Telegram Web
#ንስሐ ሰዎች ስለ ኃጢያታቸው ተጸጽተው ከ #እግዚአብሔር ጋር እንዳይታረቁ በብርቱ በሚጥረው ሰይጣን ላይ የተገኘ ታላቅ ድል ነው ምክንያቱም በፈቃደ ሰይጣን በግብረ ኃጢያት የተያዙ ሰዎች ከዲያብሎስ ግዞት ነፃ የሚወጡት በ #ንስሐ ነውና። ለብዙ ዘመናት በተሠራ ኃጢያት የተገነባ የበደል ሕንፃ በአንዲት ሰዓት በ #ንስሐ እንዳልነበረ ሆኖ ይፈርሳል። ስለዚህም #ንስሐ የበደለውን እንዳልበደለ ኃጡኡን ጻድቅ፤ ዘማዊውን ድንግል ታደርጋለች ሲል ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ተናግሯል።

#ይቀጥላል........
አንድ ወንድም #አባ_ጥጦስን "እንዴት ልቤን መጠበቅ እችላለሁ" ሲል ጠየቀው። አባ ጥጦስም "አፋችንና ሆዳችን ክፍት ከሆነ እንዴት ልባችንን መጠበቅ ይቻለናል"? ሲል መለሰለት።

#አባ_ጥጦስ
#ጥቅምት_12

#አንድ_አምላክ_በሆነ_በአብ_በወልድ_በመንፈስ_ቅዱስ ስም
ጥቅምት አስራ ሁለት በዚህች ዕለት ሊቀ መላእክት #ቅዱስ_ሚካኤል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ #ቅዱስ_ዳዊትን በሳኦል ፈንታ እንዲሾመው ለሳሙኤል የነገረበት እና በጎልያድ ላይ ኃይልን የሰጠበት እንዲሁም የወንጌላዊው #ቅዱስ_ማቴዎስ እና #የቅዱስ_ድሜጥሮስ የዕረፍት ቀን ነው፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ዳዊት_ልበ_አምላክ (የነገሠበት)

ጥቅምት ዐሥራ ሁለት በዚች ዕለት የመላእክት አለቃ የከበረ መልአክ የቅዱስ ሚካኤል የበዓሉ መታሰቢያ ነው። በዚችም ቀን ወደ ነቢይ ሳሙኤል #እግዚአብሔር ልኮታልና የዳዊት አባት ወደሆነ በቤተ ልሔም ወደሚኖር ወደ እሴይ ቤት ይሔድ ዘንድ በቂስ ልጅ በሳኦልም ፈንታ ለእስራኤል ልጆች እንዲነግሥ ልጁ ዳዊትን ይቀባው ዘንድ አዘዘው።

ቅዱስ ሳሙኤልም ወደ እሴይ ቤት ሔዶ ልጆችህን ሁሉንም አቅርብልኝ ብለው እሴይም ከዳዊት በቀር ሁሉንም አቀረባቸው እርሱ በእርሻ ውስጥ በጎችን ይጠብቅ ነበርና።

ቅዱስ ሳሙኤልም የመንግሥት ቅባት ያለበትን ብልቃጥ በራሳቸው ላይ ከፍ ከፍ በአደረገ ጊዜ #እግዚአብሔር አልመረጣቸውም ። ሳሙኤልም እሴይን ልጆችህ እነዚህ ብቻ ናቸውን አለው ዕሴይም በጎች የሚጠብቅ አንድ ትንሽ ልጅ አለ አለው።

ቅዱስ ሳሙኤልም ደግሞ ዕሴይን እሱ ሳይመጣ ምሳ አልበላምና ልከህ አስመጣው አለው። እሱም ልኮ አስመጣው መልኩም ቀይ ዐይኖቹም የተዋቡ አርአያውም ያማረ ነው #እግዚአብሔርም ሳሙኤልን ይህ ይበልጣቸዋልና ተነሥተህ ቅባው አለው። በዚያንም ጊዜ ሳሙኤል የመንግሥት ቅባት ያለበትን ቀንድ አምጥቶ በወንድሞቹ መካከል ቀባው ከዚያችም ቀን ጀምሮ ለሁል ጊዜ የ #እግዚአብሔር መንፈስ በዳዊት ላይ አደረበት በእስራኤል ልጆችም ላይ ነገሠ።

ደግሞ ሁለተኛ በዚች ቀን #እግዚአብሔር የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልን ወደ ዳዊት ላከው ረዓይታይ ጎልያድን እስኪገድለውና የእስራኤልን ልጆች እስከሚያድናቸው ረድቶ ኃይልን ሰጠው።

ስለዚህም የበዓሉን መታሰቢያ በየወሩ በዐሥራ ሁለት ቀን እናደርግ ዘንድ የቤተክርስቲያን መምህራን አዘዙን።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በመላእክት አለቃ በቅዱስ ሚካኤል አማላጅነት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ሐዋርያው_ቅዱስ_ማቴዎስ

#የጌታችን_አምላካችንና_መድኀኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስን አምላካዊ ትእዛዝ ተቀብለው ወንጌልን ለመላው ዓለም በማብሠር መምለክያነ ጣዖትን ወደ አሚነ #እግዚአብሔር፣ አሕዛብን ወደ ክርስትና ከመለሱ ቅዱሳን ሐዋርያት መካከል ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ አንደኛው ነው፡፡ ቅዱስ ማቴዎስ አገሩ ናዝሬት፣ የዘር ሐረጉም ከይሳኮር ነገድ ሲኾን አባቱ እልፍዮስ (ዲቁ)፣ እናቱ ደግሞ ካሩትያስ ይባላሉ፡፡

ለደቀ መዝሙርነት ከመመረጡ በፊት ‹ሌዊ› ይባል ነበረ፤ ከተጠራ በኋላ ግን ‹ማቴዎስ› ተብሏል፡፡ ‹ማቴዎስ› ማለት በዕብራይስጥ ቋንቋ ‹ጸጋ #እግዚአብሔር (የ #እግዚአብሔር ስጦታ)› ማለት ሲኾን ስሙን ያወጣለትም #ጌታችን_መድኀኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ነው፡፡ ለወንጌል አገልግሎት የተጠራውም በቅፍርናሆም ከተማ ከቀራጭነት ሥራ ላይ ነው /ማቴ. ፱፥፱-፲፫፤ ሉቃ. ፭፥፳፯-፴፪/፡፡

ቅዱስ ማቴዎስ ቍጥሩ ከ፲፪ቱ ሐዋርያት ሲኾን ከ፬ቱ ወንጌሎች አንደኛውን የጻፈው እርሱ በመኾኑ ‹ወንጌላዊ› እየተባለ ይጠራል፡፡ ወንጌሉን የጻፈውም #ጌታችን ባረገ በ፰ኛው ዓመት መጨረሻ በ፵፩ /፵፪ ዓ.ም፣ ቀላውዴዎስ ቄሣር በነገሠ በመጀመሪያው ዘመን በዕብራይስጥ ቋንቋ ነው /ማቴ.፳፰፥፳/፡፡ ጽሕፈቱንም በፍልስጥኤም ጀምሮ በህንድ ፈጽሞታል፡፡

እንደ መምህራነ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ወንጌሉ በውስጡ ከ፻፶ በላይ የብሉይ ኪዳን ጥቅሶችን ማካተቱ አይሁድን ለማሳመን የተጻፈ ለመኾኑ ማስረጃ ነው፡፡ የማቴዎስ ወንጌል ከኦሪታዊ ይዘቱ አኳያ በመጀመሪያ ተቀመጠ እንጂ የተጻፈው ግን ከማርቆስ ወንጌል ቀጥሎ እንደኾነም መምህራን ይናገራሉ፡፡

ቅዱስ ማቴዎስ በሀገረ ስብከቱ በፍልስጥኤም #ጌታችን ከፅንስ ጀምሮ እስከ ዕርገቱ ድረስ ያደረጋቸውን ተአምራት፣ ያስተማረውን ትምህርትና የሠራቸውን ትሩፋቶች ሲያስተምራቸው ብዙ አሕዛብ ከኦሪት ወደ ወንጌል፤ ከገቢረ ኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ ተመልሰዋል፡፡ ምእመናኑ ‹‹በቃል ያለ ይረሳል፤ በመጽሐፍ ያለ ይወረሳልና ያስተማርኸንን ጻፍልን›› ብለውት፤ አንድም እንደ አባትነቱ ከራሱ አንቅቶ /አመንጭቶ/፤ አንድም አይሁድ ክርስቲያኖችን ‹‹ #ክርስቶስ ወልደ ዳዊት ወልደ አብርሃም መኾኑን ሠፍራችሁ፣ ቈጥራችሁ አስረዱን›› ቢሏቸው ለማስረዳት የዕውቀት ማነስ ነበረባቸውና እርሱ ጽፎላቸዋል፡፡

ወንጌሉን ከጻፈ በኋላም ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶ አፓንጌ በሚባል አገር ወንጌልን በመስበክ ብዙዎችን በ #ክርስቶስ አሳምኗል፡፡ የማቴዎስን ወንጌል ወንጌላዊው /ሐዋርያው/ ዮሐንስ በእልአንሳን፣ በህንድና በኢየሩሳሌም አገሮች እየተረጐመ አስተምሮታል፡፡ የእርሱ ስብከት በመጽሐፍ ቅዱስ አለመጠቀሱም መላ ሕይወቱን ለ #ክርስቶስ አገልግሎት የሰጠ ሐዋርያ መኾኑን እንደሚያሳይ መምህራን ይመሰክራሉ፡፡

ቅዱስ ማቴዎስ በወንጌሉ ‹‹ወልደ ዳዊት፣ ወልደ አብርሃም›› በማለት የ #ክርስቶስን ምድራዊ ልደት /ሰው መኾን/ ጽፏልና ከአራቱ የኪሩቤል ገጽ መካከል በአንደኛው በገጸ ሰብእ ይመሰላል፡፡ የኤፌሶን ወንዝ ፈለገ ሐሊብ ይባላል፤ ርስትነቱም ለሕፃናት ነው፡፡ ቅዱስ ማቴዎስም በዘር የሚወለዱ አበውን ልደት ጽፏልና፤ ዳግመኛም ሄሮድስ ስላስፈጃቸው ሕፃናት ተናግሯልና በኤፌሶን ወንዝ ይመሰላል፡፡

ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌልን አስተምሮ ብዙዎችን ወደ አሚነ #እግዚአብሔር ከመለሰ በኋላ #ጌታችን ወደ ካህናት አገር እንዲሔድና የካህን ልብስ ለብሶ፣ ፀጉሩንና ጺሙን ተላጭቶ፣ በቀኝ እጁ ዘንባባ ይዞ ወደ አገሩ ቅፅር እንዲገባ ስላዘዘው በደመና ተጭኖ ሔዶ ወደ ቤተ ጣዖታቱ ገብቶ በጸለየ ጊዜ መብረቅ የመሰለ ብርሃን ወረደ፡፡ የአምላክን ከሃሊነት ለመግለጥ በተከሠተው ርዕደ መሬትም የአገሩ ጣዖታት ኹሉ ወድቀው ተሰባበሩ፡፡ አርሚስ የሚባለው የጣዖቱ ካህንም ካየው አምላካዊ ብርሃንና ድንቅ ተአምር የተነሣ በ #ክርስቶስ አምኖ ከተጠመቀ በኋላ የቅዱስ ማቴዎስ ረድእ ኾኗል፡፡

ይህ ክሥተትም በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙዎችን በ #ክርስቶስ እንዲያምኑ አድርጓቸዋል፡፡ ያማኞች ቍጥርም ፬ ሺሕ እንደ ነበረ በገድለ ሐዋርያት ተጠቅሷል፡፡ ከዚህ በኋላ የንጉሡ ልጅ በሞተ ጊዜ ቅዱስ ማቴዎስ ወደ #እግዚአብሔር ጸልዮ ከሞት ቢያስነሣው ንጉሡ፣ ቤተሰቦቹና የአገሩ ሰዎች ኹሉ በ #ኢየሱስ_ክርስቶስ አምነው አጵሎን የተባለውን ጣዖት በእሳት አቃጥለው ቤተ ጣዖቱን የአምልኮተ #እግዚአብሔር መፈጸሚያ ሥፍራ አድርገውታል፡፡ ቅዱስ ማቴዎስም አርሚስን ኤጲስ ቆጶስ በማድረግ ቀሳውስትንና ዲያቆናትን ሾሞላቸዋል፡፡

በገድለ ሐዋርያት እንደ ተጠቀሰው ቅዱስ ማቴዎስ ከማረፉ በፊት በደመና ተነጥቆ ብሔረ ብፁዓን ገብቷል፤ በዚያም ሄሮድስ በግፍ በጨፈጨፋቸው ሕፃናት ክብረ በዓል #ጌታችን ወደ እነርሱ ሲመጣ፣ መላእክትም በዙሪያው ከበው ሲያመሰግኑት ያይ ነበር፡፡ ከዚያ ተመልሶም በየአገሩ እየዞረ ወንጌልን አስተምሯል፤ ካስተማረባቸው አገሮችም ፍልስጥኤም፣ ፋርስ፣ ባቢሎን፣ ኢትዮጵያና ዓረቢያ ይጠቀሳሉ፡፡ የማስተማር ተልእኮው የተከናወነውም በታንሿ እስያ ውስጥ ነው፡፡ ግሪካውያን አሕዛብ «አምላካችንን ሰደበብን» ብለው አሥረውት በነበረ ጊዜም ወኅኒ ቤት ኾኖ ይሰብክ ነበር፡፡
ቅዱስ ማቴዎስ በ፵ ዓ.ም በአገራችን በኢትዮጵያ እየተዘዋወረ ወንጌልን እንደ ሰበከና በዘመኑ የነበሩ ኦሪታውያን ነገሥታትን ጨምሮ በርካታ አሕዛብን አስተምሮ በማጥመቅ ወደ ክርስትና ሃይማኖት እንደ መለሰ፤ እንደዚሁም ለምጻሞችን በማንጻት፣ አንካሶችን በማርታት፣ ሕሙማንን በመፈወስ፣ ሙታንን በማስነሣት ድንቅ ድንቅ ተአምራትን እንዳደረገ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትና በትግራይ ክልል በማኅበረ ጻድቃን ዴጌ ገዳም የሚገኙ የብራና መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡

በአገልግሎቱ መጨረሻም በትርያ በምትባል አገር ሲያስተምር አገረ ገዥው አሠረው፡፡ በወኅኒ ቤቱም ጌታው ለንግድ የሰጠውን ገንዘብ ማዕበል ወስዶበት በዕዳ ምክንያት የሚያለቅስ አንድ እሥረኛ አገኘና አጽናንቶ መኰንኑ ገንዘቡን ከሕዝቡ ለምኖ እንዲከፍለው በመሻት ከእሥር እንደሚፈታው፤ ከባሕር ዳርቻም የወደቀ ወርቅ የተሞላ ከረጢት እንደሚያገኝ፤ ያንንም ለጌታው ከሰጠ በኋላ ከዕዳና ከእሥር ነጻ እንደሚኾን አስረዳው፡፡ ሰውየውም ቅዱስ ማቴዎስ የተናገረው ኹሉ ስለ ተፈጸመለት ለቅዱስ ማቴዎስ እየሰገደ፤ ‹‹በ #ኢየሱስ_ክርስቶስ አምናለሁ›› እያለ ሃይማኖቱንና ደስታውን ገለጸ፡፡ ይህንን ድንቅ ተአምር የሰሙ ብዙ አሕዛብም በ #ጌታችን አምነዋል፡፡ በዚህ ምክንያትም አርያኖስ በሚባል ንጉሥ ትእዛዝ ጥቅምት ፲፪ ቀን አንገቱን በሰይፍ ተቈርጦ በሰማዕትነት ዐርፏል፤ ምእመናንም ሥጋውን በክብር ቀብረውታል፡፡ ትርጓሜ ወንጌል ደግሞ ብስባራ በምትባል አገር በደንጊያ ተወግሮ በሰማዕትነት ካረፈ በኋላ የቂሣርያ ክፍለ ዕጣ በምትኾን በቅርጣግና መቀበሩን ይናገራል፡፡

#ለእግዚአብሔር ምስጋና ይኹን፡፡ እኛንም በሐዋርያው በቅዱስ ማቴዎስ ጸሎት ይማረን፤ በረከቱም ይደርብን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባ_ድሜጥሮስ

ዳግመኛም በዚችም ቀን ንጹህ ድንግል የጠባይን ፍላጎት ድል የነሳ አባት ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ዐሥራ ሁለተኛ የሆነ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ድሜጥሮስ አረፈ።

ይህም አባት አስቀድሞ መጻሕፍትን ያልተማረ ሕዝባዊ ገበሬ ነው በወላጆቹ የወይን አታክልት ቦታዎች ውስጥ የሚሠራ ሆነ ከታናሽነቱም ሚስት አጋብተውት ከእርሷ ጋር አርባ ስምንት ዓመት ኖረ ድንግልናቸውን በንጽሕና የጠበቁ ናቸው የተሠወረውን ከሚያውቅ #እግዚአብሔር በቀር ይህን የሚያውቅ የለም።

ከእርሱ በፊት የነበረ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ ዮልያኖስ ዕረፍቱ በቀረበ ጊዜ የ #እግዚአብሔር መልአክ ተገለጠለት ። ከእርሱ በኋላ ሊቀ ጳጳሳት የሚሆነውን በምልክት ገለጠለት እንዲህም አለው ነገ የወይን ዘለላ ይዞ ወደ አንተ የሚገባ ሰው አለ ከአንተ በኋላ ሊቀ ጳጳሳት የሚሆን እርሱ ነውና ያዘው አትተወው።

በዚያችም ቀን ቅዱስ ድሜጥሮስ ወደ አታክልቱ ቦታ ገባ ያለ ጊዜው ያፈራ የወይን ዘለላ አገኘ ያንንም የወይን ዘለላ በረከት ሊቀበልበት ወደ ሊቀ ጳጳሳት አባ ዮልዮስ ይዞት ሔደ። በዚያንም ጊዜ አባ ዮልዮስ ድሜጥሮስን በእጁ ይዞ ለሕዝቡ ሁሉና ለኤጲስቆጶሳት አሳልፎ ሰጠው ከእኔ በኋላ ሊቀ ጳጳሳት የሚሆናችሁ ይህ ነው ስለ ርሱ ከ #እግዚአብሔር የተላከ መልአክ ነግሮኛልና ይዛችሁ ሹሙት አላቸው።

ከዚህም በኋላ አባ ዮልዮስ በአረፈ ጊዜ የጸሎቱን ሥርዓት ፈጽመዉለት ሊቀ ጵጵስና ሾሙት ያን ጊዜ #መንፈስ_ቅዱስ መላበት የቤተ ክርስየቲያን የሆኑ የብሉያትና የሐዲሳት መጻሕፍትን አንብቦ ተረጐማቸው ብዙዎች ምሥጢራትም ተገለጡለት።

ከዚህም በኋላ ባሕረ ሐሳብ የተባለውን የዘመን መቊጠሪያ ሠራ ከእርሱ በፊት የነበሩ የክርስቲያን ወገኖች የ #መድኃኒታችን የጥምቀቱን በዓል ጥር ዐሥራ አንድ ቀን አክብረው በማግስቱ የከበረች አርባ ጾምን ጀምረው እስከ የካቲት ሃያ ሁለት ቀን ድረስ ይጾማሉ። ከዚያም በኋላ መጋቢት ሃያ ሁለት ቀን የሆሣዕናን በዓል አክብረው በማግስቱ የሕማማትን ሰሞን ጾም ጀምረው ይጾማሉ። ከሐዋርያትም ዘመን ጀምሮ እስከርሱ ዘመን እንዲህ እያደረጉ ኖሩ።

እርሱም እንዲህ ሠራ የከበረች የ #ጌታችን ጾም መግቢያዋ ከሰኞ ቀን እንዳይፋለስ ፍጻሜውም በዐረብ ቀን ከዚህም የሆሣዕናን በዓል አያይዞ ሠራ በሚቀጥለው ሰኞ ቀን የሕማማት ጾም ተጀምሮ እንዲጾም የስቅለቱም በዓል ከዐርብ ቀን እንዳይፋለስ የከበረች የትንሣኤውና የጰራቅሊጦስም በዓል ከእሑድ ቀን የዕርገቱም በዓል ከሐሙስ እንዳይፋለስ።

እንዲሁም አዘጋጅቶ ለኢየሩሳሌም አገር ለሮሜ ሀገር ለኤፌሶንና ለአንጾኪያ ሀገር ሊቃነ ጳጳሳት ለየአንዳንዳቸው ላከላቸው። እነርሱም በደስታ ተቀብለው ሠሩበት እስከዚችም ቀን ጸንቶ ኖረ።

በቊርባን ቅደሴ ጊዜም ዘወትር ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስን የሚያየው ሆነ። የሕዝቡ ኃጢአታቸው በፊቱ ግልጥ ሆነ ስለዚህም የማይገባቸውን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ከመቀበል ይመልሳቸዋል እንዲህም ይላቸዋል ሒዱ #ንስሐ ግቡ ከዚያም በኋላ መጥታችሁ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙን ተቀበሉ ።

ስለዚህም ነገር ብዙ ሕዝቦች ኃጢአት ከመሥራት የሚጠበቁ ሆኑ ልባቸው የደነደነ ሌሎች ግን ጠሉት እርስ በርሳቸውም እንዲህ ተባባሉ። ይህ ሰው ሚስት አግብቶ ሚስቱም ከእርሱ ጋር ትኖራለች ሳይገባውም በወንጌላዊው ማርቆስ ወንበር ተቀምጠ ከንጹሕ ድንግል በቀር አይሾምበትም ነበርና እኛንም ኃጢአተኞች ናችሁ ብሎ ይገሥጸናል።

በአንዲት ሌሊትም ከ #እግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ወደርሱ መጥቶ ድሜጥሮስ ሆይ ራስህን ብቻ ማዳንን አትሻ ወገኖችህም ይጠፋ ዘንድ አትተው ነፍሱን ስለ መንጋዎቹ አሳልፎ ለሞት የሚሰጥ እርሱ ቸር ጠባቂ እንደሆነ #ጌታችን በቅዱስ ወንጌል የተናገረውን አስብ አለው።

ቅዱስ ድሜጥሮስም መልአኩን ጌታዬ የምትለኝ ምንድን ነው አለው መልአኩም በአንተና በሚስትህ መካከል ተሰውሮ ያለውን ምሥጢር ለወገኖችህ ግለጽ ብሎ መለሰለት።

ከዚህም በኋላ ሕዝቡን አሰባሰባቸው ሊቀ ዲያቆኑንም ወጥተው ወደ ቤታቸው እንዳይገቡ ሕዝቡን ንገራቸው አለው ራሱም ቅዳሴውን ቀደሰ ሁለተኛም ዕንጨቶችን ሰብስበው እሳትን እንዲአነዱ አዘዛቸው እንዳዘዛቸውም አደረጉ። ያን ጊዜ ይህ አባት ተነሥቶ ከሚነደው እሳት መካከል ገብቶ ለረጅም ጊዜ ቁሞ ጸለየ ከእሳቱም ፍም አንሥቶ በሚከናነብበት ቀጸላ አደረገ ሚስቱንም ጠርቶ መጎናጸፊያሽን ዘርጊ አላት በዚያም የእሳቱን ፍም ጨመረ በእሳቱም መካከል በአንድነት እየጸለዩ ቆሙ ሕዝቡም እጅግ ያደንቁ ነበር።

ከዚህም በኋላ ካህናቱና ሕዝቡ እንዲህ ብለው ለመኑት አባታችን ሆይ ይህን የሠራኸውን ሥራ ታስረዳን ዘንድ ከቅድስናህ እንሻለን እርሱም ይህን ሥራ የሠራሁት ከንቱ ውዳሴን ሽቼ አይደለም እናንተ እኔን አምታችሁ ስለእኔ እንዳትጐዱ እንድትድኑ ከዚች ሴት ጋር በመካከላችን ተሠውሮ ያለውን ሚሥጢር እገልጽላችሁ ዘንድ የ #እግዚአብሔር መልአክ ስለአዘዘኝ ነው እንጂ አላቸው።

እርሷ የአባቴ የወንድሙ ልጅ ናት በሕፃንነቷም አባቷ ሞተ በአባቴም ቤት ከእኔ ጋር አደገች አካለ መጠንም በአደረሰን ጊዜ አባቴ እርሷን አጋባኝ ወደ ጫጉላ ቤትም በገባን ጊዜ እኔ እኅትህ ስሆን ለአንተ እንዴት አጋቡኝ አለችኝ። እኔም የምትፈቅጂ ከሆነ ድንግልናችንን ጠብቀን በአንድነት እንኑር ይህንንም በመካከላችን ያለውን ምሥጢር የሚያውቅ አይኑር አልኋት በዚህም ተስማምተን በአንድ ቤት ውስጥ በአንድ ዐልጋ እየተኛን አንድ መጐናጸፊያንም እየተጐናጸፍን አርባ ስምንት ዓመት ያህል ኖርን ይህን ሥራችንንም ያለ #እግዚአብሔር የሚያውቅ የለም እኔም እርሷ ሴት እንደ ሆነች አላወቅኋትም እርሷም እኔን ወንድ እንደሆንኩ አታውቅም በየሌሊቱም ሁሉ በንስር አምሳል ወደ
መኝታችን እየገባ ክንፎቹን አልብሶን ያድራል ሲነጋም ከእኛ ይሠወራል አላቸው።

በዚያንም ጊዜ በደላቸውን ይቅር ይላቸው ዘንድ ከእግሩ ሥር ወድቀው ለመኑት እርሱም ይቅር አላቸው አጽናናቸውም። ይህንንም ድንቅ ሥራ ያዩ ሁሉ ምስጉን #እግዚአብሔርን አመሰገኑት።

በዚህ አባት ዘመንም ስማቸው ቀሌምንጦስ አርጌንስ የሚባሉ ሌሎችም መናፍቃን ስዎች ተነሥተው ታዩ ሌሎችም በአንድነት ሁነው ስለሃይማኖት የፈጠራ መጽሐፍን ጻፉ እርሱም አውግዞ ከምእመናን ለያቸው።

እርሱም ሁል ጊዜ ያለ ዕረፍት ከጥዋት እስከ ማታ ምእመናንን የሚያስተምራቸው ሆነ። ሸምግሎ በደከመም ጊዜ በዐልጋ ላይ አስቀምጠው ተሸክመው ወደ ቤተ ክርስቲያን ያደርሱታል እስከማታ ድረስም ያስተምራቸዋል ሰዎችም ሁሉ ትምህርቱን ይሰሙ ዘንድ ይጨናነቃሉ መላ የሕይወቱ ዘመንም መቶ ሰባት ነው በሰላም በፍቅር አንድነትም አረፈ።

#ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት_12)
🌹#የጥቅምት_12_ግጻዌ🌹

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ጥቅምት_12_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጢሞቴዎስ 5
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁹ ከሁለት ወይም ከሦስት ምስክር በቀር በሽማግሌ ላይ ክስ አትቀበል።
²⁰ ሌሎቹ ደግሞ እንዲፈሩ፥ ኃጢአት የሚሰሩትን በሁሉ ፊት ገሥጻቸው።
²¹ አንድን እንኳ በአድልዎ ሳታደርግ፥ እነዚህን ያለ መዘንበል እንድትጠብቅ በእግዚአብሔርና በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ በተመረጡትም መላእክት ፊት እመክርሃለሁ።
²² በማንም ላይ ፈጥነህ እጆችህን አትጫን፥ በሌሎችም ኃጢአት አትተባበር፤ ራስህን በንጽህና ጠብቅ።
²³ ስለ ሆድህና ስለ በሽታህ ብዛት ጥቂት የወይን ጠጅ ጠጣ እንጂ፥ ወደ ፊት ውኃ ብቻ አትጠጣ።
²⁴ የአንዳንዶች ሰዎች ኃጢአት የተገለጠ ነው ፍርድንም ያመለክታል፥ ሌሎችን ግን ይከተላቸዋል፤
²⁵ እንዲሁ መልካም ሥራ ደግሞ የተገለጠ ነው፥ ያልተገለጠም ከሆነ ሊሰወር አይችልም።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ይሁዳ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁹ የመላእክት አለቃ ሚካኤል ግን ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ ስለ ሙሴ ሥጋ ሲነጋገር፦ ጌታ ይገሥጽህ አለው እንጂ የስድብን ፍርድ ሊናገረው አልደፈረም።
¹⁰ እነዚህ ግን የማያውቁትን ሁሉ ይሳደባሉ፥ አእምሮም እንደሌላቸው እንስሶች በፍጥረታቸው በሚያውቁት ሁሉ በእርሱ ይጠፋሉ።
¹¹ ወዮላቸው፥ በቃየል መንገድ ሄደዋልና ስለ ደመወዝም ለበለዓም ስሕተት ራሳቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል በቆሬም መቃወም ጠፍተዋል።
¹² እነዚህ ከእናንተ ጋር ሲጋበዙ በፍቅር ግብዣችሁ እንደ እድፍ ናቸው፤ እንደ እረኞች ያለ ፍርሃት ራሳቸውን ይጠብቃሉ፤ በነፋስ የተወሰዱ ውኃ የሌለባቸው ደመናዎች፥ ፍሬ የማያፈሩ ሁለት ጊዜ የሞቱ ከነሥራቸው የተነቀሉ በበጋ የደረቁ ዛፎች፥
¹³ የገዛ ነውራቸውን አረፋ እየደፈቁ ጨካኝ የባሕር ማዕበል፥ ድቅድቅ ጨለማ ለዘላለም የተጠበቀላቸው የሚንከራተቱ ከዋክብት ናቸው።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 13
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²² እርሱንም ከሻረው በኋላ ዳዊትን በእነርሱ ላይ እንዲነግሥ አስነሣው፥ ሲመሰክርለትም፦ እንደ ልቤ የሆነ ሰው ፈቃዴንም ሁሉ የሚያደርግ የእሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ አለ።
²³ ከዚህም ሰው ዘር እግዚአብሔር እንደ ተስፋው ቃል ለእስራኤል መድኃኒትን እርሱም ኢየሱስን አመጣ።
²⁴ ከመምጣቱ በፊት ዮሐንስ አስቀድሞ ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ የንስሐን ጥምቀት ሰብኮ ነበር።
²⁵ ዮሐንስም ሩጫውን ሲፈጽም ሳለ፦ እኔ ማን እንደ ሆንሁ ታስባላችሁ? እኔስ እርሱን አይደለሁም፤ ነገር ግን እነሆ፥ የእግሩን ጫማ እፈታ ዘንድ ከማይገባኝ ከእኔ በኋላ ይመጣል ይል ነበር።
²⁶ እናንተ ወንድሞቻችን፥ የአብርሃም ዘር ልጆች ከእናንተ መካከልም እግዚአብሔርን የምትፈሩ ሆይ፥ ለእናንተ የዚህ የመዳን ቃል ተላከ።
²⁷ በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ሰዎችና አለቆቻቸው እርሱንና በየሰንበቱ የሚነበቡትን የነቢያትን ድምፆች ስላላወቁ በፍርዳቸው ፈጽመዋልና፤
²⁸ ለሞትም የሚያደርስ ምክንያት አንድ ስንኳ ባያገኙበት፥ ይገድለው ዘንድ ጲላጦስን ለመኑት፤
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጥቅምት_12_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇🌹

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"እስመ መምህረ ሕግ ይሁብ በረከተ። ወየሐውር እምኀይል ውስተ ኃይል። ወያስተርኢ አምላከ አማልክት በጽዮን"። መዝ 83፥6-7።

#ትርጉም፦ "በልቅሶ ሸለቆ ውስጥ በወሰነው ስፍራ የሕግ መምህር በረከትን ይሰጣልና። ከኃይል ወደ ኃይል ይሄዳሉ፤ የአማልክት አምላክ በጽዮን ይታያል"። መዝ. 83፥6-7።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጥቅምት_12_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማቴዎስ 9
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁹ ጌታችን ኢየሱስም ከዚያ አልፎ በመቅረጫው ተቀምጦ የነበረ ማቴዎስ የሚባል አንድ ሰው አየና፦ ተከተለኝ አለው። ተነሥቶም ተከተለው።
¹⁰ በቤቱም በማዕድ ተቀምጦ ሳለ፥ እነሆ፥ ብዙ ቀራጮችና ኃጢአተኞች መጥተው ከጌታችን ኢየሱስና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር አብረው ተቀመጡ።
¹¹ ፈሪሳውያንም አይተው ደቀ መዛሙርቱን፦ መምህራችሁ ከቀራጮችና ከኃጢአተኞች ጋር አብሮ ስለ ምን ይበላል? አሉአቸው።
¹² ጌታችን ኢየሱስም ሰምቶ፦ ሕመምተኞች እንጂ ባለ ጤናዎች ባለ መድኃኒት አያስፈልጋቸውም፤
¹³ ነገር ግን ሄዳችሁ፦ ምሕረትን እወዳለሁ መሥዋዕትንም አይደለም ያለው ምን እንደ ሆነ ተማሩ፤ ኃጢአተኞችን ወደ ንስሐ እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁምና አላቸው።
¹⁴ በዚያን ጊዜ የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ወደ እርሱ ቀርበው፦ እኛና ፈሪሳውያን፥ ብዙ ጊዜ የምንጦመው፥ ደቀ መዛሙርትህ ግን የማይጦሙት ስለ ምንድር ነው? አሉት።
¹⁵ ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ ሚዜዎች ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊያዝኑ ይችላሉን? ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል፥ በዚያ ጊዜም ይጦማሉ።
¹⁶ በአረጀ ልብስ አዲስ እራፊ የሚያኖር የለም፤ መጣፊያው ልብሱን ይቦጭቀዋልና፥ መቀደዱም የባሰ ይሆናል።
¹⁷ በአረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን፥ አቁማዳው ይፈነዳል፥ የወይን ጠጁም ይፈሳል አቁማዳውም ይጠፋል፤ ነገር ግን አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ያኖረዋል፥ ሁለቱም ይጠባበቃሉ።
¹⁸ ይህንም ሲነግራቸው፥ አንድ መኰንን መጥቶ፦ ልጄ አሁን ሞተች፤ ነገር ግን መጥተህ እጅህን ጫንባት፥ በሕይወትም ትኖራለች እያለ ሰገደለት።
¹⁹ ጌታችን ኢየሱስም ተነሥቶ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተከተለው።
²⁰ እነሆም፥ ከአሥራ ሁለት ዓመት ጀምሮ ደም የሚፈስሳት ሴት በኋላው ቀርባ የልብሱን ጫፍ ዳሰሰች፤
²¹ በልብዋ፦ ልብሱን ብቻ የዳሰስሁ እንደ ሆነ፥ እድናለሁ ትል ነበረችና።
²² ጌታችን ኢየሱስም ዘወር ብሎ አያትና፦ ልጄ ሆይ፥ አይዞሽ፤ እምነትሽ አድኖሻል አላት። ሴቲቱም ከዚያች ሰዓት ጀምራ ዳነች።
²³ ጌታችን ኢየሱስም ወደ መኰንኑ ቤት በደረሰ ጊዜ፥ እምቢልተኞችንና የሚንጫጫውን ሕዝብ አይቶ፦
²⁴ ብላቴናይቱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችምና ፈቀቅ በሉ አላቸው። በጣምም ሳቁበት።
²⁵ ሕዝቡን ግን ከአስወጡ በኋላ ገብቶ እጅዋን ያዛት፥ ብላቴናይቱም ተነሣች።
²⁶ ያም ዝና ወደዚያ አገር ሁሉ ወጣ።
²⁷ ጌታችን ኢየሱስም ከዚያ ሲያልፍ ሁለት ዕውሮች፦ የዳዊት ልጅ ሆይ፥ ማረን ብለው እየጮሁ ተከተሉት።
²⁸ ወደ ቤትም በገባ ጊዜ ዕውሮቹ ወደ እርሱ ቀረቡ፥ ጌታችን ኢየሱስም፦ ይህን ማድረግ እንድችል ታምናላችሁን? አላቸው። አዎን፥ ጌታ ሆይ አሉት።
²⁹ በዚያን ጊዜ፦ እንደ እምነታችሁ ይሁንላችሁ ብሎ ዓይኖቻቸውን ዳሰሰ።
³⁰ ዓይኖቻቸውም ተከፈቱ።
³¹ ጌታችን ኢየሱስም፦ ማንም እንዳያውቅ ተጠንቀቁ ብሎ በብርቱ አዘዛቸው። እነርሱ ግን ወጥተው በዚያ አገር ሁሉ ስለ እርሱ አወሩ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️ 🌹
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ቅዱስ_ጎርጎርዮስ_ዘኑሲስ ቅዳሴ­ ነው። መልካም የቅዱስ ሚካኤል ወራዊ በዓል፣ የሐዋርያው የቅዱስ ማቴዎስ፣ የአባ ድሜጥሮስ የዕረፍታቸው በዓልና የጾም ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።
🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ንስሐ_የሰማያዊም_የምድራዊም_ደስታ_ምንጭ_ነው!

አንድ ኃጢያተኛ #ንስሐ ቢገባ በሰማይ ደስታ እንደሚደረግ በቅዱስ መጽሐፍ ተጽፏል። ሉቃ.15÷7-10። በአንድ ኃጥእ #ንስሐ መግባት ሰማያውያን ቅዱሳን መላእክትና ጻድቃን ሁሉ ሐሴት ያደርጋሉ። እንደ ፈጣሪያቸው የሰው ድኅነት ያስደስታቸዋልና። በምድርም በ #ንስሐ ምክንያት ከኃጢያት እሥራት መፈታትና ከአጋንንት ግዞት ነጻ መውጣት ከኃጢያት ተለይቶ በንጽሕና በቅድስና መኖር ይገኛልና #ንስሐ ሥጋዊ ያይደለ መንፈሳዊ ደስታ ምንጭ ነው መባሉ ትክክል ሆኖ እናገኘዋለን። ኢሳ.61÷1። #ንስሐ የድል አድራጊነት ሕይወት ነውና የደስታ ምንጭ ነው። ይህን ቅዱስ ዳዊት "ለጥርሳቸው ንክሻ ያላደረገን #እግዚአብሔር ይመስገን"፤ ነፍሳችን እንደ ዖፍ ከአዳኞች ወጥመድ አመለጠች ወጥመድ ተሰበረ እኛም አመለጥን "መዝ.123÷6-7 በማለት አብራርቶታል።

#ይቀጥላል.......
🌹 "በስመ #አብ_ወወልድ_ወመንፈስ_ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። 🌹

🌹"#ሰአሉ_ለነ_አርባዕቱ_ወንጌላውያን መምህራን ሥዩማን አዕማዲሃ ለቤተ ክርስቲያን ሰአሉ ለነ አስተምሕሩ ለነ"። ትርጉም፦ የቤተ ክርስቲያን ምሶሶዎች የምትኾኑ ሹማምንት መምህራን የምትኾኑ #አራቱ_ወንጌላውያን_ለምኑልን_ማልዱልን

🌹 "#ዘብእሲ_ማቴዎስ እስመ ዜነወ ልደቶ ለመድኒነ #እምዘርዐ_ዳዊት_ንጉሥ በቤተልሔም ዘይሁዳ"። ትርጉም፦ በገጸ ብእሲ #ሰው_የተመሰለ_ማቴዎስ ነው የይሁዳ ክፍል በምኾን በቤተ ልሔም #ከንጉሥ_ዳዊት ዘር የመድኀኒታችንን ልደት ተናግሯልና። #ሊቁ_አባ_ጊዮርጊስ_ዘጋስጫ_በሰዓታቱ_ላይ
#ጥቅምት_13

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥቅምት አስራ ሦስት በዚችም ዕለት የዓለሙ ሁሉ መምህር የሆነ የከበረ አባት #ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ መታሰቢያው ነው፤ #የመነኰስ_ቅዱስ_ዘካርያስም የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ

ጥቅምት አስራ ሦስት በዚችም ዕለት የዓለሙ ሁሉ መምህር የሆነ የከበረ አባት ዮሐንስ አፈወርቅ መታሰቢያው እንደሆነ ስንክሳሩ በስም ይጠቅሰዋል።

ይህም አባት ከእስክንድርያ አገር ሰዎች ወገን ነው የአባቱም ስም አስፋኒዶስ የእናቱም ስም አትናሲያ ነው እሊህም እጅግ ባለጸጎች ነበሩ ይህንንም ልጃቸውን በመልካም አስተዳደግ አሳደጉት ትምህርትንና ጥበብንም ሁሉ አስተማሩት እርሱ ወደ አቴና ሔዶ በመምህራን ቤት ተቀምጦ ትምህርትን ሁሉ ተምሮ በዕውቀቱ ከብዙዎች በላይ ከፍ ከፍ ብሏልና።

ከዚህም በኋላ ገና በታናሽነቱ መነኰሰ የዚህንም የኃላፊውን ዓለም ጣዕም ንቆ ተወ ከእርሱም ቀድሞ በዚሁ ገዳም ቅዱስ ባስልዮስ መንኵሶ ነበር በአንድነትም ተስማምተው ብዙ ትሩፋትን ሠሩ ወላጆቹም በሞቱ ጊዜ ከተውለት ገንዘብ ምንም ምን አልወሰደም ለድኆችና ለምስኪኖች ሰጠ እንጂ ከዚያም በምንኵስና ሥራ በመጠመድ ፍጹም ገድልን እየተጋደለ ኖረ።

በዚያም ገዳም ሶርያዊ ጻድቅ ሰው ስሙ ሲሲኮስ የሚባል መነኰስ ነበረ እርሱም ወደፊት የሚሆነውን በ #መንፈስ_ቅዱስ ያይ ነበር በአንዲት ሌሊትም ለጸሎት እየተጋ ሳለ ሐዋርያትን ጴጥሮስንና ዮሐንስን አያቸው ወደ ዮሐንስ አፈወርቅ ገብተው ጴጥሮስ መክፈቻ ሰጠው ወንጌላዊ ዮሐንስም ወንጌልን ሰጠው እንዲህም አሉት በምድር ያሠርከው በሰማይ የታሠረ ይሆናል በምድርም የፈታኸው ደግሞ በሰማያት የተፈታ ይሆናልና በውስጥህ #መንፈስ_ቅዱስ ያደረብህ አዲስ ዳንኤል ሆይ የክብር ባለቤት ከሆነ ከታለቅ መምህር #ኢየሱስ_ክርስቶስ ዘንድ ወደ አንተ ተልከናልና ዕወቅ እኔም የመንግሥተ ሰማያት መክፈቻ የተሰጠኝ ጴጥሮስ ነኝ።

ሁለተኛውም እኔም በመጀመሪያው ስብከቴ በከበረ ወንጌል ቃል አስቀድሞ ነበረ ያልኩ ይህም ቃል በጠላት ላይ የእሳት ሰይፍ የሆነ ዮሐንስ ነኝ። ለአንተም ከክብር ባለቤት #ጌታ_ኢየሱስ_ክርስቶስ ዘንድ ወገኖችህ ምእመናንን በቀናች ሃይማኖት ታሳድጋቸው ዘንድ ዕውነተኛ አእምሮ ደግሞ ተሰጥቶሃል።

ጻድቅ ሲሲኮስም ይህን ራእይ በአየ ጊዜ ቅዱስ ዮሐንስ ቸር ታማኝ እረኛ ሁኖ እንደሚሾም ዐወቀ። ከዚህም በኋላ በቅዱስ ዮሐንስ ላይ የ #መንፈስ_ቅዱስ ጸጋ በላዩ ወርዶ አደረበትና ብዙ ድርሳናትንና ተግሣጻትን ደረሰ ዲያቆን ሁኖ ሳለም የቤተ ክርስቲያንን መጻሕፍት ብሉያትንና ሐዲሳትን ተረጐመ። በአንዲት ሌሊትም ቅዱስ ዮሐንስ ሲጸልይ የ #እግዚአብሔር መልአክ በድንገት እንደ በረድ ነጭ በሆነ ልብስ ተገለጠለት ቅዱስ ዮሐንስም ሲያየው ደንግጦ በምድር ላይ ወደቀ መልአኩም አርአያውን ለውጦ እንደ ሰው ሁኖ ታየው ወዳጄ አዲስ ዳንኤል ሆይ አትፍራ ተነሣ አለው የቅዱስ ዮሐንስም ልቡ ተጽናንቶ ጌታዬ አንተ ማነህ ግርማህ አስፈርቶኛልና አለው የ #እግዚአብሔር መልአክም ትሠራው ዘንድ የሚገባህን ልነግርህ ወዳንተ የተላክሁ ነኝ።

አሁንም #እግዚአብሔር አምላክ ያዘዘህን ለመሥራት ልብህን አበርታ ቃልህ ከጽንፍ እስከ ጽንፍ በአራቱ ማእዘን ይደርሳልና እልፍ አእላፋትም ትምህርትህን ተቀብለው ትእዛዝህን ሰምተው ወደ ፈጣሪያቸው #እግዚአብሔር ተመልሰው ይድናሉና በ #እግዚአብሔር መንግሥትም ውስጥ የጸና የብርሃን ዐምድ ትሆናለህና። እነሆ የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት ወደ አንተ ይመጣል ከእርሱም ጋራ ሁሉም ካህናትና ዲያቆናት በየማዕረጋቸው የሚያዝህንም አድርግ የ #እግዚአብሐር ትእዛዝ ነውና ልትተላለፍ አይገባህም አለው። ከዚህም በኋላ ያ መልአክ ለአባ ፊላትያኖስ ተገልጦ ቅዱስ ዮሐንስን ቅስና እንዲሾመው አዘዘው በማግሥቱም ሊቀ
ጳጳሳቱ መጣ ከርሱ ጋራም ካህናት አሉ ይህን ቅዱስ ዮሐንስንም ይዞ ቅስና ሾመው።

የቍስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳሳትም በአረፈ ጊዜ ንጉሥ አርቃድዮስ ልኮ አስመጥቶ ቅዱስ ዮሐንስን በቍስጥንጥንያ ላይ ሊቀ ጵጵስና ሾመው አባቶቻችን ሐዋርያት እንደሚያደርጉት በሊቀ ጵጵስናው ሥራ ላይ ጸና ሕይወትነት በአላቸው ትምህርቶችና ተግሣጾች ሕዝቡን ሁልጊዜ የሚአስተምር ሆነ። ከኤጲስቆጶሳትም ሆነ ከመንግሥት ወገን ሕግን የሚተላለፉትን ሁሉ ይገሥጻቸዋል ማንንም አይፈራም ፊት አይቶም አያደላም።

የንጉሥ አርቃድዮስ ሚስት አውዶክስያም ገንዘብ ወዳጅ ስለሆነች የአንዲት ድኃ መበለት ቦታዋን በግፍ ወሰደች ያቺ መበለትም ወደ ቅዱስ ዮሐንስ መጥታ ንግሥት አውዶክስያ ቦታዋን እንደነጠቀቻት ነገረችው እርሱም የደኃዋን ቦታዋን መልሺላት ብሎ ከብዙ ምክር ጋር እንድትመልስላት ንግሥት አውዶክስያን ለመናት እርሷ ግን እምቢ በማለት አልታዘዘችለትም። ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብታ ሥጋውን ደሙን እንዳትቀበል አውግዞ ለያት።

ቍጣንና ብስጭትንም ተመልታ ስለ ክፉ ሥራቸው ከሹመታቸው እርሱ የሻራቸውን ኤጲስቆጶሳት ሰበሰበች እነርሱም ንግሥቲቱን ስለ ተቃወመ ስደት እንደሚገባው በእርሱ ላይ ተስማምተው ጻፉ እርሷም አጥራክያ ወደ ሚባል ደሴት ሰደደችው።

ከዚያም በደረሰ ጊዜ የዚያች ደሴት ሰዎች በክፉ ሥራ ጸንተው የሚኖሩ ከሃድያን ሁነው አገኛቸው ቅዱስ ዮሐንስም አስተማራቸው ገሠጻቸውም በፊታቸው ስለ አደረጋቸው ድንቆች ተአምራት ወደ ቀናች ሃይማኖት አስገባቸው።

የሮሜ ንጉሥ አኖሬዎስና ሊቀ ጳጳሳቱ ዮናክኒዶስ ስለ ቅዱስ ዮሐንስ ስደት በሰሙ ጊዜ እጅግ አዘኑ በንጉሥ አርቃድዮስ ላይም በመቆጣት እንዲህ የሚል ደብዳቤ ጽፈው ላኩ ከዚህ ከክፉ ሥራ ተጠበቅ ትእዛዛችንንም ተቀብለህ የከበረ ዮሐንስን ከስደቱ ከአልመለስከው በአንተና በእኛ መካከል ሰላም አይኖርም። መልእክታቸውንም በአነበበ ጊዜ እጅግ አዘነ ሚስቱንም አግዶ ልኮ ቅዱስ ዮሐንስን ከስደቱ መለሰው በተመለሰ ጊዜም የቍስጥንጥንያ ሰዎች በመመለሱ ታላቅ ደስታ አደረጉ። ከጥቂት ቀኖች በኋላም ንግሥቲቱ ወደ ክፋቷ ተመልሳ ሁለተኛ ወደ አጥራክያ ደሴት ሰደደችውና በዚያው አረፈ።

ንጉሥ አኖሬዎስና ሊቀ ጳጳሳት ዮናክኒዶስም በሰሙ ጊዜ መልእክትን ላኩ ሊቀ ጳጳሳቱም የከበረ ዮሐንስን ከስደቱ እስከምትመልሰው ድረስ ሥጋውንና ደሙን እንዳትቀበል አውዶክስያን አወገዛት። ከዚህም በኋላ የከበረ ዮሐንስን ይመልሱት ዘንድ ንጉሥ ላከ ግን ሙቶ አገኙት ሥጋውንም ተሸክመው ወደ ቊስጥንጥንያ ከተማ አደረሱት። የከበረ ዮሐንስም በተሰደደበት አገር እንደአረፈና ሥጋውንም ወደ ቍስጥንጥንያ ከተማ እንዳመጡ ወደ አባ ዮናክኒዶስ መልእክት ጽፈው አስረዱት። ሁለተኛም የሮሜ ሊቀ ጳጳሳት ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብታ ሥጋውንና ደሙን እንዳትቀበል ልኮ አውድክስያን አወገዛት እየለመነችውም ስምንት ወር ያህል ኖረች በብዙ ልመናም ፈታት።

ነገር ግን ጭንቅ በሆነ ደዌ #እግዚአብሔር አሠቃያት ያድኗት ዘንድ ገንዘቧን ለባለ መድኃኒቶች ጥበበኞች እስከ ሰጠች ድረስ ግን አልዳነችም ወደ ቅዱስ ዮሐንስ መቃብርም ሔዳ በእርሱ ላይ ያደረገችውን በደል ይቅር ይላት ዘንድ እየሰገደችና እያለቀሰች ለመነችው እርሱም ይቅር አላት ከደዌዋም ፈወሳት። #ጌታችንም ከሥጋው ታላላቅ ድንቆች ታአምራትን ገለጠ።
👍1
ስለርሱም እንዲህ ተባለ በአንዲት ዕለትም ከንጉሥ አርቃዴዎስ ጋር ተቀምጦ ሳለ ንጉሡ እንዲህ አለው አባቴ ሆይ ስለ አንድ ቃል እንድታስረዳኝ እለምንሃለሁ። ይህም ቃል ከብዙ ጊዜ ጀምሮ በልቤ ውስጥ ይመላለሳል ወንጌላዊ ማቴዎስ ቅድስት ድንግል እመቤታችን #ማርያምን የበኵር ልጅዋን እስከ ወለደች ድረስ ዮሴፍ አላወቃትም ስለምን አለ ወንዶች ሴቶችን እንደሚአውቋቸው ዮሴፍ አወቃትን አለው።

የከበረ ዮሐንስም ንጉሥ ሆይ እንዲህ አትበል እንዲህ አንተ እንደምትለው አይደለም የከበረች #ድንግል እመቤታችንስ የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ በሆድዋ ውስጥ በነበረ ጊዜ የእርሱ ኅብረ መልክ በሚለዋወጥ ጊዜ ከእርሱ ጋር መልኳ ይለወዋወጥ ነበር። በንጹሕ ብርሌ ውስጥ ውኃ በጨመሩ ጊዜ ውኃ መስሎ እንደሚታይ ወይን ጠጅም ቢጨምሩ ያንኑ መስሎ እንደሚታይ ወይም ከውስጡ በተጨመረው ቀይም ቢሆን ቀልቶ እንደሚታይ ቅጠልያም ቢገባበት ቅጠልያ መስሎ እንደሚታይ። ድንግልም በሆድዋ ውስጥ የልጅዋ መልክ በሚለዋወጥ ጊዜ ከእርሱ ጋራ መልኳ ይለዋወጥ ነበር። እንደ ሮማን አበባ የምትቀላበት ጊዜ አለ እንደ ናርዶስም የምታብለጨልጭበት ጊዜ አለ የለመለመ ቅጠል የምትመስልበትም ጊዜ አለ ከወለደች በኋላ ግን አልተለወጠችምና ዮሴፍ በአንድ በቀድሞው ኅብረ መልኳ ተወስናለት መልኳን ተረዳ ማለት ነው አለው። በዚያን ጊዜ በንጉሥ አዳራሽ ውስጥ ከወርቅ የተሠራ የእመቤታችን አምላክን የወለደች የድንግል #ማርያም ሥዕል ነበረችና አፈ ወርቅ ዮሐንስ ልሳነ ወርቅ ዮሐንስ አፈ በረከት ዮሐንስ መልካም ተናገርክ የሚል ቃል ከእርሷ ወጣ።

ንጉሡና ከእርሱ ጋር ያሉት በሰሙ ጊዜ እጅግ አደነቁ #እግዚአብሔርንም አመሰገኑት በዚያን ጊዜ ንጉሥ አዝዞ ወርቅ ሠሪ አስመጥቶ ለከበረ ዮሐንስ የወርቅ ልሳን አሠርቶ ለሚያየው ሁሉ መታሰቢያ ምልክት ሊሆን አምላክን ከወለደች ከእመቤታችን ከድንግል #ማርያም ሥዕል ዘንድ ሰቀለው። ቅዱስ ዮሐንስንም ከዚያች ቀን ወዲህ ልሳነ ወርቅ ብሎ ጠራው አፈ ወርቅም ተብሎ እስከዛሬ ተጠራ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#መነኮስ_ቅዱስ_ዘካርያስ

ዳግመኛም በዚችም ቀን ደግሞ የመነኰስ ዘካርያስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ሆነ። የዚህም መስተጋድል የአባቱ ስም አቃርዮስ ነው። ይህም አቃርዮስ የምንኲስና ልብስ ሊለብስ ሽቶ ለሚስቱ ነገራት እርሷም በነገራት ነገር ተስማማች። ወንድና ሴት ሁለት ልጆች አሉአቸው እነርሱንም ከእናታቸው ዘንድ ትቶ እርሱ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔዶ ከአንድ አረጋዊ አባት መነኰስ ዘንድ በዚያ መነኰሰ።

ከጥቂት ወራትም በኋላ በሀገር ውስጥ ረኃብ ሆነ ሚስቱም ልጆቿን ይዛ ወደ አስቄጥስ ገዳም ወደባሏ አቃርዮስ መጣች በረኃብም ስለ ሆነው ችግር ነገረችው አቃርዮስም እነሆ #እግዚአብሔር በመካከላችን ፍርድን አድርጎ ልጆቻችንን አካፈለን እኔም ወንዱን ልጄን እወስዳለሁ አንቺም ሴት ልጅሽን ውሰጂ አላት ይህንንም ብሎ ልጁን ወሰደ ይኸውም ዘካርያስ ነው እርሷም ሴቷን ልጅዋን ይዛ ተመለሰች።

ከዚህም በኋላ ልጁን ዘካርያስን ወደ ቅዱሳን አረጋውያን አቀረበው እነርሱም በላዩ ጸለዩ ባረኩትም እርሱ ፍጹም መነኲሴ እንደሚሆንም ትንቢት ተናገሩለት።

ዘካርያስም ከበጎ ሥራ ጋር በገዳም ውስጥ አደገ መልኩም እጅግ ያማረ ነው ስለርሱም ጉርምርምታ ሆነ መነኰሳቱም እርስበርሳቸው ይህ ወጣት ይህን ያህል እጅግ መልከ መልካም ሲሆን በገዳም ውስጥ በመነኰሳት መካከል እንዴት ይኖራል ተባባሉ።

ዘካርያስም ስለርሱ መነኰሳት እንዳንጐራጐሩ በሰማ ጊዜ ናጥራን ወደሚባል ተራራ ስር ወደአለች ዐዘቅት ሔደ ልብሱንም አውልቆ በረግረግ ውስጥ ተኛ ሥጋውም ተነፋፍቶ ጠቆረ ተመላልጦም ቈሰለ ብዙ ዘመንም በደዌ እንደኖረ ሆነ፤ ከዚህም በኋላ ልብሱን ለብሶ ወደ ገዳም መጣ ያወቀውም የለም። ከብዙ ቀኖችም በኋላ አባቱ አስተውሎ ልጁ ዘካርያስ እንደ ሆነ አወቀውና መልክህን የለወጠው ምንድን ነው ብሎ ጠየቀው እርሱም ያደረገውን ሁሉ ነገረው።

በእሑድ ቀንም ሥጋውንና ደሙን ሊቀበል ወደ ቤተ ክርስቲያን ገባ #እግዚአብሔርም ያን ጊዜ ሥራውን ለአባ ኤስድሮስ ገለጸለት እርሱም ዘካርያስ የሠራውን ለወንድሞች መነኰሳት አስረዳቸው እነርሱም አስቀድሞ እንደ ሰው ሁነህ መጣህ ዛሬ ግን እንደ #እግዚአብሔር መልአክ ሁነህ መጣህ አሉት።

ይህ አባት ዘካርያስም በብዙ ገድል ሲጋደል ኖረ ትሕትናን ቅንነትን ያማረ የትሩፋትን ሥራ ሁሉ ገንዘብ አደረገ አባቱም ስለርሱ እኔ በገድል ብዙ ደክሜአለሁ ነገር ግን ከልጄ ሥርዓተ ገድል አልደረስኩም ብሎ ተናገረ።

በዚህ ተጋድሎውም አርባ አምስት ዓመት ኑሮ #እግዚአብሔርን ከአገለገለው በኋላ በፍቅር አንድነት አረፈ መላ ዘመኑም ሃምሳ ሁለት ነው። ከዚህም ሰባቱን ዓመት በወላጆቹ ቤት አርባ አምስቱን በገዳም ኖረ።

ዳግመኛ በዚህች ቀን ቀሲስ #አብጥልማኮስና ወንድሞቹ በሰማዕትነት አረፉ በተጨማሪም የ #አውስኖ፣ የ #የአውሲኪዮስ#ናውላውስና የአቤላ መታሰቢያቸው ነው።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳስ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት_13ና_ግንቦት_12)
🌹 #የጥቅምት_13_ግጻዌ 🌹

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ጥቅምት_13_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
2ኛ ቆሮ 9
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ለቅዱሳን ስለሚሆነው አገልግሎት ልጽፍላችሁ አያስፈልግምና፤
² በጎ ፈቃዳችሁን አውቄአለሁና፤ ስለዚህም፦ አካይያ ከአምና ጀምሮ ተዘጋጅቶአል ብዬ ለመቄዶንያ ሰዎች በእናንተ እመካለሁ፥ ቅንዓታችሁም የሚበዙቱን አነሣሥቶአል።
³ ነገር ግን ለእነርሱ እንዳልሁ፥ የተዘጋጃችሁ ትሆኑ ዘንድ በዚህም ነገር ስለ እናንተ ያለው ትምክህታችን ከንቱ እንዳይሆን ወንድሞችን እልካለሁ፤
⁴ ምናልባት የመቄዶንያ ሰዎች ከእኔ ጋር ቢመጡ፥ ያልተዘጋጃችሁም ሆናችሁ ቢያገኙአችሁ፥ እናንተ እንድታፍሩ አላልንም እኛ ግን በዚህ እምነታችን እንድናፍር አይሁን።
⁵ እንግዲህ እንደ በረከት ሆኖ ከስስት የማይሆን ይህ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ አስቀድመው ወደ እናንተ መጥተው፥ አስቀድማችሁ ተስፋ የሰጣችሁትን በረከት አስቀድመው እንዲፈጽሙ ወንድሞችን እለምን ዘንድ እንዲያስፈልገኝ አሰብሁ።
⁶ ይህንም እላለሁ፦ በጥቂት የሚዘራ በጥቂት ደግሞ ያጭዳል፥ በበረከትም የሚዘራ በበረከት ደግሞ ያጭዳል።
⁷ እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ፥ በኀዘን ወይም በግድ አይደለም።
⁸-⁹ በተነ፥ ለምስኪኖች ሰጠ፥ ጽድቁ ለዘላለም ይኖራል ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ እግዚአብሔር፥ ሁልጊዜ በነገር ሁሉ ብቃትን ሁሉ አግኝታችሁ ለበጎ ሥራ ሁሉ ትበዙ ዘንድ፥ ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ያዕቆብ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁹-¹⁰ የተዋረደው ወንድም ግን በከፍታው፥ ባለ ጠጋም በውርደቱ ይመካ፤ እንደ ሣር አበባ ያልፋልና።
¹¹ ፀሐይ ከትኵሳት ጋር ይወጣልና፥ ሣርንም ያጠወልጋልና፥ አበባውም ይረግፋልና፥ የመልኩም ውበት ይጠፋልና፤ እንዲሁ ደግሞ ባለ ጠጋው በመንገዱ ይዝላል።
¹² በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው፤ ከተፈተነ በኋላ ለሚወዱት ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን የሕይወትን አክሊል ይቀበላልና።
¹³ ማንም ሲፈተን፦ በእግዚአብሔር እፈተናለሁ አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና፤ እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም።
¹⁴ ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል።
¹⁵ ከዚህ በኋላ ምኞት ፀንሳ ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች።
¹⁶ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ አትሳቱ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 20
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁶ ጳውሎስ በእስያ እጅግ እንዳይቀመጥ ኤፌሶንን ይተው ዘንድ ቆርጦ ነበርና ቢቻለውም በዓለ ኀምሳን በኢየሩሳሌም ይውል ዘንድ ይቸኩል ነበርና።
¹⁷ ከሚሊጢንም ወደ ኤፌሶን ልኮ የቤተክርስቲያንን ሽማግሌዎች አስጠራቸው፤
¹⁸-¹⁹ ወደ እርሱም በመጡ ጊዜ እንዲህ አላቸው፦ ወደ እስያ ከገባሁበት ከመጀመሪያ ቀን ጀምሮ፥ በትሕትና ሁሉና በእንባ ከአይሁድም ሴራ በደረሰብኝ ፈተና ለጌታ እየተገዛሁ ዘመኑን ሁሉ ከእናንተ ጋር እንዴት እንደ ኖርሁ እናንተው ታውቃላችሁ፤
²⁰-²¹ ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ንስሐንና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ማመንን ለአይሁድና ለግሪክ ሰዎች እየመሰከርሁ በጉባኤም በየቤታችሁም አወራሁላችሁና አስተማርኋችሁ እንጂ፥ ከሚጠቅማችሁ ነገር አንዳች ስንኳ አላስቀረሁባችሁም።
²² አሁንም፥ እነሆ፥ እኔ በመንፈስ ታስሬ ወደ ኢየሩሳሌም እሄዳለሁ፥ በዚያም የሚያገኘኝ ምን እንደ ሆነ አላውቅም፤
²³ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ፦ እስራትና መከራ ይቆይሃል ብሎ በየከተማው ሁሉ ይመሰክርልኛል።
²⁴ ነገር ግን ሩጫዬንና ከጌታ ከኢየሱስ የተቀበልሁትን አገልግሎት እርሱም የእግዚአብሔርን ጸጋ ወንጌልን መመስከር እፈጽም ዘንድ ነፍሴን በእኔ ዘንድ እንደማትከብር እንደ ከንቱ ነገር እቆጥራለሁ።
²⁵ አሁንም፥ እነሆ፥ እኔ የእግዚአብሔርን መንግሥት እየሰበክሁ በመካከላችሁ የዞርሁ ሁላችሁ ከእንግዲህ ወዲህ ፊቴን እንዳታዩ አውቃለሁ።
²⁶ ስለዚህ እኔ ከሰው ሁሉ ደም ንጹሕ እንደ ሆንሁ ዛሬ በዚች ቀን እመሰክርላችኋለሁ።
²⁷ የእግዚአብሔርን ምክር ሁሉ ነግሬአችኋለሁና፥ ምንም አላስቀረሁባችሁም።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጥቅምት_13_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇🌹

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ጻድቅሰ ከመ በቀልት ይፈሪ። ወይበዝኅ ከመ ዘግባ ዘሊባኖስ። ትኩላን እሙንቱ ውስተ ቤተ #እግዚአብሔር"። መዝ 91፥12-13።

#ትርጉም፦ "ጻድቅ እንደ ዘንባባ ያፈራል፥ እንደ ሊባኖስ ዝግባም ያድጋል። በ #እግዚአብሔር ቤት ውስጥ ተተክለዋል፥ በአምላካችንም አደባባይ ውስጥ ይበቅላሉ"። መዝ 91፥12-13።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጥቅምት_13_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሉቃስ 12
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²⁷ አበቦችን እንዴት እንዲያድጉ ተመልከቱ፤ አይደክሙም አይፈትሉምም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ሁሉ ከእነዚህ እንደ አንዲቱ አለበሰም።
²⁸ እግዚአብሔር ግን ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን በሜዳ የሆነውን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ፥ እናንተ እምነት የጐደላችሁ፥ እናንተንማ ይልቁን እንዴት?
²⁹ እናንተም የምትበሉትን የምትጠጡትንም አትፈልጉ፥ አታወላውሉም፤
³⁰ ይህንስ ሁሉ በዓለም ያሉ አሕዛብ ይፈልጉታልና፤ የእናንተም አባት ይህ እንዲያስፈልጋችሁ ያውቃል።
³¹ ዳሩ ግን መንግሥቱን ፈልጉ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️ 🌹
የሚቀደሰው ቅዳሴ  የ #ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈ_ወርቅ ቅዳሴ ነው። መልካም የአባ ዘካርያስ የዕረፍት በዓል፣ የቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ የመታሰቢያውና የጾም ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።
🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
2025/10/22 16:39:30
Back to Top
HTML Embed Code: