Telegram Web
🌹 "በስመ #አብ_ወወልድ_ወመንፈስ_ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። 🌹

🌹 እንኳን #ለዘመነ_ለማኅሌተ_ጽጌ_ለሦስተኛ_ሳምንት ለዕለተ እሑድ #እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።

🌹 #የዚህ_ሳምንት_መዝሙር፦ ሃሌ ሉያ በ ፫ "#ወመኑ_መሐሪ_ዘከማከ፤ ምስለ #ኖኅ_ኪዳነ ዘአቀምከ #ለደቂቀ_እስራኤል መና ዘአውረድከ፤ አዝ፣ #ወበጽጌያት_ምድረ_አሠርጎከ ወሥነ ገዳምኒ ምስለ ቅዱሳኒከ፤ አዝ፣ ወከመ ወሬዛ ኀየል መላትሒሁ ጒርዔሁ መዐርዒር አምሳሉ ዘወይጠል፤ አዝ፣ ሰማየ ወምድረ ዘአንተ ፈጠርከ #ፀሐየ_ወወርኃ_ዘአስተዋደድከ፤ አዝ፣ በከዋክብት ሰማየ ዘከለልከ ወበጽጌያት ምድረ አሠርጎከ፤ አዝ፣ #ቀደሳ_ወአክበራ_አዕበያ_ለሰንበት ወአልዓላ እምኲሉ ዕለት ወመኑ መሐሪ ዘከማከ ወኲሉ ይሴፎ ኪያከ"። #ትርጉም#እንደ_አንተ_ያለ_ይቅር ባይ ማነው? #ከኖኅ_ጋር_ቃል_ኪዳንን ያቆምህ (ያጸናህ)፤ #ለእስራኤል_ልጆች_መናን_ያወረድህ#በአበቦች_ውበት_ምድርን_ያስጌጥክ፣ የገዳምን ውበት ከቅዱሳንህ ጋር ነው አስጌጥክ እንደ ኃይለኛ ጎልማሳ እንደ ዋሊያ ጉረሮው ጣፋጭ ነው ሰማይና ምድርን የፈጠርህ፣ #ፀሐይና_ጨረቃን_ያስማማህ፣ በከዋክብት ሰማይን የጋረድክ፣ በአበቦችን አሳየ፣ ቁጥር የሌለው ብዙ አበቦችን አሳይ፣ ለሕዝብህ በረከትን ስጥ፣ #ሰንበትን_ቀደሳት_አከበራት_ከዕለታት_ሁሉ_ከፍ ከፍ አደረጋት እንዳንተ ያለ ይቅር ባይ ማነው ሁሉ አንተን ተስፋ ያደርጋል። #ሊቁ_ቅዱስ_ያሬድ_በድጓው_ላይ

                    
#የጥቅምት_16_ግጻዌ

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ጥቅምት_16_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ቆሮንቶስ 10
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ወንድሞች ሆይ፥ ይህን ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ። አባቶቻችን ሁሉ ከደመና በታች ነበሩ ሁሉም በባሕር መካከል ተሻገሩ፤
² ሁሉም ሙሴን ይተባበሩ ዘንድ በደመናና በባሕር ተጠመቁ፤
³ ሁሉም ያን መንፈሳዊ መብል በሉ፥ ሁሉም ያን መንፈሳዊ መጠጥ ጠጡ፤
⁴ ይከተላቸው ከነበረው ከመንፈሳዊ ዓለት ጠጥተዋልና፥ ያም ዓለት ክርስቶስ ነበረ።
⁵ እግዚአብሔር ግን ከእነርሱ በሚበዙት ደስ አላለውም፥ በምድረ በዳ ወድቀዋልና።
⁶ እነዚህም ክፉ ነገር እንደ ተመኙ እኛ ደግሞ እንዳንመኝ ይህ ምሳሌ ሆነልን።
⁷ ሕዝብም ሊበሉ ሊጠጡም ተቀመጡ ሊዘፍኑም ተነሡ ተብሎ እንደ ተጻፈ ከእነርሱ አንዳንዶቹ እንዳደረጉት ጣዖትን የምታመልኩ አትሁኑ።
⁸ ከእነርሱም አንዳንዶቹ እንደ ሴሰኑ በአንድ ቀንም ሁለት እልፍ ከሦስት ሺህ እንደ ወደቁ አንሴስን።
⁹ ከእነርሱም አንዳንዶቹ ጌታን እንደ ተፈታተኑት በእባቦቹም እንደ ጠፉ ጌታን አንፈታተን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ራእይ 14
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ አየሁም፥ እነሆም፥ በጉ በጽዮን ተራራ ቆሞ ነበር፥ ከእርሱም ጋር ስሙና የአባቱ ስም በግምባራቸው የተጻፈላቸው መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ።
² እንደ ብዙ ውኃም ድምፅና እንደ ታላቅ ነጐድጓድ ድምፅ ያለ ከሰማይ ድምፅን ሰማሁ፥ ደርዳሪዎችም በገና እንደሚደረድሩ ያለ ድምፅ ሰማሁ።
³ በዙፋኑም ፊት በአራቱም እንስሶችና በሽማግሌዎቹ ፊት አዲስ ቅኔ ዘመሩ፤ ከምድርም ከተዋጁት ከመቶ አርባ አራት ሺህ በቀር ያን ቅኔ ሊማር ለማንም አልተቻለውም።
⁴ ከሴቶች ጋር ያልረከሱ እነዚህ ናቸው፥ ድንግሎች ናቸውና። በጉ ወደሚሄድበት የሚከተሉት እነዚህ ናቸው። ለእግዚአብሔርና ለበጉ በኵራት እንዲሆኑ ከሰዎች የተዋጁ እነዚህ ናቸው።
⁵ በአፋቸውም ውሸት አልተገኘም፤ ነውር የለባቸውም።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 4
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁹ ጴጥሮስና ዮሐንስ ግን መልሰው፦ እግዚአብሔርን ከመስማት ይልቅ እናንተን እንሰማ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት የሚገባ እንደ ሆነ ቍረጡ፤
²⁰ እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ዝም ማለት አንችልም አሉአቸው።
²¹ እነርሱም እንደ ምን እንደሚቀጡ ምክንያት ስላላገኙባቸው፥ እንደ ገና ዝተው ከሕዝቡ የተነሣ ፈቱአቸው፤ ሰዎች ሁሉ ስለ ሆነው ነገር እግዚአብሔርን ያከብሩ ነበርና።
²² ይህ የመፈወስ ምልክት የተደረገለት ሰው ከአርባ ዓመት ይበልጠው ነበርና።
²³ ተፈትተውም ወደ ወገኖቻቸው መጡና የካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች ያሉአቸውን ሁሉ ነገሩአቸው።
²⁴ እነርሱም በሰሙ ጊዜ በአንድ ልብ ሆነው ወደ እግዚአብሔር ድምፃቸውን ከፍ አደረጉ እንዲህም አሉ፦ ጌታ ሆይ፥ አንተ ሰማዩንና ምድሩን ባሕሩንም በእነርሱም የሚኖረውን ሁሉ የፈጠርህ፥
²⁵ በመንፈስ ቅዱስም በብላቴናህ በአባታችን በዳዊት አፍ፦ አሕዛብ ለምን አጕረመረሙ? ሕዝቡስ ከንቱን ነገር ለምን አሰቡ?
²⁶ የምድር ነገሥታት ተነሡ አለቆችም በጌታና በተቀባው ላይ አብረው ተከማቹ ብለህ የተናገርህ አምላክ ነህ።
²⁷-²⁸ በቀባኸው በቅዱሱ ብላቴናህ በኢየሱስ ላይ ሄሮድስና ጴንጤናዊው ጲላጦስ ከአሕዛብና ከእስራኤል ሕዝብ ጋር፥ እጅህና አሳብህ እንዲሆን አስቀድመው የወሰኑትን ሁሉ ሊፈጽሙ፥ በዚች ከተማ በእውነት ተሰበሰቡ።
²⁹-³⁰ አሁንም፥ ጌታ ሆይ፥ ወደ ዛቻቸው ተመልከት፤ ለመፈወስም እጅህን ስትዘረጋ በቅዱስ ብላቴናህም በኢየሱስ ስም ምልክትና ድንቅ ሲደረግ፥ ባሪያዎችህ በፍጹም ግልጥነት ቃልህን እንዲናገሩ ስጣቸው።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጥቅምት_16_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇🌹

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ጻድቅሰ ከመ በቀልት ይፈሪ። ወይበዝኅ ከመ ዘግባ ዘሊባኖስ። ትኩላን እሙንቱ ውስተ ቤተ #እግዚአብሔር"። መዝ 91፥12-13።

#ትርጉም፦ "ጻድቅ እንደ ዘንባባ ያፈራል፥ እንደ ሊባኖስ ዝግባም ያድጋል። በ #እግዚአብሔር ቤት ውስጥ ተተክለዋል፥ በአምላካችንም አደባባይ ውስጥ ይበቅላሉ"። መዝ 91፥12-13።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጥቅምት_16_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማቴዎስ 12
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ በዚያን ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ በሰንበት ቀን በእርሻ መካከል አለፈ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተራቡና እሸት ይቀጥፉ ይበሉም ጀመር።
² ፈሪሳውያንም አይተው፦ እነሆ፥ ደቀ መዛሙርትህ በሰንበት ማድረግ ያልተፈቀደውን ያደርጋሉ አሉት።
³-⁴ እርሱ ግን እንዲህ አላቸው፦ ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት በተራቡ ጊዜ፥ እርሱ ያደረገውን፥ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንደ ገባ ካህናትም ብቻ እንጂ እርሱና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሊበሉት ያልተፈቀደውን የመሥዋዕቱን ኅብስት እንደ በላ አላነበባችሁምን?
⁵ ካህናትም በሰንበት በመቅደስ ሰንበትን እንዲያረክሱ ኃጢአትም እንዳይሆንባቸው በሕጉ አላነበባችሁምን?
⁶ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ከመቅደስ የሚበልጥ ከዚህ አለ።
⁷ ምሕረትን እወዳለሁ መሥዋዕትንም አይደለም ያለው ምን እንደሆነ ብታውቁስ ኃጢአት የሌለባቸውን ባልኰነናችሁም ነበር።
⁸ የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነውና።
⁹ ከዚያም አልፎ ወደ ምኩራባቸው ገባ።
¹⁰ እነሆም፥ እጁ የሰለለች ሰው ነበረ፤ ይከሱትም ዘንድ። በሰንበት መፈወስ ተፈቅዶአልን? ብለው ጠየቁት።
¹¹ እርሱ ግን፦ ከእናንተ አንድ በግ ያለው በሰንበት በጉድጓድ ቢወድቅበት፥ ይዞ የማያወጣው ሰው ማን ነው?
¹² እንግዲህ ሰው ከበግ ይልቅ እንደምን አይበልጥም! ስለዚህ በሰንበት መልካም መሥራት ተፈቅዶአል አላቸው።
¹³ ከዚያም በኋላ ሰውየውን፦ እጅህን ዘርጋ አለው። ዘረጋትም፥ እንደ ሁለተኛይቱም ደህና ሆነች።
¹⁴ ፈሪሳውያን ግን ወጥተው እንዴት አድርገው እንዲያጠፉት ተማከሩበት።
¹⁵ ጌታችን ኢየሱስም አውቆ ከዚያ ፈቀቅ አለ። ብዙ ሰዎችም ተከተሉት፥ ሁሉንም ፈወሳቸው፥ እንዳይገልጡትም አዘዛቸው፤
¹⁶-¹⁷ በነቢዩ በኢሳይያስ የተባለው ይፈጸም ዘንድ እንዲህ ሲል፦
¹⁸ እነሆ የመረጥሁት ብላቴናዬ፥ ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ወዳጄ፤ መንፈሴን በእርሱ ላይ አኖራለሁ፥ ፍርድንም ለአሕዛብ ያወራል።
¹⁹ አይከራከርም አይጮህምም፥ ድምፁንም በአደባባይ የሚሰማ የለም።
²⁰ ፍርድን ድል ለመንሣት እስኪያወጣ፥ የተቀጠቀጠን ሸምበቆ አይሰብርም የሚጤስን የጥዋፍ ክርም አያጠፋም።
²¹ አሕዛብም በስሙ ተስፋ ያደርጋሉ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️ 🌹
የሚቀደሰው ቅዳሴ የእመቤታችን የ #ማርያም_ቅዳሴ ነው። መልካም በዓል፣ ዕለተ ሰንበት፣ የማኅሌተ ጽጌ ሦስተኛ ሳምንትና የጾም ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።
🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ጥቅምት_17

#አንድ_አምላክ_በሆነ_በአብ_በወልድ_በመንፈስ_ቅዱስ ስም
ጥቅምት አስራ ሰባት በዚችም ዕለት የዲያቆናት አለቃ #ቅዱስ_እስጢፋኖስ ለተሾመባት ቀን መታሰቢያ ነው፣ የታላቁ ነቢይና ካህን ሳሙኤል እናት #ቅድስት_ነቢይት_ሐና የተወለደችበት ነው፣ ኤጲስቆጶስ #ቅዱስ_ፊልያስ በሰማዕትነት ያረፈበት ነው፣ የከበረ #ቅዱስ_ጎርጎርዮስ_ዘኑሲስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው፣ ሊቀ ጳጳሳት #ቅዱስ_ዲዮስቆሮስ_ካልዕ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቀዳሜ_ሰማዕት_ቅዱስ_እስጢፋኖስ

ጥቅምት አስራ ሰባት በዚችም ዕለት የዲያቆናት አለቃ የሰማዕታት መጀመሪያ የሆነ የከበረ እስጢፋኖስ ለተሾመባት ቀን መታሰቢያ ናት።

ለዚህም ለከበረ እስጢፋኖስ የ #እግዚአብሔርን ኃይልና ጸጋ የተመላ ሰው እንደነበረና በሕዝቡም መካከል ታላላቅ ተአምራትንና ድንቅ ሥራን ይሠራ እንደነበረ የሐዋርያት ሥራ የተባለ መጽሐፍ ስለርሱ ምስክር ሆነ።

ከዚህም በኋላ አይሁድ ቀኑበት የሐሰት ምስክሮች የሚሆኑ ሰዎችንም አስነሡበት ይህን ሰው በሙሴና በ #እግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃልን ሲናገር ሰምተነዋል እንዲሉ ሐሰትን አስተማሩአቸው። ሕዝቡንና ሽማግሌዎችን ጸሐፊዎችንም አነሣሡአቸው አዳርሱን ብለው ከበው እየጐተቱ ወደ ሸንጎ ወሰዱት።

የሐሰት ምስክሮችንም አቆሙበት እነርሱም ይህ ሰው በቤተ መቅደስ ላይ በኦሪትም ላይ ስድብን ሲናገር ተው ብንለው እምቢ አለ። የናዝሬቱ #ኢየሱስ ቤተ መቅደሳችሁን ያፈርሰዋል ሙሴ የሰጣችሁን ኦሪታችሁንም ይሽራል ሲል ሰምተነዋል አሉ።

በአደባባይ ተቀምጠው የነበሩት ሁሉ ተመለከቱት ፊቱንም የ #እግዚአብሔርን መልአክ ፊት ሁኖ አዩት። ሊቀ ካህናቱም እውነት ነውን እንዲህ አልክ አለው። እርሱም እንዲህ አለ ወንድሞቻችንና አባቶቻችን ስሙ ወደ ካራን ከመምጣቱ አስቀድሞ በሶርያ ወንዞች መካከል ሳለ ለአባታችን ለአብርሃም የክብር ባለቤት #እግዚአብሔር ተገለጠለት። ካገርህ ውጣ ከዘመዶችህም ተለይ እኔ ወደማሳይህ ሀገርም ና አለው።

ከዚህም በኋላ ከከላውዴዎን ወጥቶ በካራን ተቀመጠ አባቱም ከሞተ በኋላ ዛሬ እናንተ ወደ አላችሁባት ወደዚች አገር አመጣው። ከዚህም በኋላ የግዝረትን ሥርዓት ሰጠው ይስሐቅንም በወለደው ጊዜ በስምንተኛው ቀን ገዘረው እንዲሁ ይስሐቅም ያዕቆብን ገዘረው ያዕቆብም ዐሥራ ሁለቱን ነገድ አባቶችን ገዘረ።

የቀደሙ አባቶቻችንም በዮሴፍ ላይ ቀንተው ወደ ግብጽ አገር ሸጡት #እግዚአብሔር ግን አብሮት ነበር። ከመከራው ሁሉ አዳነው በግብጽ ንጉሥ በፈርዖን ፊትም ዕውቀትን መወደድን ሰጠው በግብጽ አገር ሁሉና በቤቱ ሁሉ ላይ ሾመው። ነገርም በማስረዘም በሰሎሞን እጅ እስከተሠራችው ቤተ መቅደስ ያለውን ተረከላቸው።

ከዚህም በኋላ ድምፁን ከፍ ከፍ አድርጎ እናንተም እንደ አባቶቻችሁ ዘወትር #መንፈስ_ቅዱስን የምታሳዝኑት ዐይነ ልቡናችሁ የታወረ ዕዝነ ልቡናችሁ የደነቈረ አንገተ ደንዳኖች አላቸው። አባቶቻችሁ ከነቢያት ያላሳደዱት ያልገደሉት ማን አለ እናንተ ክዳችሁ የገደላችሁትን የአምላክን መምጣት አስቀድመው የነገሩዋችሁን ገደላችኋቸው።

በመላእክት ሥርዓት ኦሪትን ተቀብላችሁ አልጠበቃችሁም። ይህንንም ሰምተው ተበሳጩ ልባቸውም ተናደደ ተነሣሣ ጥርሳቸውንም አፋጩበት። በእስጢፋኖስም #መንፈስ_ቅዱስ አደረበት ሰማይም ተከፍቶ #ኢየሱስ_በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ የ #እግዚአብሔርን ክብር አየ። እነሆ ሰማይ ተከፍቶ የሰው ልጅም በ #እግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ አያለሁ አለ።

ጆሮአቸውን ይዘው በታላቅ ድምፅ ጮኹ በአንድነትም ከበው ጐተቱት። እየጐተቱም ከከተማ ወደ ውጭ አውጥተው በደንጊያ ወግረው ገደሉት የገደሉትም ሰዎች ልብሳቸውን ሳውል ለሚባል ጐልማሳ ልጅ ያስጠብቁ ነበር። #ጌታዬ_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሆይ ነፍሴን ተቀበል እያለ ሲጸልይ እስጢፋኖስን በደንጊያ ወገሩት።

ዘለፍለፍ ባለ ጊዜም ድምፁን ከፍ አድርጎ አቤቱ ይህን ኃጢአታቸውን ይቅር በላቸው በደልም አታድርግባቸው ይህንንም ብሎ አረፈ። ደጋግ ሰዎችም መጥተው የእስጢፋኖስን ሥጋ ወስደው ቀበሩት ታላቅ ልቅሶም አለቀሱለት።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በሰማዕቱ ቅዱስ እስጢፋኖስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ነቢይት_ሐና

ዳግመኛም በዚህች ቀን የታላቁ ነቢይና ካህን ሳሙኤል እናት ቅድስት ነቢይት ሐና ተወለደች።

ይችም ቅድስት ከሌዊ ነገድ ናት የታኅርም ልጅ ሕልቃና አገባት ፍናና የምትባልም ሌላ ሚስት አለችው እርሷም ወላድ በመሆኗ ሐና ልጅ ስለሌላት መካንም ስለሆነች ሁልጊዜ ትገዳደራት ነበር።

ሐና ግን ፈጽማ በማዘን አትበላም አትጠጣም ባሏ ሕልቃናም ያረጋጋታል ማረጋጋቱንም አልተቀበለችውም በሊቀ ካህናቱ በኤሊ ዘመንም ወደ ቤተ #እግዚአብሔር ወጣች እያለቀሰችና እያዘነች በ #እግዚአብሔር ፊት ጸለየች እንዲህም ብላ ስለትን ተሳለች አቤቱ ልጅ የሰጠኸኝ እንደሆነ በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ለአንተ የሚያገለግል አደርገዋለሁ።

ካህኑ ኤሊም አያትና እርሷ የወይን ጠጅ ጠጥታ እንደ ሰከረች አሰበ እርሷ በዝምታ በልቧ ትጸልይ ነበርና በቊጣና በግሣጼ የወይን ጠጅ ጠጥተሽ ወደዚህ ወደ #እግዚአብሔር ቤት ለምን መጣሽ አሁን ሒጂ ስካርሺን በእንቅልፍ አስወግጂ አላት።

እርሷም እንዲህ አለችው የወይን ጠጅ ከቶ አልጠጣሁም ልጅ ያጣሁ በመሆኔ በልቤ አዝናለሁ እንጂ ካህን ኤሊም አጽናናት እንዲሁም ብሎ ባረካት የእስራኤል ፈጣሪ የለመንሽውን ይስጥሽ በሰላም ሒጂ በቃሉም አምና ወደ ቤቷ ገባች።

ከዚህም በኋላ ፀንሳ ወንድ ልጅን ወለደች ስሙንም ሳሙኤል ብላ ጠራችው። ጡትንም በአስጣለችው ጊዜ ወደ #እግዚአብሔር ቤት ይዛው ወጣች ወደ ካህን ኤሊም አቀረበችውና እንዲህ ብላ አስረዳችው ከአሁን በፊት ልጅን ይሰጠኝ ዘንድ ወደ #እግዚአብሔር ስጸልይና ስለምን ያየኸኝ ሴት ነኝ ልመናዬንም ሰምቶ ይህን ልጅ ሰጠኝ አሁንም በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ለ #እግዚአብሔር አገልጋይ ይሆን ዘንድ አመጣሁት።

ከዚህም በኋላ ሐና #እግዚአብሔርን አመሰገነችው። ልቤ በ #እግዚአብሔር አምኖ ጸና የሚለውን ጸሎትና ትንቢት እስከ መጨረሻው ተናገረች። ይቺም በዳዊት መዝሙር መጨረሻ ከሙሴ መኀልይ ቀጥላ ተጽፋለች።

ከዚህም በኋላ #እግዚአብሔርን አገልግላ በሰላም ጥቅምት 6 አርፋለች።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅድስቷ ጸሎት ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ፊልያስ_ሰማዕት

ዳግመኛም በዚች ቀን የሀገረ ቀምስ ኤጲስቆጶስ ቅዱስ ፊልያስ በሰማዕትነት አረፈ። ይህንንም ቅዱስ በመኰንኑ ቊልቊልያኖስ ዘመን ወደ ፍርድ አደባባይ አቀረቡት ቊልቊልያኖስም ለአማልክት ሠዋ አለው። ፊልያስም እኔ ከብቻው #እግዚአብሔር በቀር ለአማልክት አልሠዋም አለ። ቊልቊልያኖስም #እግዚአብሔር ምን አይነት መሥዋዕት ይሻል አለ ቅዱስ ፊልያስም ቅን ትሑት የሆነ ንጹሕ ልቡናን ዕውነተኛ ፍርድን ቁም ነገርን እንዲህ ያለ መሥዋዕትን #እግዚአብሔር ይወዳል አለው።

ቊልቊልያኖስም የምትጋደል ስለ ነፍስ ነው ወይስ ስለ ሥጋ አለ ቅዱስ ፊልያስም ስለ ነፍስና ስለ ሥጋ ነው እነርሱ በአንድነት ይነሣሉና አለ። ቊልቊልያኖስም የምትወዳት ሚስት የምትወዳቸው ልጆች ወይም ወንድምና ዘመድ አለህን አለው ቅዱስ ፊልያስም ከሁሉም የ #እግዚአብሔር ፍቅር ይበልጣል አለ።
ቊልቊልያኖስም #እግዚአብሔር ከበጎ ሥራ የሠራው ምንድን ነው አለ ቅዱስ ፊልያስም #እግዚአብሔር ያደረገልን ይህ ነው ሰማይና ምድርን በውስጣቸው ያሉትን ሁሉ ፈጠረልን። ዳግመኛም ከጠላታችን ከሰይጣን እጅ ያድነን ዘንድ ከሰማያት ወርዶ ከቅድስት #ድንግል_ማርያም ሰው ሁኖ ተወለደ የሕይወት መንገድንም በዓለም ውስጥ ተመላልሶ አስተማረ መከራንም በሥጋው ተቀብሎ ተሰቅሎ ሞተ በሦስተኛውም ቀን ተነሥቶ በአርባ ቀን ዐረገ ዳግመኛም ለፍርድ ይመጣል ይህን ሁሉ ስለ እኛ አደረገ።

ቊልቊልያኖስም አምላክ ይሰቀላልን ይሞታልን አለ ቅዱስ ፊልያስም አዎን የዘላለም ሕይወትን ይሰጠን ዘንድ ስለ እኛ ፍቅር ሞተ አለው።

ቊልቊልያኖስም እንዲህ አለው እኔ እንዳከበርኩህ ልጣላህም እንዳልፈለግሁ አላወቅህምን አንተ በወገን የከበርክ እንደሆንክ አውቃለሁና አሁንም ለአማልክት ሠዋ በክፉ አሟሟት እንዳትሞት አለው። ቅዱስ ፊልያስም እኔን ደስ ማሰኘት ከወደድክ እንዲያሰቃዩኝና እንዲገድሉኝ እዘዝ አለው በዚያንም ጊዜ በሰይፍ ራሱን እንዲቆርጡት አዘዘ።

ሊገድሉት ሲወስዱትም ዘመዶቹና የሀገር ታላላቆች ወደርሱ መጡ ለመኰንኑም በመታዘዝ ለአማልክት እንዲሠዋ እጆቹን እግሮቹን እየሳሙ ለመኑት። እርሱ ግን የ #ጌታዬ_ኢየሱስ_ክርስቶስን መከራ #መስቀልን ልሸከም እሔዳለሁና እናንተ አሳሳቾች ከእኔ ወግዱ ብሎ ገሠጻቸው።

ከሚገድሉበትም ሲደርስ ፊቱን ወደ ምሥራቅ መልሶ እጆቹን ዘርግቶ ክብር ይግባውና ወደ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ጸለየ ሕዝቡን አደራ ወደ #ጌታ አስጠበቀና ተሰናበተ ከዚህም በኋላ ራሱን ቆረጡት የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀበለ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ መስተጋድል አባት ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ታላቁ_ሊቅ_ቅዱስ_ጎርጎርዮስ_ዘኑሲስ

በዚችም ዕለት የኑሲስ ኤጲስቆጶስ የባስልዮስ ወንድም የከበረ ጎርጎርዮስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው።

ይህም ቅዱስ ጎርጎርዮስ እጅግ የተማረ አዋቂ ነበረ በደሴቶችም ላይ ኤጲስቆጶስነት ተሾመ እነሆ በዚህ ወር በአሥራ አምስት ቀን የሆነውን ከገድሉ ጥቂት እንጽፋለን። ስለርሱም እንዲህ ተባለ እርሱ መሥዋዕቱን ለማክበር በሚቀድስ ጊዜ በመሠዊያው ላይ ሲወርድ #መንፈስ_ቅዱስን የሚያየው ሆነ ከዚህም በኋላ ቅዱስ ኪሩብን አየው በደረቱም ውስጥ አቀፈው በመሠዊያውም ላይ ሳለ ወደ ዝምታና ተደሞ አደረሰው ሰዎችም ሁሉ ሥጋዊ እንቅልፍ የሚያንቀላፋ ይመስላቸው ነበር።

በኤጲስቆጶስነት ሹመት ሠላሳ ሦስት ዘመናት በተፈጸሙለት ጊዜ ወንድሙ ቅዱስ ባስልዮስ ሊጠይቀው መጣ እርሱ ከተጋድሎ ብዛት የተነሣ በጽኑ ደዌ የሚታመም ሁኖ ነበርና በቅዱስ ባስልዮስ መምጣት ደስ አለው።

ቅዱስ ጎርጎርዮስም እንደ ልማዱ ሊቀድስ ወደ መሠዊያው በወጣ ጊዜ የከበረች ድንግል እመቤታችን #ማርያም ተገለጸችለትና ዛሬ ወደኔ ትመጣለህ አለችው የቊርባኑንም ቅዳሴ ሲጨርስ ሕዝቡ በቀናች ሃይማኖት ጸንተው እንዲኖሩ ይመክራቸውና ያስተምራቸው ዘንድ ወንድሙን ባስልዮስን ለመነው እርሱም እንደሚያንቀላፋ ሆነ በቀሰቀሱትም ጊዜ ሙቶ አገኙት ቅዱስ ባስልዮስም ሣጥን እንዲሠሩለት አዘዛቸው። ጸሎታትንም በመጸለይ መዝሙራትንም በመዘመር በማመስገንም እንደሚገባ ገንዞ በመቃብር ውስጥ አኖሩት።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሱ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ትኑር ለዘላለሙ አሜን

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ዲዮስቆሮስ_ካልዕ

በዚችም ቀን ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሠላሳ አንደኛ የሆነ የእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አባት ዲዮስቆሮስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው ። ይህም አባት በዘመኑ ካሉ ትውልድ እርሱን የሚመስል ያልተገኘ በጠባዩ ቅን የዋህ በእውቀቱ አስተዋይ በበጎ ሥራው ፍጹም የሆነ ነው።

#መንፈስ_ቅዱስ ፈቃድ ሊቀ ጵጵስና በተሾመ ጊዜ መልእክትን ጽፎ ወደ አንጾኪያ ሊቀ ጳጰሳት ቅዱስ ሳዊሮስ ላካት ። እርሱም ልዩ ሦስት የሆኑ #ሥላሴ በመለኮት አንድ እንደሆኑ እየገለጠና እያሳሰበ ነው። ስለ ወልደ #እግዚአብሔርም ሰው መሆን እርሱ ፍጹም ሥጋን ነባቢትና ለባዊት ነፍስን ከእመቤታችን ከቅድስት #ድንግል_ማርያም እንደ ነሣ በመለኮቱና በትስብእቱም አካል ያለው አንድ ልጅ እንደሆነ ከተዋሕዶውም በኋላ በሥራው ሁሉ የማይለያይ ጭማሪ ወይም ጉድለት የሌለው ነው።

መልእክቱም ወደ ቅዱስ አባት ሳዊሮስ በደረሰች ጊዜ አነበባትና ፈጽሞ ደስ ተሰኘባት ለአንጾኪያም ሕዝብ አስተማረባት ሁሉም ደስ አለቸው።

ከዚህም በኋላ አባ ሳዊሮስ ለአባ ዲዮስቆሮስ የመልእክቱን መልስ እንዲህ ብሎ ጻፈ ። በኒቅያ ከተማ ተሰብስበው ሃይማኖታቸው የቀና ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንቱ ቅዱሳን አባቶቻችን በቀናች ሃይማኖት አጽንተው የሠሩዋትን ቤተ ክርስቲያኑን እንድትጠብቅ ለዚች ለከበረች አገልግሎት የመረጠህ #እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ። ዳግመኛም በዚሁ እንዲጸና ወደ ቀኝም ወደ ግራም ፈቀቅ እንዳይል አስገነዘበው ደግሞም በቀናች ሃይማኖት እንዲጸኑ ሕዝቡን ሁል ጊዜ አስተምራቸው አለው።

የአባ ሳዊሮስም መልእክት ወደ አባ ዲዮስቆሮስ በደረሰች ጊዜ ደስ ተሰኘባት በሁሉ ቦታም እንዲአስተምሩባት አዘዘ ይህም አባት ሕዝቡን ሁል ጊዜ የሚያስተምራቸው ሆነ። ሁል ጊዜም ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ ያስተምራቸዋል ኤጲስቆጶሳቱንና ካህናቱንም መንጋዎቻቸውን ስለ መጠበቅ ያዛቸዋል መልካም አገልግሎቱንም አድርሶ #እግዚአብሔርንም ደስ አሰኝቶ አረፈ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ትድረሰን ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት_17)
🌹#የጥቅምት_17_ግጻዌ🌹

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ጥቅምት_17_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
2ኛ ጢሞቴዎስ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
³ ሌትና ቀን በልመናዬ ሳላቋርጥ ስለማስብህ እንደ አባቶቼ አድርጌ በንጹሕ ሕሊና የማመልከውን እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፤
⁴ እንባህን እያሰብሁ በደስታ እሞላ ዘንድ ላይህ እናፍቃለሁ።
⁵ በአንተ ያለውን ግብዝነት የሌለበትን እምነትህን አስባለሁ፤ ይህም እምነት ቀድሞ በአያትህ በሎይድ በእናትህም በኤውንቄ ነበረባቸው፥ በአንተም ደግሞ እንዳለ ተረድቼአለሁ።
⁶ ስለዚህ ምክንያት፥ እሳት እንደሚያቀጣጥል ሰው፥ እጆቼን በመጫኔ በአንተ ያለውን የእግዚአብሔርን ስጦታ እንድታነሣሣ አሳስብሃለሁ።
⁷ እግዚአብሔር የኃይልና የፍቅር ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንምና።
⁸ እንግዲህ በጌታችን ምስክርነት ወይም በእስረኛው በእኔ አትፈር፥ ነገር ግን እንደ እግዚአብሔር ኃይል መጠን ስለ ወንጌል አብረኸኝ መከራን ተቀበል፤
⁹ ያዳነን በቅዱስም አጠራር የጠራን እግዚአብሔር ነውና፥ ይህም እንደ ራሱ አሳብና ጸጋ መጠን ነው እንጂ እንደ ሥራችን መጠን አይደለም፤ ይህም ጸጋ ከዘላለም ዘመናት በፊት በክርስቶስ ኢየሱስ ተሰጠን፥
¹⁰-¹¹ አሁን ግን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ ታይቶአል። እርሱ ሞትን ሽሮአልና እኔ ሰባኪና ሐዋርያ አሕዛብንም አስተማሪ እንድሆን በተሾምሁበት በወንጌል ሕይወትንና አለመጥፋትን ወደ ብርሃን አውጥቶአል።
¹² ስለዚህም ምክንያት ይህን መከራ ደግሞ ተቀብዬአለሁ፥ ነገር ግን አላፍርበትም፤ ያመንሁትን አውቃለሁና፥ የሰጠሁትንም አደራ እስከዚያ ቀን ድረስ ሊጠብቅ እንዲችል ተረድቼአለሁ።
¹³ በክርስቶስ ኢየሱስ ባለ እምነትና ፍቅር አድርገህ፥ ከእኔ የሰማኸውን ጤናማ ቃል ምሳሌ ያዝ፤
¹⁴ መልካሙን አደራ በእኛ በሚኖረው በመንፈስ ቅዱስ ጠብቅ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጴጥሮስ 5
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
² በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ ሳይሆን፥ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘት ሳይሆን ጐብኙት፤
³ ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ማኅበሮቻችሁን በኃይል አትግዙ፤
⁴ የእረኞችም አለቃ በሚገለጥበት ጊዜ የማያልፈውን የክብርን አክሊል ትቀበላላችሁ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 7
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁵⁴ ይህንም በሰሙ ጊዜ በልባቸው በጣም ተቈጡ ጥርሳቸውንም አፋጩበት።
⁵⁵ መንፈስ ቅዱስንም ተሞልቶ ወደ ሰማይ ትኵር ብሎ ሲመለከት የእግዚአብሔርን ክብር ኢየሱስንም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየና፦
⁵⁶ እነሆ፥ ሰማያት ተከፍተው የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ አለ።
⁵⁷ በታላቅ ድምፅም እየጮኹ ጆሮአቸውን ደፈኑ፥ በአንድ ልብ ሆነውም ወደ እርሱ ሮጡ፥
⁵⁸ ከከተማም ወደ ውጭ አውጥተው ወገሩት። ምስክሮችም ልብሳቸውን ሳውል በሚሉት በአንድ ጎበዝ እግር አጠገብ አኖሩ።
⁵⁹ እስጢፋኖስም፦ ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ ነፍሴን ተቀበል ብሎ ሲጠራ ይወግሩት ነበር።
⁶⁰ ተንበርክኮም፦ ጌታ ሆይ፥ ይህን ኃጢአት አትቍጠርባቸው ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ይህንም ብሎ አንቀላፋ፦ ሳውልም በእርሱ መገደል ተስማምቶ ነበር።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጥቅምት_17_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇🌹

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
   "ወጽንሐሐኒ ኢትሠምር። መሥዋዕቱ ለ #እግዚአብሔር መንፈስ የዋህ። ልበ ትሑተ ወየዋሃ ኢይሜንን #እግዚአብሔር"። መዝ. 50፥17

#ትርጉም፦ "የ #እግዚአብሔር መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፥ የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ #እግዚአብሔር አይንቅም"።

ወይም👇

"ልበ ንጹሕ ፍጥር ሊተ እግዚኦ። መንፈሰ ርቱዕ ሐዲስ ውስተ ከርሥየ። ኢትግድፈኒ እምቅድመ ገጽከ"። መዝ.50÷10

#ትርጉም፦ "አቤቱ፥ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ፥ የቀናውንም መንፈስ በውስጤ አድስ። ከፊትህ አትጣለኝ፥ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድብኝ"። መዝ.50÷10
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጥቅምት_17_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሉቃስ 21
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ዓይኑንም አንሥቶ መባቸውን በመዝገብ የሚጥሉ ባለ ጠጎችን አየ።
² አንዲትም ድሀ መበለት ሁለት ሳንቲም በዚያ ስትጥል አየና፦
³ እውነት እላችኋለሁ፥ ይህች ድሀ መበለት ከሁሉ ይልቅ አብልጣ ጣለች፤
⁴ እነዚህ ሁሉ ከትርፋቸው ወደ እግዚአብሔር መዝገብ ጥለዋልና፤ ይህች ግን ከጕድለትዋ የነበራትን ትዳርዋን ሁሉ ጣለች አለ።
⁵ አንዳንዶቹም ስለ መቅደስ በመልካም ድንጋይና በተሰጠው ሽልማት እንዳጌጠ ሲነጋገሩ፦ ይህማ የምታዩት ሁሉ፥
⁶ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ የማይቀርበት ዘመን ይመጣል አለ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️  🌹
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ቅዱስ_ዮሐንስ_ወልደ_ነጎድጓድ_ቅዳሴ ነው። መልካም የቅዱስ እስጢፋስ የሢመት በዓል፣ የጾም ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።
🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"እንደ ቀራጩ ሁን፤ ከፈሪሳዊው ጋር አብረህ እንዳትኮነን፤ የሙሴን ትሕትና ምረጥ፣ ጠጣሩና ዐለቱ ልብህ ወደ ውኃ ምንጭ ሲለወጥ ታገኘዋለህና"።

#እማሆይ_ሲንቅለጢቃ
#ጥቅምት_18

#አንድ_አምላክ_በሆነ_በአብ_በወልድ_በመንፈስ_ቅዱስ ስም
ጥቅምት አሥራ ስምንት ቀን የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት #ቅዱስ_ቴዎፍሎስ ያረፈበት፣ የከበረ #ቅዱስ_ሮማኖስ በሰማዕትነት ያረፈበት ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ቴዎፍሎስ

ጥቅምት አሥራ ስምንት በዚህች ቀን ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሃያ ሦስተኛ የሆነ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት የከበረ አባት ቴዎፍሎስ አረፈ። ይህም አባት ንጉሥ ቴዎዶስዮስ በነገሠ በስድስተኛ ዓመት ተሾመ በወንጌላዊ ማርቆስም ወንበር ሃያ ስምንት ዓመት ኖረ።

በዘመኑ ብዙ መጻሕፍትን የተረጎመ ከእሳቸውም የወንጌላዊ ቅዱስ ዮሐንስን ራእይና የሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስን መልእክት የተረጎመ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ተነሣ ዳግመኛም ለደሴተ ቆጵሮስ ኤጲስቆጶስ የሆነ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ነበረ።

በዘመኑም ሰባቱ ደቂቅ ሦስት መቶ ሰባ ሁለት ዓመት ከአንቀላፉ በኋላ ተነሡ። ይህም አባት የሐዋርያዊ ሊቀ ጳጳሳት አባት አትናቴዎስ ደቀ መዝሙር ነው የቤተ ክርስቲያንንም መጻሕፍትና ሥርዓቱን ሁሉ እየተማረ በእርሱ ዘንድ አደገ። ከእርሱ በፊት የነበረ ሊቀ ጳጳሳት አባ ጢሞቴዎስም በአረፈ ጊዜ ይህ አባት በእስክንድርያ አገር ላይ ሊቀ ጵጵስና ተሾመ አዋቂና አስተዋይም ስለሆነ ስለ ፍቅር ስለ ርኅራኄ ከ #ንስሐ በፊት ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ከመቀበል መጠበቅ ስለ ሚገባ ስለ ሙታን መነሣትና ለኃጥአን ስለ ተዘጋጀ ስለዘላለማዊ ሥቃይ ሌሎችም ጠቃሚ የሆኑ ድርሳናትንና ተግሣጻትን ደረሰ።

ቅዱስ ቄርሎስም ለዚህ አባት ቴዎፍሎስ የእኅቱ ልጅ ነው እርሱም በበጎ አስተዳደግ አሳደገው የቤተ ክርስቲያንንም ትምህርት አስተማረው። ከዚያም በኋላ ወደ አባ ሰራብዮን ላከው አባ ሰራብዮንም መንፈሳዊ ተግባርን ሁሉ አስተማረው።

በአትናቴዎስም ዘመን አስቀድሞ እንዲህ ሆነ በጎ ዘመን ባገኝ ይህን ኮረብታ ባስጠረግሁት ነበር። ለከበሩ ለመጥምቁ ዮሐንስና ለነቢይ ኤልሳዕም ቤተ ክርስቲያን በሠራሁም ነበር ሲል ይህ አባት ቴዎፍሎስ አባ አትናቴዎስን ይሰማው ነበር። በሹመቱ ወራትም ይህን ነገር አስታውሶ የሚያዝንና ክብር ይግባውና ወደ #ጌታችን የሚጸልይ ሆነ።

በዚያ ወራትም ባሏ ብዙ ገንዘብ ትቶላት የሞተ አንዲት ባለጸጋ ሴት ከሮሜ አገር መጣች ሁለት ልጆቿም ከእርሷ ጋር አሉ ሊቀ ጳጳሳት አባ ቴዎፍሎስንም ሲያዝን አየችውና ክቡር አባት ሆይ ምን ያሳዝንሐል አለችው። እርሱም ብዙ ወርቅ በዚህ ኮረብታ ውስጥ እያለ ድኆች ይራባሉና አላት እርሷም አንተ ስለ እኔ ጸልይ እኔም አስጠርገዋለሁ አለችው።

ይህንንም ብላ ያን ኮረብታ አስጠረገችው በውስጡም በደንጊያ ሠሌዳ እየአንዳንዱ የተከደኑ ሦስት ሣጥኖች ተገለጡ። በላያቸው ቴዳ ቴዳ ቴዳ የሚል ተጽፎባቸዋል አባ ቴዎፍሎስም በአየው ጊዜ በ #መንፈስ_ቅዱስ ምሥጢራቸውን አውቆ ቴዳ ማለት የ #ጌታ ስም ነው ይህም ለድኆች ይገባል አለ ሁለተኛውም ቴዳ የንጉሥ ቴዎዶስዮስ ነው ሦስተኛውም ቴዳ ቴዎፍሎስ ማለት ነው። የእኔ ገንዘብ ስለሆነ በዚህም አብያተ ክርስቲያናትን እሠራለሁ አለ። እሊህም ሣጥኖች በመቄዶንያዊው ፊልጶስ ልጅ በንጉሥ እስክንድር ዘመን እንደ ተቀበሩ የዘመን ቊጥር ተገኘ እርሱም ሰባት መቶ ዘመናት ነው።

ከዚህም በኋላ ያን የወርቅ ሣጥን ለንጉሥ ቴዎዶስዮስ ላከለት ስለዚያም የወርቅ መዝገብ አስረድቶ ቦታውን መጥቶ እንዲያይ አሳሰበው እርሱም በመርከብ ተጭኖ ወደ እስክንድርያ አገር መጥቶ ሁሉንም አየ የዚያንም ወርቅ እኵሌታ መለሰለት አባ ቴዎፍሎስም ብዙዎች አብያተ ክርስቲያንን ሠራ።

አስቀድሞም በቅዱሳን በመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስና በነቢይ ቅዱስ ኤልሳዕ በስማቸው ቤተ ክርስቲያን ሠራ ሥጋቸውንም ከእስራኤል አገር አፍልሶ አምጥቶ በውስጧ አኖረ እርሷም የታወቀች ናት ዴማስ በሚባል ቦታ ሁለተኛም በእመቤታችን በቅድስት #ድንግል_ማርያም ስም በሀገሩ ምሥራቅ በኩል ሠራ ከዚህም በኋላ በሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል ስም በደሴት ውስጥ ሠራ ሌሎችንም ብዙዎች አብያተ ክርስቲያን አሳነፀ።

ንጉሡም አብያተ ክርስቲያናትን ለመሥራት ያለውን የሊቀ ጳጳሳቱን ፍቅር አይቶ በግብጽ አገር ያሉትን የጣዖታት ቤቶችን ሁሉንም ሰጠው እርሱም ተቀብሎ አፈረሳቸውና በቦታቸው አብያተ ክርስተከያናትንና የእንግዶች ቤቶችን ሠራ ሁለተኛም ምድራቸውን ሁሉ ሰጠው።

ይህም አባት ቴዎፍሎስ የክርስትና ጥምቀትን በሚያጠምቅ ጊዜ የብርሃን በትረ #መስቀል በሚጠመቁት ላይ በ #መስቀል ምልክት ሲያማትብ ያይ ነበር።

ይህ አባት ቴዎፍሎስና ንጉሥ ቴዎዶስዮስ ልጆች በሆኑበት ጊዜ ሁለቱም በአንዲት ሌሊት አንዲት የሆነች ራእይን እነርሱ እንጨቶችን እንደሚለቅሙ አዩ። ከእነርሱም አንዱ ንጉሥ እንደሚሆን ሁለተኛውም ሊቀ ጳጳሳት እንደሚሆን ያቺን ራእይ ተረጎሟት እንዲሁም ሆነ።

ይህም አባት ቴዎፍሎስ ሊቀ ጵጵስና በተሾመባት በመጀመሪያዪቱ ዓመት ንጉሥ ቴዎዶስዮስ ሃይማኖትን እናስተምራለን የሚሉ ሁሉ ሃይማኖታቸውን በመጽሐፍ ጽፈው ወደርሱ እንዲአቀርቡ አዘዛቸው እንዳዘዛቸውም አደረጉ።

ከዚህም በኋላ ንጉሡና ሊቀ ጳጳሳቱ ተነሥተው እነዚያን ጽሑፎች በመሠዊያው ላይ አድርገው ወደ #እግዚአብሔር ጸለዩ #ጌታም_ወልድ በመለኮቱ ከአብ ከ #መንፈስ_ቅዱስ ጋር ትክክል ነው ብሎ ከሚታመን በቀር ከውስጣቸው በቀናች ሃይማኖት የጸና እንደ ሌለ ገለጠላቸው። በዚያንም ጊዜ እሊህን የመና*ፍ*ቃን መጻሕፍትን እንዲአቃጥሏቸው እነዚያንም መና*ፍ*ቃን ከሚገዛው አገር እንዲአሳድዷቸው ንጉሥ አዘዘ።

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም መጻሕፍትን ማንበብና መመርመር ያበዛ ነበር ስለዚህም የአውጋርዮስን መጻሕፍት አወገዘ ያወግዙ ዘንድም ወደ እስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ወደዚህ አባት ወደ ቴዎፍሎስ ወደ ቆጵሮስ ኤጲስቆጶስ ወደ ኤጲፋንዮስ ወደ ኤዺስቆጶሳት ሁሉ በየሀገሩ ላከ። ከዚህም በኋላ መልካም ጒዞውን በፈጸመ ጊዜ #እግዚአብሔርንም አገልግሎ በሰላም አረፈ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ አባት ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

#አርኬ ሰላም ለቴዎፍሎስ ድልወ ዘተረክበ። በመንበረ ማርቆስ ይንበር ድኅረ አትናቴዎስ ሰበከ። በ #መንፈስ_ቅዱስ ሎቱ ከመ አእምሮ ተውህበ። ይሬኢ ለለአሐዱ ለለ ያጠምቅ ሕዝበ። እንዘ በትረ ብርሃን የኅትም ከዊኖ ማዕተበ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#መነኰስ_ቅዱስ_ሮማኖስ

ዳግመኛም በዚህች ቀን ክርስቲያኖችን በአሳደደ በመኰንን አስቅልጵያኖስ ዘመን የከበረ መነኰስ ሮማኖስ በሰማዕትነት አረፈ። ይህም ቅዱስ የክርስቲያን ወገኖችን መኰንኑ እንዳሳደዳቸው በሰማ ጊዜ ከቀሳውስትና ከዲያቆናት ጋር የክርስቲያን ወገኖችን ሁሉ በአንድነት ሰበሰባቸው ስለ #ክርስቶስ ሃይማኖትም መክሮ አጸናቸው።

አስቅልጵያኖስም ይህን ሰምቶ እንዲአመጡት አዘዘ በፊቱም በቆመ ጊዜ አስቅልጵያኖስ በወገን የከበርክ ሮማኖስ አንተ ነህን አለው ቅዱሱም የወገን ክብር ምን ይጠቅመኛል ክብሬ ግን #ክርስቶስ ነው ብሎ መለሰለት። መኰንኑም ሰምቶ እንዲሰቅሉትና ጉንጮቹን ይሰነጣጥቁ ዘንድ አዘዘ ጉንጮቹንም ሲሰነጣጥቁት ምንም አልተናገረምና መኰንኑ ትዕግሥቱን አደነቀ።
በዚያንም ጊዜ ሮማኖስ መኰንኑን እንዲህ አለው እነሆ ስንፍናህን እዘልፍ ዘንድ ፈጣሪዬ አፌን ከፈተ እውነት ነገርን ብታውቅ ለ #እግዚአብሔር እንሰግድ ዘንድ ይገባ እንደሆነ ወይም ለአማልክት እንዲነግረን ሕፃን ልጅ እንዲአመጡ እዘዝ መኰንኑም ታናሽ ሕፃንን እንዲአመጡ አዘዘ መኰንኑም ሕፃኑን ስግደት ለማን እንዲገባ ዕውነቱን ንገረን አለው። ሕፃኑም ልብ የሌለህ ደንቆሮ መኰንን በአንዲት ቃል ዓለሙን ሁሉ ለፈጠረ ለሕያው #እግዚአብሔር ስግደትና አምልኮ እንዲገባ አታውቅምን አለው።

መኰንኑም ሕፃኑን ይሰቅሉት ዘንድ አዘዘ የሕፃኑም እናት ልታየው መጣች ሕፃኑም እናቱን ተጠምቻለሁና ውኃ አጠጭኝ አላት። እናቱም ልጄ ሆይ ከዚህ ውኃ የለም ነገር ግን ወደ ሕይወት ውኃ ሒድ አለችው።

በዚያንም ጊዜ የሕፃኑን ራስ በሰይፍ እንዲቆርጡ የቅዱስ ሮማኖስንም ምላሱን ከግንዱ እንዲቆርጡ መኰንኑ አዘዘ። ያን ጊዜ መኰንኑን ይዘልፍ ዘንድ ለአባ ሮማኖስ ረቂቅ አንደበት ተሰጠው ሲዘልፈውም መኰንኑ ሰምቶ ምላሱ እንዳልተቆረጠ ተጠራጠረ። ወታደሩንም ጠርቶ ምላሱን ያልቆረጥክ ለምንድን ነው አለው ወታደሩም የምላሱን ቁራጭ ያመጡ ዘንድ እዘዝ አለው አምጥተውለትም አይቶ መኰንኑም ወደ ወህኒ ቤት አስገብተው በዚያ አንቀው እንዲገድሉት አዘዘ። እንዲህም ምስክርነቱን ፈጽሞ የምስክርነት አክሊልን በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

#አርኬ ሰላም ለሮማኖስ ሰማዕት #ኢየሱስ ዋሕድ። ምቱረ ልሳን በመጥባህት ወሕሉቀ ካሣድ በእድ። ስመ ዚአሁ አግሀደ ንዑስ ወልድ። እንተ ነበበ ወይቤ እምነ አምልኮ ለባዕድ። ለ #እግዚአብሔር ይደሉ ወትረትዕ ሰጊድ።

ዳግመኛ በዚህች ቀን የቅዱሳን የሰማዕት ቅዱስ ዮሐንስ፣ ቅዱስ አድራኒ፣ ቅዱስ አርቴማዎስ፣ ቅዱስ አርስጦስ፣ ቅዱስ ሉዲኖስ፣ የቅድስት አስማኒትና የሰባቱ ልጆቿ መታሰቢያቸው ነው። ለ #እግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎታቸው ይማረን በረከታቸው ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት_18)
🌹#የጥቅምት_18_ግጻዌ🌹

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ጥቅምት_18_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ቲቶ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁷ ኤጲስ ቆጶስ፥ እንደ እግዚአብሔር መጋቢ፥ የማይነቀፍ ሊሆን ይገባዋልና፤ የማይኮራ፥ የማይቆጣ፥ የማይሰክር፥ የማይጨቃጨቅ፥ ነውረኛ ረብ የማይወድ፥
⁸ ነገር ግን እንግዳ ተቀባይ፥ በጎ የሆነውን ነገር የሚወድ፥ ጠንቃቃ፥ ጻድቅ፥ ቅዱስ፥ ራሱን የሚገዛ ይሁን፤
⁹ ሕይወት በሚገኝበት ትምህርት ደግሞ ሊመክር ተቃዋሚዎቹንም ሊወቅስ ይችል ዘንድ፥ እንደተማረው በታመነ ቃል ይጽና።
¹⁰ የማይታዘዙና ከንቱ የሚናገሩ የሚያታልሉ ይልቁንም ከተገረዙት ወገን የሚሆኑ ብዙ ናቸውና፤
¹¹ እነዚህም ስለ ነውረኛ ረብ የማይገባውን እያስተማሩ ቤቶችን በሞላው ስለ ሚገለብጡ፥ አፋቸውን መዝጋት ይገባል።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጴጥሮስ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁶-⁷ በዚህም እጅግ ደስ ይላችኋል፥ ነገር ግን በእሳት ምንም ቢፈተን ከሚጠፋው ወርቅ ይልቅ አብልጦ የሚከብር የተፈተነ እምነታችሁ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ፥ ለምስጋናና ለክብር ለውዳሴም ይገኝ ዘንድ አሁን ለጥቂት ጊዜ ቢያስፈልግ በልዩ ልዩ ፈተና አዝናችኋል።
⁸-⁹ እርሱንም ሳታዩት ትወዱታላችሁ፤ አሁንም ምንም ባታዩት በእርሱ አምናችሁ፥ የእምነታችሁን ፍፃሜ እርሱም የነፍሳችሁን መዳን እየተቀበላችሁ፥ በማይነገርና ክብር በሞላበት ሐሤት ደስ ይላችኋል።
¹⁰ ለእናንተም ስለሚሰጠው ጸጋ ትንቢት የተናገሩት ነቢያት ስለዚህ መዳን ተግተው እየፈለጉ መረመሩት፤
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 20
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²⁹-³⁰ ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ፥ ደቀ መዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሡ እኔ አውቃለሁ።
³¹ ስለዚህ ሦስት ዓመት ሌሊትና ቀን በእንባ እያንዳንዳችሁን ከመገሠጽ እንዳላቋረጥሁ እያሰባችሁ ትጉ።
³² አሁንም ለእግዚአብሔርና ያንጻችሁ ዘንድ በቅዱሳንም ሁሉ መካከል ርስትን ይሰጣችሁ ዘንድ ለሚችል ለጸጋው ቃል አደራ ሰጥቻችኋለሁ።
³³ ከማንም ብር ወይም ወርቅ ወይም ልብስ አልተመኘሁም፤
³⁴ እነዚህ እጆቼ በሚያስፈልገኝ ነገር ለእኔና ከእኔ ጋር ላሉት እንዳገለገሉ እናንተ ታውቃላችሁ።
³⁵ እንዲሁ እየደከማችሁ ድውዮችን ልትረዱና እርሱ ራሱ፦ ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው እንዳለ የጌታን የኢየሱስን ቃል ልታስቡ ይገባችሁ ዘንድ በሁሉ አሳየኋችሁ።
³⁶ ይህንም ብሎ ተንበርክኮ ከሁላቸው ጋር ጸለየ።
³⁷ ሁሉም እጅግ አለቀሱ፥ ጳውሎስንም አንገቱን አቅፈው ይስሙት ነበር፤
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጥቅምት_18_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇🌹

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ወይረውዩ እምጠለ ቤትከ። ወትሠቅዮሙ እምፈለገ ትፍሥሕትከ። እስመ እምኀቤየ ነቅዐ ሕይወት"። መዝ 35፥8-9

#ትርጉም "ከቤትህ ጠል ይጠጣሉ፥ ከተድላም ፈሳሽ ታጠጣቸዋለህ። የሕይወት ምንጭ ከአንተ ዘንድ ነውና፤ በብርሃንህ ብርሃንን እናያለን"። መዝ 35፥8-9
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጥቅምት_18_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማቴዎስ 22
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁵ ስለዚህ ፈሪሳውያን ሄዱና እንዴት አድርገው በነገር እንዲያጠምዱት ተማከሩ።
¹⁶ ደቀ መዛሙርታቸውንም ከሄሮድስ ወገን ጋር ላኩበት፥ እርሱም፦ መምህር ሆይ፥ እውነተኛ እንደ ሆንህ በእውነትም የእግዚአብሔርን መንገድ እንድታስተምር እናውቃለን፥ ለማንምም አታደላም፥ የሰውን ፊት አትመለከትምና፤
¹⁷ እንግዲህ ምን ይመስልሃል? ንገረን ለቄሣር ግብር መስጠት ተፈቅዶአልን ወይስ አልተፈቀደም? አሉት።
¹⁸ ጌታችን ኢየሱስም ክፋታቸውን አውቆ፦ እናንተ ግብዞች፥ ስለ ምን ትፈትኑኛላችሁ?
¹⁹ የግብሩን ብር አሳዩኝ አለ። እነርሱም ዲናር አመጡለት።
²⁰ እርሱም፦ ይህች መልክ ጽሕፈቲቱስ የማን ናት? አላቸው።
²¹ የቄሣር ነው አሉት። በዚያን ጊዜ፦ እንኪያስ የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ አላቸው።
²² ይህንም ሰምተው ተደነቁ፥ ትተውትም ሄዱ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️ 🌹
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ቅዱስ_ባስልዮስ_ቅዳሴ ነው። መልካም የአቡነ ቴዎፍሎስ እና የቅዱስ ሮማኖስ የዕረፍት በዓልና የጾም ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።
🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
2025/10/27 13:49:37
Back to Top
HTML Embed Code: