተወለድሽ ጀምሮ ፈጽሞ ዕረፍት አላገኘም፡፡ በአንቺ ታመመ በልጅሽም ተጨነቀ በአንድ ልጅሽ መስቀል ሥቃይ አገኘው፡፡ ከፍጡራን ወገኖች ሁሉ ይልቅ ሰይጣል አንቺን ይጠላል፡፡"

#አባ_ጊዮርጊስ_ዘጋስጫ
ብሒላተ አበው ወእመት ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ
Photo
[•• አምስቱ ትንሣኤዎች••]
      
‹‹...በፊተኛው ትንሣኤ ዕድል ያለው ብፁዕና ቅዱስ ነው ሁለተኛው ሞት በእርሱ ላይ ሥልጣን የለውም፡፡›› ራእ ፳ ፥ ፮

ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት «ትንሣኤን» በየመልኩ፣ በየዐይነቱ ሲያመሠጥሩት በአምስት ዓይነት ትርጉም ያስቀምጡታል፡፡

ይኸውም ትንሣኤ ኅሊና፣ ትንሣኤ ልቡና፣ ትንሣኤ ሙታን፣ ትንሣኤ ክርስቶስና ትንሣኤ ዘጉባኤ በሚል በአምስት መንገድ ይከፈላል።

፩ኛ. ትንሣኤ ኅሊና ነው
ይህ ትንሣኤ ኅሊና ተዘክሮተ እግዚአብሔር (እግዚአብሔርን ማሰብ) ማለት ነው። ሙሴ በኦሪቱ ‹‹እመኒ እንዘ ተሐውር ወእመኒ እንዘ ትትነሣእ ኢትርሣእ ተዘክሮተ እግዚአብሔር፡፡ ስትሄድም ስትነሣም እግዚአብሔርን ማሰብ አትርሣ›› ብሎ ሊቀ ነቢያት ሙሴ እንደተናገረው።

፪ኛ. ትንሣኤ ልቡና ነው፤
ትንሣኤ ልቡና ደግሞ ቃለ እግዚአብሔርን በመስማትና በንስሐ እየታደሱ በሕይወት መኖር ማለት ነው:: ይኸውም ሰው ሁለት ጊዜ ይሞታል፤ ሁለት ጊዜ ይነሣል፤

የሰው ልጅ የመጀመሪያው ሞቱ ኀጢአት መሥራቱ ከእግዚአብሔር መለየቱ ነው፤ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በሥጋ ፍትወት በምድራዊ ቅንጦት የሚቀማጠሉትን ሲናገር ‹‹ቅምጥሊቱ ግን በሕይወቷ ሳለ የሞተች ናት›› ፩ኛ ጢሞ ፭ ÷፲ ፯ ሲል በኀጢአት መኖር ትልቁ ሞት እንደኾነ ነግሮናል፣

ሁለተኛው በሥጋ መሞቱ ነው:: ስለዚህ ሰው ሁለት ጊዜ እንደሚሞት ሁለት ጊዜ ይነሣል፤

የሰው ልጅ የመጀመሪያ ትንሣኤው እንዴትና ምን እንደሆነ ቅዱስ ዮሐንስ በራእዩ እንዲህ ሲል ነግሮናል፤ ‹‹ይህ የፊተኛው ትንሣኤ ነው፤ በፊተኛው ትንሣኤ ዕድል ያለው ብፁዕና ቅዱስ ነው
ሁለተኛው ሞት በእርሱ ላይ ሥልጣን የለውም፡፡›› ራእ ፳ ፥ ፮  በማለት ንስሐ ገብቶ ከእግዚአብሔር ታርቆ ትንሣኤ ልቡናን ገንዘብ ያደረገ ሰው ሞተ ሥጋንና ሞተ ነፍስ ድል ነሥቶ እንደሚኖር ነግሮናል፡፡ 

ለትንሣኤ ልቡና ትልቅ ምክር የሚሆነን በሉቃስ ወንጌል የተመዘገበው ታሪክ ነው፤  ‹‹ይህ ልጄ ሞቶ ነበረና ደግሞም ሕያው ሆኗል፤ ጠፍቶም ነበር ተገኝቷል›› በማለት በኀጢአት መኖር እንደ መሞት ከኀጢአት መመለስ እንደ ትንሣኤ መቆጠሩን አስረድቶናል። ሉቃ ፲፭ ፥ ፳፬ ማንኛውም ሰው ከቤተ ክርስቲያን ከመንፈሳዊ ሕይወት ከወጣ እንደ ሞተ ነው የሚቆጠረው፡፡

፫ኛ. ትንሣኤ ሙታን ነው
ይህ ደግሞ ለጊዜው የሙታን በሥጋ (በተአምራት) መነሣት ሲሆን፤ ነገር ግን ድጋሚ ሞት ይከተለዋል:: ይኸውም በብሉይ ኪዳን ነቢዩ ኤልያስ አንድ ሙት፣ ነቢዩ ኤልሳዕ ሁለት ሙት አስነሥተዋል፤ በሐዲስ ኪዳን ጌታችን የዐራት ቀን ሬሳ አልአዛርን፣ የዕለት ሬሳ ወልደ መበለትን፣ ወለተ ኢያኤሮስን ከሞት አስነሥቷል፤ ይህ ‹‹ትንሣኤ ሙታን›› ይባላል፡፡

፬ኛ. ትንሣኤ ክርስቶስ ነው
ትንሣኤ ክርስቶስ እንደሚታወቀው ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገዛ ሥልጣኑ ሞትን ድል አድርጎ መነሣቱን የሚገልጥ ነው:: ይህ ትንሣኤ የትንሣኤው ሁሉ በኵር ተብሎ ይጠራል᎓᎓ ትንሣኤው ከፍጡራን ትንሣኤ የተለየና ብቸኛ ነው:: 

፭ኛ. ትንሣኤ ዘጉባኤ ነው
ትንሣኤ ዘጉባኤ ከዓለም ኅልፈት በኋላ ሰው ዅሉ እንደየሥራው ለጽድቅና ለኩነኔ በአንድነት የሚነሣው የዘለዓለም ትንሣኤ ነው።

በሕብረት፣ በነገድ፣ በጉባኤ ለዓለም ሕዝብ ሁሉ የሚደረግ ትንሣኤ በመሆኑ ትንሣኤ ዘጉባኤ ተብሏል። ጌታ በወንጌሉ ስለትነሣኤ ዘጉባኤ ሲናገር «በመቃብር ያሉት ሁሉ ድምፁን
የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ፤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ።» ዮሐ ፭ ፥ ፳፱ ሲል በትንሣኤ ዘጉባኤ ከሚደረጉ ተአምራት አንጻር ዛሬ የሚደረጉ ተአምራት ምንም እንዳልሆኑ አስተምሯል። ትንሣኤ ክርስቶስ ለትንሣኤ ሙታን ምስክር ለትንሣኤ ዘጉባኤ በኵር  ነው
   ©መ/ር ሚኪያስ ዳንኤል
ክርስቶስ ተነሥቷል(Christ Risen) በሚለው ቃል ውስጥ ያለው መንፈሳዊ ኀይል።

በአባ ዮሐንስ ገባሬ መንክራት (St. Jonh Maximivotch) የተደረገው ተአምር።

አባ ዮሐንስ ገባሬ መንክራት በአንድ ወቅት የብርሃን ሳምንት ተብሎ በሚታወቅበት ሳምንት አንድ የታመመ ኦርቶዶክዊ ምዕመንን ለመጠየቅ ጉዞውን ወደ አንድ የአይሁዳውያን ሆስፒታል ያደርጋሉ።

አባ ዮሐንስ በሆስፒታሉ በአንደኛው ዋርድ ፊትለፊት ሲያልፍ ድንገት ቆመና በመጋረጃ በተሸፈነው ክፍል ውስጥ አንዲት አይሁዳዊት አሮጊት ሕይወቷ አልፏል በመባሉ ሸፋፍነዋት አልጋ ላይ እንዳስተኟት ይረዳል።

አባ ዮሐንስ ገባሬ መንክራት ድንገት ከተጋረደው ክፍል ፊትለፊት ቆመና ቅዱስ መስቀሉ አውጥቶ ድምጹ ከፍ አድርጎ ጮኸና "ክርስቶስ ተነሥቷል" እያለ በመስቀል ምልክት እያማተበ ተናገረ፣ ድንገት ይኸንን በሚያደርግበት ወቅት ሞተች የተባለችዋ እናት አእምሮዋ ተመለሰላትና ቃል አውጥታ ውሃ ስጡኝ ብላ ጠየቀች።

አባ ዮሐንስም አንዷን ነርስ ጠራት እንዲህ አላት ታማሚዋ ውሃ እየፈለገች ነው ብሎ ሲነግራት ይኸንን የሰሙ የሆስፒታሉ ሠራተኞችም አስቀድማ አርፋለች ተብላ የነበረችው ታማሚዋ ባሳየችው አስገራሚ ለውጥ በጣም ተደነቁ ከዚያ በኋላ ታማሚዋም በተደረገላት አስደናቂ ተአምር ተሽሏት አገግማ ከሆስፒታሉ ወጥታ ወደ ቤቷ ሔደች።

አባ ዮሐንስም በክርስቶስ የትንሣኤው ኃይል በማያምኑት መካከል አስደናቂውን ተአምር አደረጉ።

አቤቱ ሆይ የትንሣኤህ ኃይል ይገለጥ ሰይጣን ከነ ሠራዊቱ ይሸነፍ፣ ሞትም ከነ መውጊያው ይወገድ፣ ሲኦልም ከነ ድል መንሣቷ ትሻር፣ ኃጢአት እና አለማመን ከእኛ ይራ፣ ሕይወታችን የተቀደሰች ትሁን ዙሪያችን በትንሣኤው ኃይል በትንሣኤው ብርሃን የታጠረ ይሁን።

ክርስቶስ ተነሥቷል
በእውነት እርሱ ተነሥቷል።
በአንዳች ነገር መጠን ባለፈ ሁኔታ እየተጨነቅንና እየተበሳጨን ከሆነ ፈቃድህ ይሁን ብለን ብንጸልይም እንደ ጌታ ፈቃድ ያለመኖራችንና ለእግዚአብሔር ፈቃድ ሙሉ በሙሉ እጅ እንዳልሰጠን ማሳያ ነው።።
እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሚኖር ሰው ስለ ምንም ነገር አይጨነቅም።ፈቃድህ ይሁን ብሎ እራሱን እና ፍላጎቱን ለእግዚአብሔር አሳልፎ ስለሚሰጥ የሚፈልገውን ባያገኝ እንኳን በትዕግስት ጸንቶ ጌታን ያመሰግናል።
ለእግዚአብሔር ፈቃድ የተገዛች የክርስቲያን ነፍስ በምንም ነገር አትታወክም አትፈራም አትጨነቅምም።ትናንትን ያሻገራት ዛሬን የሚጠብቃት ነገን ከበረከት ጋር የሚያሳያት ጌታ እንዳላት ታምናለችና።አሜን

~ ቅዱስ ሰሎዎስ ዘአቶናዊ
በእውነት የተመሰገኑት ተአምራትን ማድረግና ቅዱሳን መላእክትን ማየት የቻሉት ብቻ ሰዎች ሳይሆኑ የተመሰገኑት የራሳቸውን በደል ማየት የቻሉት ሰዎችም ናቸው።

ቅዱስ አትናቴዎስ
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ "ክርስቶስ ካልነሣማ እምነታችን ከንቱ ናት" 1 ቆሮ.15፦17) እንዳለው የክርስቶስ ትንሣኤ እርሱ የሚጠበቀው መሲህና የእግዚአብሔር ልጅ ለመኾኑ ፍጹም ማረጋገጫ ነው። ክርስቶስ ከሞት በመነሣቱ ምክንያት ነፍሳችን የኢመዋቲነት(የሕያውነት) እና የዘለዓለማዊነት ተስፋን ትቀበላለችና።
ጎርጎርዮስ ፓላማስ(St. Gregory Palamas)
"ከዓወሎ ነፋስ የተነሣ ምዕመናንን የምታሻግር የመድኃኒት ድልድይ, የድኅነት መርክብ ሆይ ክኃጢአት ማዕበል ሞገድ አሻግሪኝ, መርክብ ሰውነቴን እንዳያነዋውፀው። "
አባ ጊዮርጊስ ዘጋዝጫ
ብሒላተ አበው ወእመት ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ
Photo
መንፈሳዊ ሕይወትን

ገና ስትጀምረው ለፍጹምነት ጥቂት የቀረህ ያህል ይሰማሃል። አንተ ጋር ያለው ደስታ እና ሰላም ሌሎች ጋር የሌለ ይመስልሃል። በዚህች ሁከት በሞላባት ዓለም አንተ ብቻ ክርስቶስን እንዳገኘኸው ታስባለህ። የቀረው ሕዝበ አዳም እንዲሁ በከንቱ ሲርመሰመስ የሚውል ባካና ሆኖ ይታይሃል። ታዝንለታለህ፣ አይይይ ይህ ኃጢአተኛ ሕዝብ ምን ይሻለዋል? ትላለህ።

የእውነተኛ መንፈሳዊ እድገት መገለጫ ግን ይህ አይደለም። ሰው ወደ እግዚአብሔር እየቀረበ ሲመጣ ከሌላው ሰው ይልቅ የራሱ ጉድለት ይታየዋል። መንፈሳዊነት የሚገልጥልህ ሰዎችን ተመልክተህ የምትፈርድበትን ውጫዊ ዓይንህን ሳይሆን ራስህን አይተህ የምትወቅስበት የውስጥ ዓይንህን ነው። መንፈሳዊ ሕይወትህ ሲጎመራ "አይ ሰው" ሳይሆን "አይ እኔ!" ያሰኝሃል። "ሰው የበለጠ ወደ እግዚአብሔር ሲቀርብ ይበልጥ ኃጢአተኛ መሆኑ እየታየው ይመጣል። ነቢዩ ኢሳይያስ እግዚአብሔርን ካየ በኋላ ከንፈሮቼ የረከሱብኝና የጠፋሁ ሰው ነኝ እንዳለ።"

ከብቃት ደርሰህ መላእክት ሲወጡና ሲወርዱ ቢታዩህ እንኳን ሁሉ እንዳንተ ስለሚመስልህ እንደ ዮሐንስ ሐጺር "ሚካኤል ይበልጣል ወይስ ገብርኤል?" እያልህ ከአጠገብህ የቆመውን ትጠይቃለህ እንጂ "አይይ አንተ እንኳን ገና አልበቃህም። ብዙ ይቀርሃል" ብለህ ወዳጅህን አታናንቅም። ይልቅ "ለእኔ ብቻ ገልጦ ለሌላው እንዲሰውር የሚያደርገው ምንም ቁም ነገር የለኝም" በማለት ከወንድምህ የተሻልህ እንዳልሆንክ በፍጹም ልብህ ታምናለህ።

ለመንፈሳዊ ሕይወት አዲስ ስትሆን ገና ጥቂት ጸልየህ፣ ጥቂት ጾመህ፣ ጥቂት መጽውተህ ሳለ ግን ሩጫህን ወደ መጨረሱ የተቃረብህ ይመስልሃል። ጉዞህን በግማሽ እርምጃ ከመጀመርህ ከፍጻሜው ላይ የደረስህ ያህል ይሰማሃል። "እኔን ምሰሉ" ማለት ያምርሃል። ነገር ግን መንፈሳዊ ሕይወት የቱንም ያህል ብትሮጥበት ሁል ጊዜ እንደ ጀማሪ የሚያደርግ ረጅም ጎዳና ነው። ሰማንያ ዓመት በገዳም ሲጋደል የነበረው አባ ሲሶይ ነፍሱ ከሥጋው ልትለይ በቀረበች ጊዜ ብዙ መነኮሳት በአልጋው ዙሪያ ከበውት ሳለ ቅዱሱ "አምላኬ ሆይ፣ እባክህ ለንስሐ የሚሆን ጥቂት ጊዜን ስጠኝ?" እያለ በልቅሶ ሲማጸን ሰሙት። በዚህ የተገረሙት መነኮሳቱ አባ ሲሶይን "አባታችን አንተ እድሜ ልክህን በንስሐ የኖርህ መምህረ ንስሐ ሆነህ ሳለ እንዴት አሁን ጥቂት የንስሐ ጊዜን ትለምናለህ?" ቢሉት፣ ቅዱሱም "ልጆቼ ይህን መንፈሳዊ ጥበብ (ንስሐን) ገና አሁን መጀመሬ ነው" አላቸው።

ጌታ ሆይ መንፈሳዊ ሕይወት እኖር ዘንድ አስጀምረኝ፤ ገና ጀማሪ ሳለሁ ደርሻለሁ ከማለትም ሰውረኝ። እንድቆም አትፍቀድልኝ፤ ወደ አንተ ሳበኝ፣ አሳድገኝ። ብለን ሁልጊዜ መጸለይ ይገባናል።
እግዚአብሔር አምላክ ለንስሐ ሞት ያብቃን። ንስሐ የምንገባበት ጥቂት የንስሐ ዕድሜ ለሁላችንም ያድለን።
2024/05/19 23:37:50
Back to Top
HTML Embed Code:


Fatal error: Uncaught Error: Call to undefined function pop() in /var/www/tgoop/chat.php:243 Stack trace: #0 /var/www/tgoop/route.php(43): include_once() #1 {main} thrown in /var/www/tgoop/chat.php on line 243