Warning: Undefined array key 0 in /var/www/tgoop/function.php on line 65

Warning: Trying to access array offset on value of type null in /var/www/tgoop/function.php on line 65
- Telegram Web
Telegram Web
‹‹የእኛ ልጅ››

+++++++++++++++++++

እሷ ምድር ቤት ትሰራለች፡፡ሬስቶራንቱ ውስጥ። ውዱ ሬስቶራንት ውስጥ። አስተናጋጅ ነች።
እነሱ እላይኛው ፎቅ ላይ ዘና-ፈታ ፣ ሽር ብትን ይላሉ፡፡ ስፓው ውስጥ። ሃብታሞች የሚያዘወትሩት የቅንጦት ስፓ ውስጥ፡፡ ሥራ የላቸውም፡፡


የስፓ ጣጣቸውን ሲጨርሱ ቁንን እያሉ ወደ ሬስቶራንቱ ይወርዳሉ፣ ጥሩ ጥሩ እየሸተቱ፣ እንደ ጸሃይ እያበሩ፡፡ እየተንሳፈፉ ከገቡ በኋላ ሁልጊዜ እሷ በምታስተናግድበት የሬስቶራንቱ ክፍል ይቀመጣሉ፡፡


ይወዷታል፡፡ እንደ ጓደኛ ያወሯታል፡፡



ውድ ቦርሳዎችን ይይዛሉ፤ ገንዘብ ግን አይሸከሙም፡፡ መሸከም የለባቸውም፡፡
አንጸባራቂ ስልኮቻቸው ሁልጊዜም እጆቻው ላይ፣ አረፍ ሲሉ ደግሞ ጠረጴዛው ላይ ናቸው፡፡

ከዚያ ይጠሯትና ያሻቸውን ያዛሉ፡፡
ትእዛዛቸው ደርሶ ፊታቸው ከመቀመጡ ሃሳባቸውን ከቀየሩ ግን ያለማቅማማት ሌላ ነገር ያዛሉ፡፡ የበሉና የጠጡበት ሂሳብ የሚከፈለው ሁሌም አብሯቸው በሌላ ሰው፣ በሩቁ ነው፡፡





አንዳንድ ጊዜ ወደ ስፓው ከመሄዳቸው በፊት ይመጣሉ፡፡

ከመቀመጣቸው ከመካከላቸው አንዷ፣

“ሃኒ፣ ለማኒኪዊር እና ለፔዲኪዊር ገንዘብ ላክልኝ እንጂ- ተጎሳቆልኩ እኮ” ወይም፣
“ውይ አንተ ደግሞ…ሃያ አምስት ሺህ ብር ምን ይራልኛል ብለህ ነው? ምኑን ከምኑ ላደርገው ነው? …ጸጉሬን ስል፣ ጥፍሬን ስል…ኦኬ በቃ ለዛሬ እንደምንም አብቃቃዋለሁ›› ስትል ትሰማለች፡፡

የጠየቁት ገንዘብ ሁሌም ወዲያው እንደሚላክላቸው ታውቃለች ፡፡
ምክንያቱም ሁልጊዜም ሻይ ቡና ብለው ሲጨርሱ እየተሳሳቁ ወደ ስፓው ይወጣሉ፡፡


ለእሷ መልካም ናቸው፡፡ ደህና ቲፕ ይተዉላታል፡፡
አንዳንዴ ደግሞ ‹‹ይህን የመሰለ መልክ ይዘሽ ለምን አስተናጋጅነት ትሰሪያለሽ ›› ይሏታል፡፡ አፍ አውጥተው፣ ‹‹የቆንጆ ከርፋፋ ነሽ››ም ብለዋታል፡፡

ምን ለማለት እንደፈለጉ ታውቃለች ነገር ግን እንዲህ ያለውን ወሬ መቀጠል ስለማትፈልግ ሌላ ነገር አንስታ ታረሳሳቸዋለች፡፡



ማታ ማታ ሲመጡ ያልከፈሉባቸውን ውድ ኮክቴሎች ፉት እያሉ ሬስቶራንቱን እና ጥግ ላይ ያለውን ባር በቀላዋጭ አይኖቻቸው ያስሳሉ።
አንዳንዴ የዚያን ምሽት እራትና መጠጥ ሂሳብ ዛሬ ያዩት ወንድ እንዲከፍልላቸው ሲያባብሉ ታያለች፡፡ ሳይሳካላቸው ቀርቶ አንዱን ያላጠመዱበት ምሽት የለም፡፡
በውበትና አኳሃናቸው የደነዘዘው ተረኛ ወንድ ሌላ እንዳይቀድመው ተቻኩሎ ሂሳባቸውን ጠቅልሎ ይዘጋና የአንዳቸውን ስልክ ቁጥር ለመቀበል ጠጋ ብሎ ያዋራቸዋል፡፡




እሷ…
ደሞዟ አምስት ሺህ ሁለት መቶ ነው። ደህና ቲፕ ስለምታገኝ ኑሮዋን በእሱ ብትደጉምም ሞልቶላት ግን አያውቅም፡፡
አልፎ አልፎ ለመስተንግዶ ተገትራ በቆመችበት እነዚህ ወጣት ቆነጃጅት ሴቶች ለምግብ፣ ለኮክቴል መጠጥ፣ ለጥፍርና የፀጉር ሥራ ብቻ እንደዋዛ በወር የሚጨፈጭፉትን ገንዘብ ታሰላለች።

ልታገኘው ሳይሆን ልታልመው የማትችለው መጠን መሆኑን ስትደርስበት በዚህ ዘመን የሴትነት ክብርን ጠብቆ የመኖር ዋጋ ከፍተኛ ስለመሆኑ ታስባለች፡፡



ለመኖር በመረጡት ጎዳና ሴቶቹ ላይ ላለመፍረድ ትሞክራለች።
ከዚያ የበለጠ ደግሞ በእነሱ ላለመቅናት ትሞክራለች።
ዝም ብላ ማየት ብቻ ነው ምርጫዋ፡፡



አንዳንዴ ግን፣ በተለይ የቸገራት ሰሞን የህሊና ሚዛኗ ሸርተት፣ ገርገጭ ሲል ይሰማታል፡፡
አሳሳቃቸውን፣ አለባበስና አኳሃናቸውን ስትመለከት በኑሮ ያልጎበጠ ቀላል ትከሻቸው ጎልቶ ይታያታል፡፡ ሕይወት ለእነሱ ውብና አጓጊ፣ ቀላልና ሸክም አልባ ሆና ትታያታለች፡፡ የፈለጉት ሁሉ በእጃቸው፣ ያሻቸው ሁሉ በደጃቸው፡፡ እንዲህ ያለ ጭንቀት መኖር ደስ አይልም…?


ስለ የቤት ኪራይ፣ ስለ ሽንኩርትና ቲማቲም፣ ስለ ትራንስፖርት መጨመር አለመጨነቅ ምንኛ ነጻነት የሚያቀዳጅ መታደል ይሆን? ብላ ታስባለች፡፡
ዛሬም ሙሉ፣ ነገም ሙሉ የሆነ ልፋት እና ይሄ አለቀ…ይሄ ተወደደ በማለት የማያሳቅቅ ሕይወት….



--
ፈረቃዋን ጨርሳ ወደ ታክሲው ሰልፍ በምትቀላቀልባቸው በእንዲህ ያሉ ቀናት ምርጫዋ ምን ያህል እንዳጎበጣት ጎልቶ ይሰማታል..


ደግነቱ በማግስቱ ያ ስሜት በትኩስ ‹‹የእኛ ልጅ በርቺ በርቺ እንዳትረቺ›› ይተካና ለአዲስ የለፍቶ አዳሪነት ቀኗ ያቀብላታል፡፡
"ማሬ አትበለኝ"


÷÷÷÷÷÷




ደግሞ የት ልትሄድ ነው ብዬ አላፋጥጥህም፡፡
ዛሬስ የት አመሸህ እያልኩ አልነተርክህም።
ልሰልልህ ብዬ ፣ ስልክህን ከፍቼ እኔ አልበረብርም።
ከእሷ ልፎካከር፣ እሷን ላስንቅ ብዬ ያልለመደብኝን አልቀባባም፡፡
የማላውቅበትን አልሸቀረቀርም፡፡




ለምን ተውከኝ ብዬ አላላዝንም።
እኔን ምረጥ ብዬም አልለማመጥም፡፡

ክህደትህ አቁስሎኝ ጥዬህም አልሄድም ፡፡

….ቢያንስ ዛሬ አልሄድም፡፡



እንዲህ አድርግልኝ
እንደዚህ ሁንልኝ እያልኩ

አላስቸግርህም፡፡


ግን አንዲት ነገር ብቻ ተለመነኝ፡፡


ማሬ አትበለኝ፡፡


ስለ ፈጠረህ ብለህ እንደዚያ ብለህ መጥራትህን ተወኝ፡፡



ምክንያቱም ‹‹ማሬ›› ብለህ ስትጠራኝ…

ማሬ የምትላት ብቸኛዋ ሴት እንዳልሆንኩ አውቃለሁና፣
ለአላፊው አግዳሚዋ እንካችሁ የምትለው የጅምላ ስያሜ መሆኑን እረዳለሁና፣


በዚያ ስም ስትጠራኝ ይከፋኛል፡፡
ማሬ ስትለኝ ሆድ ይብሰኛል፡፡
ታዝሎ የሚሄደው አዛዩን
"ቅርብ ነው "

አሽካሚው ተሽካሚውን
"ቀላል ናት"  ይላል።
---

‹‹ነጻነት እና ድንች በስጋ››


-----
ቀኑ ቅዳሜ ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ ጓዜን ጠቅልዬ ከእናትና አባቴ ቤት ለመኮብለል ስወስን ገና የስምንት አመት ልጅ ነበርኩ።



እናቴ የምፈልገውን ቆንጆ ጫማ አልገዛም ብላ አንዱን አስቀያሚ ግን ‹‹አቻዮ›› የአንበሳ ጫማ ገዝታልኝ መመለሳችን ነበር፡፡

ጫማውን ደጋግሜ ሳየውና ከጓደኛዬ ነጃት ቆንጅዬ ጫማ ጋር ሳወዳድረው ግን ንዴቴ እየጨመረ ሄደና የእናቴ  ነገር በቃኝ፡፡



የጨርቅ ቦርሳዬ ውስጥ ካሉኝ ሁለት ጫማዎቼ አንዱን (አዲሱንና አስቀያሚውን ትቼ)፣ ከሹራቦቼ ሁሉ አስበልጨ የምወዳትን ቀይ ሹራብ፣ ሮዟን ጉርድ ቀሚሴን፣ እና የአማርኛና እንግሊዝኛ ትምህርት ደብተሮቼን መርጬ ከተትኩ።


አዲሱ ሕይወቴን ለመጀመር ከዚህ ውጪ ምን ሊያስፈልገኝ?



ከዚያ ወደ እናቴ ዞር አልኩና ፣
“እማ፣ ከዚህ ቤት ልወጣ ነው” አልኳት።

"እንዴ ምነው..ለምን?" ብላ ጠየቀችኝ፣ ከሳቋ ጋር እየታገለች፡፡

"በቃ አልወድሽም። በጣም ክፉ ሰው ነሽ " ብዬ መለስኩ።


አሁንም ሳቋን ለማፈን ሞከረችና፣

"እሺ፣ ደህና፣ መንገዱን ጨርቅ ያርግልሽ። እኔ ግን ምሳ ላቀርብ ነው" አለችኝ።



ቦርሳዬን አንግቤ ከሳሎን ስወጣ አባቴ ወደ ቤት እየተመለሰ አየሁት፡፡

ወንድሞቼ እና እህቶቼ ከኋላው እንደ ጫጩት ይከተሉታል፡፡

ሁሉም ምን እያደረግኩ እንደሆነ ስነግራቸው በሳቅ ፍርክስክስ አሉ፡፡


አባቴ ሳቁን ሲጨርስ ነጻነቴን በማወጄ ‹‹የእኔ ልጅ አንበሳ›› ብሎ አበረታታኝ፡፡

ቦርሳዬን እንደተሸከምኩ ጥቂት እርምጃዎችን እንደሄድኩ  እናቴ ከቤት ወጣች።

ጠራችኝ፡፡


ዞር አልኩ፡፡

ፊቷ ላይ አንዳች ፈገግታ ይታያል፡፡

ሮጥ ብላ አጠገቤ ደረሰችና ቀኝ እጇን ዘርግታ፤

“መንገድ እኮ በባዶ ሆድ ጥሩ አይደለም፣ ባይሆን ምሳ ብዪና ከዚያ በኋላ መሄድ ይሻልሻል” አለችኝ።


ያለ ማንገራገር ተስማማሁ፡፡

እውነቱን ለመናገር ገና ከመውጣቴ ይከተለኝ የነበረው የወጥ ሽታ ልቤን ለሁለት ከፍሎት ነበር፡፡


ነጻነት ይሻላል ድንች በስጋ ወጥ?



ጠባቧ ሳሎናችን ስገባ የወጡ ጠረን ተቀብሎ እንደሰው አቀፈኝ፡፡

በምን ነበር የተናደድኩባት እስክል ሁሉን ነገር አስረሳኝ፡፡


እናም ታላቁ የነጻነት ጉዞዬ በእዚህ ሁኔታ በእማዬ ድንች በስጋ ወጥ ተቀየረና በአጭሩ ተቀጨ፡፡
‹‹ጋቢና አስቀመጣት››
----
ከስንት ልምምጥ በኋላ አንድነት ፓርክ አብረን ለመጎብኘት ጊዜ በማግኘቱ ያለ ቅጥ ተደስቼ ነበር፡፡
ስንቴ ቀጠሮ ይዘን ባለቀ ሰአት እያፈረሰ፣ ነገ እንሄዳለን ተባብለን በተቀጣጠርን ማግስት እየሰረዘ አስቸግሮኝ ነበር፡፡ በመጨረሻ ዛሬ ሆነለት፡፡

ቤት መጥቶ እንደሚወስደኝ ስለነገረኝ መጫወቻ ቦታ እንደሚሄድ ልጅ ጓጉቼ ገና ሰኣቱ ሳይደርስ ተዘገጃጅቼ ጠበቅኩት።

ሲደርስ ግን ብቻውን አልነበረም።ያቺ መዥገር አብራው ነበረች፡፡ ሳባ የሚሏት መዥገር፡፡

ሳትጠራ በሄደበት ሁሉ ተነቅልቅላ ራሷን እየጋበዘች ስር ስሩ ትላለች፡፡ በምን ቸገረኝ የኮሌጅ ዘመን ፎቶዎቻቸውን ስካን እያደረገች በየፌስቡኩ ትለጥፍና፣ጣፋጭ ትዝታችን ገለመሌ እያለች ሰባ ሰማኒያ ሰው ታግ ታደርጋለች፡፡ ዛሬም በእኛ ቀጠሮ ቀድማኝ ተገኝታ አብራው ነች፡፡ አጅሪት ይባስ ብላ ጋቢና ነው ጉብ ያለችው፡፡ የእኔ ወንበር ላይ፡፡

ይቺ አይን የበላች ወመኔ፡፡


ያየሁትን ባለማመን ቆም አልኩ፡፡


ጨጓራዬ እየጨሰ፡፡ ከወንበሬ ወርዳ ወደኋላ ትሄዳለች በሚል ሰላላ ተስፋ ጥቂት ቆምኩ፡፡
እሷ እቴ፡፡


እያመነታሁ ቀስ ብዬ የኋላውን በር እጀታ ጨበጥ አደረግኩት፡፡
አልከፈትኩትም፡፡ አለመክፈቴ እሷ ሆን ብላ ነገሬ ባትለኝ እሱ አንድ ነገር ብሎ አሳፍሯት ቦታዬን ትለቃለች ብዬ ነበር.. ግን እሱም እንደ እሷ ዝም አለ፡፡

ቁርጤን አውቄ ከኃላ ገባሁ። ተደላድዬ ለመቀመጥ ስጣጣር
“እሺ የተከበሩ- እንዴት ዋሉ ?”
አለኝ እንደነገሩ ዞር ብሎ እያየኝ፡፡
“ ድንቄም ክብር! አክብረኸኝ ልብህ ውልቅ ብሎ የለም እንዴ...? እንዲህ ነው እንዲ ክብር አለ እንዴ?” ብዬ እያሰብኩ….

ጭጭ አልኩ፡፡

እመት መዥገር ዝምታዬን ተከትላ በዛ ለጆሮ በሚቀፍ በልጣጣ ድምጿ-

“ሃይይይ ትሁትዬ!” አለችኝ ትሁት እሱ እንደሆነ ሁሉ እሱን እሱን እያየች፡፡


ውስጥ ውስጡን ተለበለብኩ ግን ፊቴን አጥቁሬ ደስ ላሰኛት ስላልፈለግኩ የሆዴን በሆዴ ያዝ አድርጌ መምጣቷን ቀድሞ እንዳወቀ ሰው ቀለል ባለ ሁኔታ ‹‹ ሰላም ሳባ›› አልኳት ስሟ አፌን እየጎመዘዘኝ፡፡


በገዛ ቀጠሮዬ፣ በገዛ ቦይፍሬንዴ፣ በገዛ መኪናው እንደተጋባዥ እንግዳ መሳቀቄ፣ የሁለት ሰዎችን ጣፋጭ ጊዜ ሊበርዝ እንደተገኘ እንግዳ መቆጠሬ ደግሞ የባሰ አተከነኝ፡፡

ልገንፍል ልገንፍል የሚል ንዴቴን ዋጥ አደረግኩ፡፡

መኪናው ተንቀሳቀሰ፡፡ ጉዞ ተጀመረ።


የአወራራቸው ፍጥነት ትንግርት ነው፡፡ አንዱ ወሬ ሳያልቅ በላይ በላዩ ኣዲስ ወሬ እየጨመሩ ይሉታል።

እኔ የምለው…ከመቼ ወዲህ ነው ሳምሶን እንዲህ ወሬኛ የሆነው?…ከኔ ጋር እንዲህ ወሬን ተስገብግቦ ኣውርቶ አያውቅም።

ብዙ ነገራቸው አልገባ አለኝ፤ ወሬያቸው፣ ቀልዳቸው፣ ሳቃቸው።

እሷ ደግሞ በበነነ በተነነው አመድ ላይ እንደሚንደባለል አህያ ነው የምታናፋው። ሌላ ቀን በትንሽ በትልቁ ድምጽ ተረበሽኩ፣ ራሴን አመመኝ ምናምን የሚለው ሳምሶን የእሷ የሚያንባርቅ ድምጽና የማያቋርጥ ሳቅ ግን የረበሸው አይመስልም፡፡


እኔም አልፎ አልፎ ራሴን በወሬያቸው መሃከል እየሰካሁ በሳቅ ልሳተፍ ሞክሬ ነበር፡፡
ውስጤ ግን አልቅሽ አልቅሽ ነው ያለኝ። ይሄ በውስጤ የሚንተከተክ የመከፋት ስሜቴ ፊቴ ላይ ያስታውቅ ይሆን ብዬ ብሳቀቅም ዞር ብሎ ያየኝም የለ። ወሬያቸው መች ፋታ ሰጥቷቸው!


ትንሽ እንደሄድን….






“ሳሚዬ አፈር ስሆንልህ አንድነት ፓርክ ከመሄዳችን በፊት ምሳ ነገር እንብላ። በጣም ነው እኮ የራበኝ” አለችው።


ምን አይነቷ አይን አውጣ ናት በገብርኤል?
ትንሽ እንኳን አትፍርም አንዴ…….?

መቼስ ይሄ ሁኔታዋ ከመስመር ያለፈ በመሆኑ እሱም ቢሆን ‹‹አይ ያ እንኳን አይሆንም›› ይላታል፡፡

ለዚህ ቀጠሮ፣ ለዚህች ቀን የነበረኝን ጉጉት እያወቀ እሷን ደርቦ ይዞ መምጣቱ፣ ከፊት ማስቀመጡ ሳያንስ፣ ተሞላፍጣ ስለጠየቀችው እሺ አይላትም፡፡
‹‹ ለምሳማ አንቆምም..ሃኒዬ ፓርኩን ለማየት ስትጓጓ ስንት ጊዜዋ መሰለሽ! …ይረፍድብናል…ባይሆን እዚያው አንዱ ካፌ ሄደን የሆነ ነገር ትበያለሽ›› ይላታል አይደል?



“እሺ..ምን ችግር አለው…? የት እንሂድ” አላት፡፡

እኔን ሳይሆን እሷን እያየ፡፡ ለእኔ ሳይሆን ለእሷ ፍላጎት ቅድሚያ እየሰጠ፡፡


የእሳት ነበልባል አላምጨ የዋጥኩ አስኪመስለኝ ድረስ ጉሮሮዬ፣ ሆዴ ነደደ።


ከንዴቴ በላይ ግን እጅጉን አፈርኩ፤ የምናገረው እስኪጠፋኝ፣ እንስ፣ ኩምሽሽ፣ ስቅቅ አልኩ፡፡ አንዳቸውም ልብ ያሉኝ አይመስሉም፡፡ አፌን ከፍቼ አንዳች የተቃውሞ ነገር ለማለት ፈለግኩ፤ ምላሴ ግን በጄ ብሎ አልታዘዝ አለኝ፡፡



ስለዚህ እዚህ መኪና ውስጥ፣ ከተማው ውስጥ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ፣ በአፍሪካ ቀንድ፣ አፍሪካ ውስጥ፣ በዓለም ላይ እንደሌለ ሰው ዝም አልኩ፡፡



“ግሬት…ለምን ፒያሳ ዮሃሚያ አንሄድም ታዲያ? …ክትፏቸውን እንዴት እንደምወደው ታውቅ ኣይደል?” አለችው፡፡

የምትወደውን ክትፎ ቤትም ያውቃል፡፡
ጥሩ ነዋ!

“ሹር…! “ ብሎ እኔን ዞር ብሎ እንኳን ሳያየኝ አቅጣጫ ቀይሮ ወደ ፒያሳ መንዳት ጀመረ።

በነገራችን ላይ እኔ ቬጂተሪያን ነኝ፤ ስጋ ኣልበላም።


ዮሃሚያ ገብተን እንደተቀመን ልክ የአባትዋ ቤት እንደሆነ ሁሉ ብልጥጥና ልጥጥ ብላ ሶስት ለብለብ ክትፎ ኣዘዘች።

ይሄን ጊዜ ነው ሳሚ ከእንቅልፉ እንደነቃ ሰው ብንን ብሎ፤
“ውይ አልነገርኩሽም ለካ! ሃኒ እኮ ስጋ አትበላም” ያለው።

ተመልሻለሁ ሰዎች፡፡ ካለመኖር ወደመኖር መጥቻለሁ፡፡

በመጨረሻም እዚህ ከእነሱ ጋር አብሬ መሆኔ እውቅና አገኘ፡፡ ፍላጎቴ ከቁምነገር ተጻፈ፡፡

ኡፎይታ ቢጤ ተሰማኝ፡፡ አሁን ነገሮች ፈር ይይዛሉ፡፡ አሁን ማን የማን እንደሆነ፣ ደረጃችን ይለያል፡፡


እፎይታዬን አጣጥሜ ሳላበቃ በዚያው ብታንሾካሹክም በሚያደነቁር ድምጽዋ-
“ውይ ቬጂተሪያን ነሽ እንዴ? …ለነገሩ ልክ ነሽ…ከዚህም በላይ እንዳትወፍሪ ይረዳሻል…አሪፍ ነው፡፡ ታዲያ ለምን የጎመን ክትፎ አታዢም? ቅቤውን ከፈራሽ ያለቅቤ ይሰሩልሻል” አለችኝ፡፡


ጠረጰዛው ላይ በትንሽዬ ሙዳይ የተቀመጠውን ሚጥሚጣ አንሺና እዚያ ነገረኛ አይኗ ላይ ሞጅሪባት ሞጅሪባት አለኝ፡፡
እንባዬ ኣይኔን ቆጠቆጠው።

‹‹ላለመወፈር ምናምን አይደለም…ከልጅነቴም አልወድም…አሁን ደግሞ የፕሪንስፕል ጉዳይ ነው›› አልኳት ከቃላቱ እየታገልኩ፡፡

-
ባልለመድኩት ሁኔታ ጸጥ ብላ ሰማችኝና ‹‹ክትፎዬ ሳይመጣ እጄን ልታጠብ›› ብላ የሌላትን ቂጥ እያገላበጠች እየተመናቀረች ሄደች፡፡ አሁን ለብቻው አግኝቼው ንዴቴን እዘረግፍበታለሁ ብዬ ስመቻች ያሰብኩትን እንዳወቀ ሁሉ ተከትሏት ሄደ፡፡
የባሰ ጦፍኩ፡፡
እያሽካኩ ተመልሰው መጡና ከመቀመጣቸው አስተናጋጁ ሲከንፍ መጥቶ ‹‹ እህስ..የሚጠጣ ምን ይምጣ?›› አለ አፈራርቆ እያያቸው፡፡ እሱም እኔን ከነመኖሬ የዘነጋኝ ይመስላል፡፡

‹‹የተለመደው ይምጣ?›› ብላ ጠየቀችው፡፡ ሳምሶንን፡፡ ጭራሽ የለመዱትም አላቸው…

አስተናጋጁ አንድ ኮካና አንድ አምቦውሃ ይዞ ተመለሰ፡፡

ሳምሶን ‹‹እኔ ቢራ እጠጣለሁ ፡፡ ይሄ ለሁለት ይበቃችኋል›› ብሎ ያዘዘው ነው፡፡ እኔ እና እሷ ለሁለት የምንካፈለው ብቸኛው ነገር ግን አንድ ኮካ እና አንድ አምቦውሃ እንዳልነበረ ግልጽ ነው፡፡
(ከላይ የቀጠለ)
አፍ ለአፍ ገጥመው ማውራታቸውን ቀጠሉ፡፡
አፋቸው ክትፎ በቆጮ በማያላመጥበት ቅፅበት በወሬ እንደተጠመደ ነው፡፡ በዘይት የተጠበሰው የጎመን ክትፎ ጣእሙ መጥፎ ባይሆንም አልበላ ስላለኝ ለኮፍ ለኮፍ አድርጌ ተውኩት፡፡ ፊልም ለማዳመቅ እንደገባ አስተኔ ገጸ ባህሪ አፌ ተለጉሞ ሳያቸው ክትፏቸውን ጨረሱ፡፡


ሂሳብ እየከፈለ ድንገት ድንቅ ሃሳብ እንደተከሰተለት ሁሉ እያያት-
‹‹ፒያሳ ከመጣን ላይቀር ክሪያዚስ እንሂዳ?›› አለ፡፡

እንደ ልጅ ፈነደቀች፡፡
‹‹እሱማ አይቀርም..ትዝታውስ እንዴት ያስችለናል?›› አለችው፡፡

‹‹ሃኒ ቶሎ ኬክ በማኪያቷችንን በልተን እንወጣለን እሺ?›› አለኝ አጠገብ ለአጠገብ በተቀመጥንበት ለመጀመሪያ ጊዜ ትከሻዬን ያዝ እያደረገኝ፡፡
ከእሷ ጋር ከጨረሰ በኋላ ውሳኔያቸው ላይ ማህተም እንዳደርግለት እኔ ጋር የሚመጣው ለምንድነው?

የምለው ጠፍቶኝ አሁንም በዝምታዬ ገፋሁ፡፡

ስንወጣ አማራጭ እንደሌለው ሰው እጁን ይዤ ወደ ክራይዚስ የሚወስደውን ዳገትe በእግር ሄድን፡፡ ሶስት ማኪያቶና ሶስት ኬክ አዘዘና አሮጌው የብረት ወንበር ላይ ከመቀመጣችን የማያልቅ ወሬያቸውን ቀጠሉ፡፡
እሱ ስለ ስድስት ኪሎ የባህል ማእከል ደጋግሞ እያነሳ ያወራል፡፡ ሃሳቡንም አረፍተነገሩንም ቀምታው ትጨርስለታለች፡፡ ይስቃሉ፡፡
ስለ አንዱ የዩኒቨርስቲ ገገማ መምህር ታነሳለች፡፡ ይስቃል፡፡ አረፍተነገሯን ይጨርስላታል፡፡

ትእግስቴን ጨረስኩ፡፡

ከዚህ በፊት አይቻት እንደማላውቅ ሁሉ ትክ ብዬ አየኋት፡፡

ለነገሩ ከዛሬ በፊት በአካል ያገኘኋት አንዴ ብቻ፣ ብሄራዊ ቲያትር ጋር መንገድ ላይ ነበር፡፡ ለአፍታ፡፡ ግን የሆነ ነገሯ ኮሰኮሰኝ፡፡ ሳሚ አባባሏ፣ ደረቱ ላይ አለጣፈፏ፣ ለከንፈሩ የቀረበ የጉንጩ ቦታ ላይ በቆራጣ አሳሳሟ፡፡ አንገቱ ጋር አከራረሟ፡፡


ከዚያ በፊት ስለ እሷ ብዙ ሰምቻለሁ፡፡


እሱ ደጋግሞ በሚያወራልኝ፣ በሚጻጻፏቸው መልክቶች፣ አልፎ አልፎ ደግሞ ምሽቱን ሙሉ በስልክ በሚሰልቁት ጅራታም ወሬ…..ሳልፈልጋት ነው ያወኳት። ሁኔታቸው ቢቀፈኝም ስለምወደው ነገሩን ችላ አልኩት፡፡ ያም ሆኖ አልፎ አልፎ ‹‹ይሄ ነገር አልበዛም?›› ስለው ‹‹አንቺ ደግሞ ጓደኛዬ እኮ ናት..ንጹህ ጓደኛዬ›› እያለ አፍ አፌን ይለኛል፡፡

ቆሻሻ ጓደኛ አለ እንዴ?

ከኬክ ቤቱ ወጥተን ወደ ኣንድነት ፓርክ እየሄድን ስልኩን ብድግ ኣድርጋ ፓስወርዱን አስገብታ ስትከፍተው አየሁ። በኋላ መስታወቱ ፊቱን አየሁት፡፡ ፈገግ ብሏል- ከእኔ ደብቆት የቆየ ቅብጥብጥ ፈገግታ፡፡



ስልኩን ስትነካካ ቆየችና “እኛ ነው ማየት” የሚለውን የታምራት ደስታን ዘፈን ከፈተችው፡፡

ፊቱ በራ፡፡

‹‹ ውውው ይሄ ዘፈን!›› አለ፡፡
በትዝታ ገመድ የተጠለፈ ይመስላል፡፡ እኔ በማላውቀው፣ እኔን በማይመለከት የሁለቱ ብቻ ትዝታ ወደ ኋላ የነጎደ ይመስላል፡፡

ከዚያ ዘፈኑን ጮክ ብለው እየተቀባበሉ አብረው ዘፈኑት።
ውስጤ ሲተራመስ ተሰማኝ፡፡
ልቤ ከነበረበት የተንሸራተተ፣ ተንከባሎ እግሬ ስር የወደቀ መሰለኝ፡፡


--
ከአንድነት ፓርክ መልስ ወደቤት ሊያደርሰኝ ጋቢና ተቀምጨ እየሄድን አንድ ነገር ብቻ ጠየኩት።
“እንዴት እኔ እያለሁ እሷን ጋቢና ታስቀምጣታለህ?”

ለመልሱ የተዘጋጀ ይመሰል ፈጥኖ መለሰልኝ፡፡

“ ያው መጀመሪያ ያገኘኋት እሷን አይደል? ለዛ ነው። “


እህ፡፡
መጀመሪያ ያገኘኋት እሷን አይደል?

አጭርና ስለታም መልስ ነበር- እያንገራገረ ያስቸገረን አንጀት የሚቆርጥ፡፡
ሰኒ ሆቴል
------


አውቶቡሱ ሰው እጭቅ አድርጎ መጣ።
ከቆሸሹና ከተዘጉ በሮቹ አፈትልከው የወጡ ልብሶች ይታያሉ፡፡
ያን ያህል ነው ጢም- ጢቅ እስኪል የጫነው፡፡



ሰኒ ሆቴል  አጠገብ ቆማለች።
ቦርሳዋን ጥብቅ አድርጋ ይዛ።



ከመውጣቷ በፊት ዝናብ እንዳይዘንብ ጸሎት ቢጤ እያነበነበች -
አልፎ አልፎ ከሚገጥሟት ባዶ አውቶቡሶች አንዱ ፊት ለፊቷ እንዲቆም፣ ወይ ደግሞ አንድ ‹‹ሃይገር በወንበር›› እያለ የሚለፈልፍ ወያላ ያለበት ሃይገር ሲከንፍ መጥቶ ሲያክለፈልፍ ቤቷ እንዲጥላት እየተመኘች።



‹‹እዚህ ውስጥማ አልገባም›› አለችና፣
ሌላ አውቶቢስ ለመጠበቅ ወሰነች፡፡

ሆቴሉን ዞር ብላ በጨረፍታ ተመለከተች።



አሁን ድረስ እልልታው ይሰማታል፡፡ ጭብጨባው፡፡ ጭፈራው፡፡
ወርቃማና አይን የሚያፈዝ ብርሃን የሚረጩ ትልልቆቹ የሆቴሉ አዳራሽ የክሪስታል መብራቶች ይታይዋታል፡፡


ቬሎዋ የእብነበረድ ወለሎቹን በስሱ እየጠረገ ስትሄድ፣ ሰፊው የጥሬ ስጋ ግድግዳ፣ እንደ ልብ ሲፈስ የነበረው መጠጥ አሁንም ምስላቸው አንድ በአንድ  ድቅን ይልባታል።



እንግዶቻቸው ከመጠን በላይ ተደስተው ነበር፡፡
ጠግበው፣ ሰክረው፣ ጨፍረው ሲያበቁ፣


‹‹ከደገሱ አይቀር እንዲህ ነው እንጂ!›› ብለው ሰርጓን አሞግሰው፣ ቤተሰቧን አመስግነው፣ በድሎታቸው ቀንተዋል፡፡
ሰርግዋ እዚህ፣ ሰኒ ሆቴል ነበር፡፡
ከአስራ አንድ ወራት በፊት፡፡




አሁን እሱው ሆቴል አጠገብ አውቶቢስ ትጠብቃለች።
በፊት ውስጥ ነበረች፣ አሁን ውጪ ነች፡፡
ያኔ ቬሎ ለብሳለች፣ አሁን የአዘቦት እንደነገሩ ልብስ አድርጋለች፡፡




ሌላ አውቶቡስ መጣ።
ይሄኛውም ወንበር ቀርቶ ደህና መቆሚያ ቦታ የለውም፡፡
ልግባ አልግባ…?


አመነታች፡፡



ስፒከሩ ከተበላሸ የሰነባበተ ስልኳን፣ ግማሽ የተበላለት ምሳቃዋን እና ዘጠና ስድስት ብር የያዘውን ቦረሳዋን በድጋሚ አጥብቃ ያዘች፡፡



---
ባሏ ድግሱ መጧጧፍ ሲጀምር ፣


‹‹ራኬብዬ፣ ይህን የሰርግ ጣጣ ቀለል ብናደርገው አይሻልም? ኑሯችንን በአግባቡ እንድንጀምር…›› አላት።
‹‹ ኑሯችንን በአግባቡ ለመጀመር መሰለኝ እኮ ሰርግ የምናደርገው…›› ብላ መለሰችለት፡፡
‹‹ግን እኮ እጃችን ላይ ብር የለንም…›› አላት።
‹‹ ብር..ብርማ ወደፊት ሰርተን እናገኛለን…ሰርግ ግን አንዴ ካለፈ አለፈ…›› ፈጠን ብላ መለሰችለት፡፡



ጭንቅላቱን እየነቀነቀ ሄደ፡፡



ከሳምንታት በኋላ የወጪውን መከመር ሲያስተውል ዳግመኛ መጣና፣
‹‹ ይሄ ሁሉ ወጪ…ለዚያውም በብድር ! ሰው ተሰብስቦ አንድ ቀን በልቶት ለሚሄድ ድግስ አግባብ አይመስለኝም…እዳ ለድግስ…?››  ሲላት፣
‹‹ከልጅነቴ ጀምሮ ሳልመው የኖርኩትን ቀንማ ድግስ ብለህ አታቃልለውም….›› አለችው፡፡



እንዲህ እንዲህ አፍ አፉን ስትለው ዝም አለ፡፡




እናም ተበደሩ።
እንደገና ተበደሩ፡፡
ደግሞ እንደገና ተበደሩ፡፡

ቀሚሷ፡፡
ሜካፑዋ፡፡
ልብሱ፡፡
አዳራሹ።
ምግቡ።
አዳራሽ ማስጌጫው።
መኪናው፡፡
ፎቶና ቪዲዮው፡፡

አሁን ድረስ ሲሶውን ያልከፈሉትን እዳ እስኪቆልሉ እሺ ብሎ ከሰጣቸው ሰው ሁሉ አይናቸውን ሳያሹ ተበደሩ፡፡



አሁን የሚኖሩት ሩቅ ነው።
ከከተማ ወጥተው፡፡
ስቱዲዮ ኮንዶሚኒየም፡፡
ቤታቸው ከተሰረጉበት ቦታ እጅግ ሩቅ ነው፡፡



ራኬብ ወደ ስራና ከስራ መልስ  አውቶቢስ ጥበቃ ብቻ በቀን ሁለት ሰዓት መንገድ ላይ ታጠፋለች።
ያውም ሲቀናት፡፡
አውቶቢስ ቶሎ ቶሎ ከመጣ፡፡ ካልዘነበ፡፡ የአዲሳባ መንገድ ጂኒው ዞር ካለ፡፡



ሆኖም ግን፣
ብዙ የከፈለችው ፎቶግራፈር አሁን ድረስ ፎቶዎቿን ሌሎችን ሙሽሮች ለማጥመድ ፌስቡክ ላይ ሲለጥፍ ታግ ሲያደርጋት መንፈሷ ይታደሳል፡፡

ሲደብራት ሲደብራት ቆሎዋን እያሻመደች፣ ሻይዋን ፉት እያለች የሰርጓን ቪዲዮ በትንሽዬ ቲቪዋ እያየች ትጽናናለች፡፡




በቆመችበት የጋብቻ ቀለበቷን ትክ ብላ ተመለከተች፡፡
"ብሸጠው ምን ያህሉን እዳ ያቀልልኝ ይሆን?" ብላ አሰበች፡፡
"ባሌ ይሄንንስ ሃሳብ እሺ ይለኝ ይሆን?" ብላ ተጨነቀች፡፡



ሌላ አውቶቢስ መጣ፡፡


እዚህኛው ውስጥ መቀመጫ ባይኖርም ዘና ብሎ መቆም ይቻላል፡፡


ገባች፡፡


አንዱን ቋሚ ዘንግ ተደግፋ ከመቆሟ ስልኳ ጮኸ፡፡
እሱ ነው፡፡ ባሏ፡፡


አነሳች፡፡


‹‹አይሰማኝም!›› አለች ጮክ ብላ፡፡
"እየሰማሁህ አይደለም" አለች እንደገና፡፡



‹‹ይሄ ብሽቅ ስፒከር….››  አለች ለራሷ፡፡



ሲሰለቻት፣
ብስጭት ብላ ‹አይሰማኝም አልኩህ! ››
አለችና ስልኩን ዘጋችው፡፡



አልሰማችውም እንጂ ባሏ በዚያች ቅጽበት
‹‹መች ተሰምቶሽ ያውቅና!›› ብሎ ነበር፡፡



ስልኳን ቦርሳዋ መልሳ በአውቶቢሱ መስኮት ወደ ውጪ አየች፡፡


ሆቴል ሰኒ ያንጸባርቃል፡፡ ያብረቀርቃል፡፡ ምናልባትም አዲስ ተጋቢዎችን ለመሞሸር አፉን ከፍቶ ይጠብቃል፡፡



አውቶቢሱ በሩን ዘግቶ ለረጅም ጉዞው ተንቀሳቀሰ፡፡
‹‹እንዲህ ብሎኝ ነበር››
--

በተዋወቅን የመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት እንዲህ ብሎኝ ነበር…


• በሕይወቴ እንዳንቺ አይነት ሴት አጋጥማኝ አታውቅም፡፡
• እነ ጥላሁን ገሰሰ የዘፈኑላት ሴት ማለት አንቺ ነሽ፡፡
• ብዙ ጊዜ የማውቅሽ ይመስለኛል፡፡
• ፍቅር በዚህ ፍጥነት ይዞኝ አያውቅም፡፡
• አንዳንዴ ገና ሳንተዋወቅ በፊት የተመኘኋት፣ ያለምኳት ሴት ትመስይኝና የአምላክ ቸርነት ግርም ይለኛል፡፡ ሰው በልኬ አለ ቴዲ አፍሮ፡፡ አሁን ገና ልኬን አገኘሁ፡፡
• ካንቺ ጋር ስሆን የሚሰማኝ ሰላም ከማንም ጋር ተሰምቶኝ አያውቅም፡፡
• እናቴን እንኳን እንዳንቺ የምወዳት አይመስለኝም፡፡
• መልክሽ ቢባል፣ ቁመናሽ ቢባል፣ ጸባይሽ ቢባል…ቆይ ግን የሌለሽ ምንድነው?


በሶስተኛው ሳምንት እንዲህ ብሎኝ ነበር...


• በራስ መተማመንሽንና ነጻነትሽን ስወደው፡፡
• ዓለም ስታስከፋኝ የምጽናናው ባንቺ ነው፡፡
• እንደሌሎች ወንዶች አይደለሁም…
• ላንቺ ስል የተሻለ ሰው መሆን እፈልጋለሁ- እንድመጥንሽ፡፡
• ንፅህናሽ ግርም ይለኛል..በዚህች ቆሻሻ ዓለም እንዳንቺ አይነት ሰው ያውም በዚህ ነቀዝ ዘመን መኖሩ ይደንቀኛል፡፡
• ከክፉ ነገር ሁሉ ልከልልሽ እፈልጋለሁ…
• ከእንግዲህ አይኔ ሌላ አያይም…ሚስቴን፣ የልጆቼን እናት አግኝቻለሁ…
• ጓደኞቼ እንኳን አስጠሉኝ…እኔ ላንቺ አንቺም ለእኔ እንበቃለን በቃ…


ወር ተኩል ሲሞላን እንዲህ ብሎኝ ነበር…

• የእናቴን ቀን ይስጠኝ እንደሌሎች ሴቶች አይደለሽም፡፡
• ከዚህ በፊት እንደተጎዳሽ አውቃለሁ፤ አትስጊ ፈጽሞ አልጎዳሽም፡፡
• ለእህቴ ስላንቺ ነግሬያት ገና በወሬ ወዳሽ ልትሞት…
• አንቺ ብቻ ግልጽ ሆነሽ የልብሽን አጫውቺኝ፡፡ ምንም ቢሆን እረዳሻለሁ፡፡
• ስላለፈው ሕይወትሽ አንድ ሳታስቀሪ ንገሪኝ፡፡ አበጥሬ ላውቅሽ እፈልጋለሁ፡፡
• በእኔና አንቺ መሃል መደባበቅ ምስጢር ምናምን እንዲኖር አልፈልግም…ሁሉን ነገር ንገሪኝ
• እንዳንቺ የምትረዳኝ ሴት አግኝቼ አላውቅም፡፡
• መቼም ቢሆን እንዳንወሻሽ እሺ?



ሁለት ወር ሲያልፈን እንዲህ ማለት ጀመረ....

• ቆንጆ እኮ ነሽ…ሜካፑ ቢቀርስ?
• ዛሬ ላገኘሽው ሰው ሁሉ ምስጢርሽን አትዘርግፊ…አንቺ ምስኪን ስለሆንሽ ነው ግን በኋላ ሊጎዱሽ ይጠቀሙበታል…
• እኔ የምለው…ከኤክስሽ ጋር አሁን ፌስቡክ ላይ ጓደኞች ናችሁ እንዴ?
• ጓደኛ ባታበዢ ደስ ይለኛል…እኔ አልበቃሽም…?
• ልክ ነው ለሁሉ ነገር ፈጥነናል ግን በቃ ተዋደድና…ከተዋደድን ምናለ?
• ፍቅራችንን እንድንንከባከበው ብዬ ነው ትርፍ ጊዜሽን ሁሉ ከእኔ ጋር አሳልፊ የምልሽ…ከተውነው ባጭሩ ይቀጭብናል…
• ይህቺ ልጅ ጓደኛሽ መስላ ትቀናብሻለች…ብትርቂያት ይሻላል ባይ ነኝ፡፡
• አንቺን እኮ አይደለም…እሱን ነው የማላምነው፡፡



ሶስተኛ ወር ላይ እንዲህ ይለኝ ጀመር....


• ሁልጊዜ ልክ ነኝ ብለሽ ነው የምታስቢው…?በጣም ግትር ነሽ..
• ሁሉንም ነገር ለምን ክርክር እንደምታደርጊው አላውቅም
• ጡትሽን የሚያሳይ ልብስ አትልበሺ ማለት ነው ቅናት…?
• ከእንግዲህ ግን ቀድመሽ ንገሪኝ፡፡ ሁሌም የት እንዳለሽ ማወቅ አለብኝ፡፡
• ዛሬ ኢንስታግራም ላይ የለጠፍሽው ፎቶ ምንድነው…?ሁከር ነው የምትመስይው እኮ…ቶሎ አንሺው…
• ጓደኞችሽ ስለሚቀኑብሽ ይሄ ሪሌሽንሺፕ ደስ አይላቸውም
• ላንተ ስል እተዋቸዋለሁ አላልሽኝም ነበር…?



አራተኛው ወር ላይ እንዲህ ማለት ጀመረ....

• አንዳንዴ እንኳን እንደ ወንድ ብትቆጥሪኝ ምናለ…?ፌሚኒስት ነሽ እንዴ?
• እሱማ ሰውየው ፊት ስትቁላዩ ፍለርት ስታደርጊ ነበር፡፡ እጅ ከፍንጅ ነው የያዝኩሽ ባክሽ…ንጹህ ንጹህ ለመጫወት አትሞክሪ
• ሁሉን ነገር ታወሳስቢዋለሽ..
• አንዳንዴ ድክም ታደርጊኛለሽ፡፡
• ሁሌ አጥፍተሸ እንደተበዳይ የምትሆኝው ለምንድነው ?
• እኔ ሆኜ ነው እንጂ ሌላ ወንድ ቢሆን እንዲህ ለብሸስ ስትወጪ አናትሽን ነበር የሚለው ፡፡
• ፐርፌክት ላልሆን እችላለሁ ግን ቢያንስ እንዳንቺ ያልሆንኩትን ለመምሰል አልሞክርም…



አምስተኛው ወር ላይ እንዲህ አለኝ..


• ፌስቡክ ላይ የምትለጥፊው ነገር ሁሉ እሮሮ…ሰው ስለእኔ ምን እንዲያስብ ፈልገሽ ነው? …ዴሊት አርጊው ሳንጣላ…
• ይሄ ልጅ አስተያየቱ ደስ አላለኝም
• ስለዚያ ክላስ ሜትሽ ስታወሪ እንዴት እንዴት ነው የሚያደርግሽ ?
• ስለ ልጅነቴ የነገርኩሽን ነገር እንደ ፍልፍሉ ቀልድ በየቦታው የምታወሪው ለምንድነው…እንዳትደግሚው፡፡
• ስንገናኝ ደስ ትዩ ነበር አሁን ግን…
• አንዳንዴ ገርልፍሬንዴ እንደሆንሽ ትረሻለሽ ልበል?
• ከዚህች ልጅ ጋር ጓደኝነት አቁሚ አላልኩሽም…?
• ወንድ ልጅ መሪ ነው..ቢያንቅሽም ዋጪው፡፡
• ሁለተኛ እንዲህ ስትይ እንዳልሰማሽ..!
• ይሄ አለባበስሽ የሸርሙጣ ነው…የት ለመድሽው?
• ይሄኛውም ኤክስሽ ነው…ሁለት ብቻ ናቸው አላልሽም ነበር...?ውሸታም!



ስድስተኛው ወር ላይ እንዲህ ይለኝ ጀመር...


• ሁለተኛ እንደዛሬው ሰው ፊት ታሳፍሪኝና አጠናግርሻለሁ፡፡
• ደህና ሰው ላይ ጥሎሽ ነው እንጂ ሌላ ወንድ ቢሆን እንዲህ አይታገስሽም!
• ተናገሪአ! ማነው ወንዱ? እ…እኔ…እኔ ነኝ…በይ አሁን ከዚህ ሂጂ..አስኮናኝ!
• ካንቺ በሁሉም ነገር የሚበልጡ ሴቶች እንኳን እንዳንቺ አይቆለሉም….መልክሽም ቢሆን እንደበፊቱ አይደለም…አረጋጊው እሺ..
• ጓደኞቼ ጋር ብውል አይደለም ባድር አይመለከትሽም እሺ…ልትቆጣጠሪኝ ትፈልጊያለሽ…?
• አሁን እኔ ብተውሽ ሌላ ወንድ አያነሳሽም..ለእራስሽ ያለሽ አመለካከት በጣም ትልቅ ነው ባክሽ…በጣም….ከየት አመጣሽው ግን…ማነው እንዲህ ነሽ ብሎ የቀለደብሽ…




በተዋወቅን የመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት እንዲህ ብሎኝ ነበር…

በሕይወቴ እንዳንቺ አይነት ሴት አጋጥማኝ አታውቅም…
ያልተነሳ ጥሪ
----
( በአንድ የቲክቶክ ቪድዮ ኮርኳሪነት የተፃፈ)


---

የሌሊት ሺፍቴን ጨርሼ ከንጋቱ አስራ ሁለት ሰአት ከሩብ ሲል ቤቴ ገባሁ።


ከልክ በላይ ደክሞኝ፣ እንቅልፍ እያንጎላጀጀኝ ነበር፡፡

ስልኬን ጭጭ አሰኘሁ፡፡
እንደ ሬሳ ተኛሁ፡፡




ጠዋት 5.33
---
ነቃሁ፡፡
አስራ ሰባት ሚስድ ኮል፡፡
አስር የድምጽ መልእክት፡፡
ሁሉም የገርልፍሬንዴ ነው፡፡



2:03
“ሄይ ማሬ፣ ተኝተህ መሆን አለበት፡፡ ስትነሳ ደውልልኝ፡፡ እምዋ!”

የእኔ አሳቢ፡፡


2:17
“እስካሁን ተኝተህ ባልሆነ…?  የአዲሳባ ሰው መተኛት ትቶ ሌሊት ሌሊት ሆስፒታል ለመዝናናት መሄድ ጀመረ እንዴ?ደውልልኝ”

አሽሙሩ ቢቀርባት ጥሩ ነበር፡፡


2:41
“ይሄን ያህል ጊዜ መጋደም እንኳን የጤና አይደለም….እውነት ግን ተኝተህ ነው …ነው ወይስ ብቻህን አይደለህም?”

ምን? ከማን ጋር እሆናለሁ ታዲያ?


2:59
“እንደምታፈቅርህ ተስፋ አደርጋለሁ…መልካሙን ሁሉ እመኝላችኋለሁ”
ቆይ ቆይ- ማናት እሷ የምታፈቅረኝ?



3:14
“ የሚገርመው ያን ያህል እንኳን ብልጥ አይደለህም፡፡ በቀላሉ ነቃሁብህ”
ብልጥ? የምን ብልጥ?



3:21
“ሶፎኒያስ፣ ባንተ ምክንያት ማበዴ ነው፡፡ ”
አዎ- እሱንማ በደንብ እያየሁ ነው፡፡



3:43
“እሺ…ለእህትህ ደውዬላት ነበር፡፡ እውነት ተኝቶ ነው ስልኬን የማያነሳው ብዬ ጠየቅኳት፡፡ ይሆናላ አትለኝም፡፡ እንዴት ስላት…እኔ በምን አውቃለሁ አብሬው አይደለሁ አለችኝ፡፡ እኔ የምለው…መንታ አይደላችሁ እንዴ…?  ከልጅነታችን ጀምሮ አንድ ላይ ሳንሆን ራሱ ስሜታችንን እናውቃለን ስትሉ የነበራችሁት ፉገራ ነበር….?  ነው ወይስ የሆነ ነገር እየደበቀችልህ ነው…?”

እየደበቀችልህ? ምንድነው የምትደብቅልኝ?



4:06
“እህትህ ጮኸችብኝ፡፡ ሶስቴ ስለደውልኩላት ተናዳ እኮ ነው፡፡ እኔም ጮህኩባት፡፡ ምን አባቷ እንዲህ ያቆናጥራታል…?  ስለምወድህ ስላንተ ተጨንቄ ብጠይቃት ቢች ቢች የምትጫወተው ለምንድነው?”

በጌታ በእየሱስ ስም፡፡


4:13
“እኔ የምልህ ግን…ከእኔ ምን አጥተህ ነው አይንህ ሌላ ያየው? …ምን አጎደልኩብህ…?  ምግብ ስሰራ እንደ እናት…መኝታ ቤት ስገባ እንደ ሚስት ስለሆንኩልህ?”

ይሄ ነገር ፕራንክ እየመሰለኝ ነው፡፡ መጥፎ ፕራንክ፡፡



4:45
“እህትህ ሱቅ መሄዴ ነው፡፡ በስልክ የምትሰድበኝን ፊት ለፊቴ ቆማ ትደግመው እንደሆነ አያለሁ !”

ይሄ ቅዠት ነው፡፡ አልነቃሁም እንዴ?


+++
ደወልኩላት፡፡
አነሳችውና ምንም እንዳልተፈጠረ እርግትግት ባለ ድምጽ




‹‹እንዴት ዋልክ የእኔ ፍቅር?  ….ፖሊስ ጣቢያ ስለሆንኩ ብዙ ማውራት አልችልም….አይዞህ ....እንዳትደነግጥ- ደህና ነኝ፡፡…እህትህ ጋር ሄጄ…ሳላስበው ነገሩ ከረረና የቡቲኳን ዲስፕሌይ መስታወት ሰበርኩት…እሷን እንኳን ትንሽ ነከስኳት እንጂ ምንም አልሆነችም…ይልቅ ቶሎ ና እና ዋስ ሆነህ አስወጣኝ…››

አለችኝ፡፡



‹‹ወይ ይሄን የሌሊት ሺፍት ስራ ማቆም ወይ ሴት ከመጥበሴ በፊት የአእምሮ ጤና ምርመራ ማድረግ ይኖርብኛል›› ብዬ እያሰብኩ መንታ እህቴ ደወለች፡፡


ኡፍፍ፡፡
‹‹እግዚአብሔር ሰጠ…››
---




ልጄ በጥቅምት ወር ሞተብኝ ፤  የሚወደው ካልሲ ግን አሁንም መሳቢያዬ ውስጥ አለ።


ቀዩን ፣ እላዩ ላይ ትናንሽ  ነጫጭ ዳክዬዎች ያሉበትን ካልሲ ነው የሚወደው፡፡


ሁለቱም እግር ካልሲዎቹ እስካሁን ሳሙና ሳሙና እና አፈር አፈር ይሸታሉ፡፡ አጥቤያቸው አላወቅም፤ ግን ሁልጊዜ ማታ፣ ጥቅላቸውን እፈታና ደግሞ እንደገና እጠቀልላቸዋለሁ፡፡



እሱን ካጣሁ ወዲህ እራሴን ያስለመድኩት፣ ከሚያስፈራው ጸጥታ ጋር የማወራበት፣ የዘወትር ተግባሬ፣ የቀን ተቀን ጉዳዬ ሆኗል፡፡
ካልሲውን ጠቅልሎ መፍታት፡፡ 



በሞቱ ማግስት ለሁለት ሳምንታት ግማሹ ሰው ምግብ፣ ሌላው ከእኔ ጋር፣ እኔው ላይ ማራገፍ የሚፈልገውን ሃዘን፣ ቀሪው ደግሞ ያልጠየቅኩትን ምክር በግድ ሊግተኝ ይመላለስ ነበር፡፡ 


የመጡት ሁሉ ምክርና ሃሳባቸው ተመሳሳይ ነበር፡፡




‹‹እግዚአብሔር ያጽናናሻል››
‹‹እግዚአብሔር ለሁሉም ምክንያት አለው። ››
‹‹እግዚአብሔር አይሳሳትም››
‹‹አይዞሽ! ፈጣሪ ያበረታሽና ደህና ትሆኛለሽ›› ይሉኛል።




ከሚሉኝ ሁሉ አንዱም ስሜት አይሰጥም፡፡ አንዳች ትርጉም አልነበረውም።
የለውም፡፡


እንዲያው  ለይስሙላ፣ እንዲተዉኝ በምነቀንቀው ጭንቅላቴ ላይ ነጥሮ ይመለሳል፡፡ በሰማሁት ቅጽበት ብንን ብሎ ይጠፋል፡፡



ከልጄ ሞት በኋላ ፣


ለምኜ የማገኘውን እንቅልፍ ሳሎን፣ መሬት ላይ ነው የምተኛው፡፡


መኝታ ቤት የማልተኛው አንድም እንዲመቸኝ ስለማልፈልግ፣ ሁለትም አልጋው፣ ክፍሉ፣ ቤቱ፣ ዓለም ልጄ እዚያ አልጋ ላይ ይተኛ እንደነበር እንዳይረሳ ስለምፈራ ነው፡፡



ምቾትን ማስወገድ አዲሱ ባህሪዬ ነው፡፡


ልጄ አብሮኝ እያለ እሆን እንደነበረው መሆንን እንደ ጦር እፈራለሁ፡፡ ነጋ ጠባ ጉድለቱ እንዲሰማኝ፣ እጦቱ እንዲያሳምመኝ ነው የምፈልገው፡፡




የሚጣፍጥ ነገር አፌ አላደርግም፤ ሙዚቃ አላዳምጥም፡፡
ሳቅና ፈገግታን ሊያጭር ከሚዳዳው  ነገር እቆጠባለሁ።


ሙሉ ሰው ሆኖ መኖርን፣ ሕያው ሆኖ መገኘትን ስራዬ ብዬ እሸሻለሁ፡፡




‹‹አይዞሽ ጠንከር በይ›› ይለኛል ሁሉም ሰው።
‹‹እግዚአብሔር ሰጠ። እግዚአብሔር ነሳ።›› ብለው ቃሉን ይጠቅሱልኛል፡፡
‹‹ምነው ታዲያ እኔን ሳይጠይቀኝ ነሳ?›› ብዬ እጠይቃለሁ፡፡





ባለቤቴ ብዙ አይናገርም፡፡
ከጥቂት ሳምንታት በፊት እንደገና መጸለይ ጀመረ። ወደ

ጣሪያው አንጋጦ ሲያጉረመርም አየሁት፡፡.


‹‹ፈጣሪ ሆይ እባክህ›› እያለ አምላኩን ሲማፀን፡፡
እባክህ…?
እባክህ ምን?


እባክህ ብሎ በመማጸኑ ኢየሱስ ፣ “አልዓዛር ተነሳ!” ብሎ  ሲያዘው የሞተው አልዓዛር በጨርቅ እንደተጠቀለለ ከመቃብሩ እንደወጣ የእኛም ብላቴና ከሞት ይነሳል ብሎ ነው….?




‹‹ጠንካራ መሆን አለብን›› ይለኛል።

‹‹መበርታት አለብን››


"ለምንድነው የምንጠነክረው…ለማን ነው የምንበረታው?" ብዬ እጠይቃለሁ።


መጠንከራችን ምን ሊፈይድ?
በሕይወቴ ያገኘሁት ብርቅ ስጦታ ድንገት ተመንትፎብኝ ሲያበቃ
ልበታተን እንጂ…ልሸረካከት፣ ልበጣጠስ እንጂ…እንክትክት ልበል እንጂ 
መጠንከሬ ምን ሊያመጣ…?




አንዳንድ የሩቅ ሰዎች አሁን ድረስ ደውለው ‹‹ልጅሽ እንዴት ነው?›› ብለው ይጠይቁኛል፡፡


ያልሰሙት መሆናቸው ነው፡፡


‹‹አሁንማ ታናሽ ወንድም ወይ እህት ይፈልጋል…ውለጅለት እንጂ›› ይሉኛል፡፡


‹‹ ትምህርት ቤት ገባ?›› ብለው ይጠይቁኛል፡፡


ያን ጊዜ ‹‹አዎ መላእክት እያስተማሩት ነው›› እላለሁ፡፡



ግራ ተጋብተው ይስቃሉ።




ስልኩን እዘጋለሁ፡፡


ቆይተው (ሲሰሙ) ይደውላሉ፡፡
አላነሳም፡፡ ደግሜ ከእነሱ ጋር አላወራም፡፡





--
በፊት በፊት ህልም ብዙ አላይም ነበር፡፡
አሁን ግን እንቅልፍ እሺ ብሎ ከወሰደኝ ሳላልም አልነቃም፡፡


ህልሙ ደግሞ ሁሌም አንድ አይነት ነው፡፡  ጥቃቅኗ ነገር እንኳን ሳትዛነፍ ትደገማለች፡፡


ወሊሶ ያለው የእናቴ ቤት የአትክልት ስፍራ ውስጥ ቆሞ አየዋለሁ፡፡
ልጄን፡፡


በባዶ እግሩ። ቢጫ ኳሱን ጭምድድ አድርጎ ይዞ፡፡
የአቮካዶ ዛፉ አፍርቷል፡፡ እሱ ስር ነው የሚቆመው፡፡




ልጄ እጁን አያውለበልብልኝም፡፡
አይነቃነቅም፡፡ ግን በዝምታ ትክ ብሎ ያየኛል፡፡


‹‹ልጄ …መንግስተ ሰማያት ብንገናኝ ስሜን ታስታውሰዋለህ?›› ብዬ ጮክ ብዬ እጠይቀዋለሁ፡፡



መልስ አይሰጠኝም፡፡ ግን ይሄንን ጊዜ ትከሻውን ወደላይ ይሰብቃል። በግዴለሽነት፡፡



ገና ካሁኑ ስሜን እንደረሳው ሁሉ፡፡



ከዚያ እባንናለሁ፡፡



ትንፋሼ እየቆራረጠ እነሳና መኝታ ቤት ብገባ ከሚወዳት ቀይ ባለ ነጭ ዳክዬ ካልሲው ውጪ ሌላ ካልሲ አላደርግም ብሎ ሲነጫነጭ፣ ጫማውን ሳያስር ለመሮጥ ሲያኮበኩብ ወይ ደግሞ ራበኝ ብሎ ለቁርስ ወደሳሎን ሊሮጥ ሲል  የማገኘው ይመስለኝና ስበር እሄዳለሁ፡፡



ሳጣው ሁሉ ነገር እንደ አዲስ ይገባኝና ሳሎን መሬት ላይ ተኮማትሬ እምባ የሌለው ለቅሶዬን እጀምራለሁ፡፡


ቦይ የተቀደደለት እምባዬ አልቋል፡፡

የእምባ ከረጢቴ ደርቋል፡፡ለቅሶዬ ግን አላባራ ብሏል፡፡




የዚያን እለት ጠዋት ለመጨረሻ ጊዜ ያልኩትን ነገር ለማስታወስ እታገላለሁ፡፡
አስፋልት ላይ ከመውጣታችን በፊት፡፡ ከእጄ አፈትልኮ ከሚበር መኪና ጎማ መሃል ከመግባቱ በፊት፡፡ ከ ሲጥጥጥጡ በፊት፡፡

ጫማህን አላሰርክም ይሆን ያልኩት?
ወይስ ምንም አላልኩትም ?
ስልክ ይዤ ነበር እንዴ…?
ልቤ ከእሱ ጋር አልነበረም እንዴ?




እናቴ ‹‹ከእግዜር ተጣልቶ እስከመቼ? …ልብሽን ወደ ፈጣሪሽ መልሺ…ሰላምሽን አግኚ››
‹‹በእግዜር ላይ ማመፅ ትርፉ ገሃነም ነው ልጄ›› ትለኛለች፡፡

‹‹ታዲያ አሁንስ ገሃነም አይደል እንዴ ያለሁት?›› እላታለሁ፡፡



ካለ ልጄ ሰላም የለም፡፡
ካለ እሱ እቅድ፣ ወደ ፊት የለም፡፡
እንኳን የምድሩ ነገርና እንዲህ አንጀት በስለት የሚቆርጥ ልበ ደንዳና ፈጣሪም የለም፡፡




አሁን በእኔ ዓለም ውስጥ  ያሉት ሁለት ነገሮች ልጄ ዳግመኛ የማያደርገው ካልሲና እያደር የሚፋጅ ረመጥ የታቀፈች እናቱ ናት፡፡



ስለዚህ የሚወደውን ካልሲውን በጥንቃቄ ይዣለሁ፡፡
በተኛሁ ቁጥር ለጥያቄዎቼ መልስ የማይሰጠኝ ልጄን በህልሜ አያለሁ፡፡




ልጄ ሳልንገዳገድ እንድቆም ያግዘኛል?
ምክንያቱም ካለ እሱ እራሴን ችዬ መቆም አልቻልኩም።


ልጄ አሁንም እናቴ ይለኝ ይሆን? ምክንያቱም የእሱ እናት ካልሆንኩ ማን እንደሆንኩ አላውቅም፡፡

ከሁሉ በላይ ግን አዳልጦኝ በመውደቅ ፈንታ፣ ተደናብሬ በመጠለፍ ፈንታ፣  ፈጥኜ ደርሼበት፣ እጁን ይዤ ሳላላዳንኩት ይቅር ይለኛል…?




"ጊዜ ብዙ ቁስልን ይፈውሳል" ይላሉ።


እንደ እኔ ግን ጊዜ ባለጌ ነው፡፡ ባገኘው አጋጣሚና ቦታ በአዲስ መልክ ቁስል ላይ እንጨት ይሰዳል፡፡


ጊዜ በልጄ ጉዳይ እያደባ ብዙ ጊዜ አጥቅቶኛል፡፡



ኩሽና ስገባ ተጥሎ የተረሳ የልጅነት የፕላስቲክ ማንኪያውን ያሳየኛል፡፡
መኝታ ቤት ስገባ ባገጠጠ የጸጥታ ጥርሱ ቀርጥፎ ይበላኛል፡፡
መታጠቢያ ቤት ስገባ አልጥልም ብዬ ያስቀመጥኩትን ፖፖውን እዩ ብሎ ከእንግዲህ የማያድግ ልጄን ያስታውሰኛል፡፡



በህልሜ እያሳደደ የማይናገር ልጄን አኩርፎ ያሳየኛል፡፡



ሰው ሁሉ
‹‹እግዚአብሔር ሰጠ
እግዚአብሔር ነሳ››
ይለኛል፡፡



እኔ ግን እላቸዋለሁ፤
‹‹እግዚአብሔርን ልጅ ስጠኝ ብዬ ለመንኩት፡፡

ሰጠኝ፡፡

ግን ‹‹አቅፈሽና ስመሽ ጠገብሽው ወይ?›› ብሎ ሳይጠይቀኝ፣ ሳያዘጋጅና ሳያማክረኝ ያንኑ ልጅ ነሳኝ፡፡ ››
‹‹አብረን ባለን ጊዜ››
-------


ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኘነው ታወን ስኩዌር ሞል ጋር ነው። 22 ማዞሪያ፡፡

ዣንጥላሽን ስላልያዝሽ ድንገት የመጣው ዝናብ እስኪያባራ ድረስ የህንጻው መግቢያ ጋር ተጠልለሽ፡፡
እኔ አንዱ ሱቅ መስታወት አጠገብ ነበርኩ፣ አላፊ አግዳሚውን እያየሁ፡፡



ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ፈገግ ብለሽ ተጠጋሽኝ፡፡
ፈጣን ነበርሽ፣ ቀልጣፋ፡፡ ጊዜ ሳትፈጂ ወደ ቤትሽ ይዘሽኝ ሄድሽ፡፡



አብራሽ የምትኖረው እህትሽ አልወደደችኝም።
ገና በዝናብ የራሰ ጃኬትሽን አውልቀሽ እንዳስተዋወቅሽን ከላይ እስከታች ተመለከተችኝና፣
‹‹ የማያዛልቅ እንደሆነ ያስታውቃል›› ብላ ሸረደደችሽ፡፡



ሳቅሽና፣ ‹‹ድሮ ማን ለዘላለም ይሆነኛል አለሽ!›› ብለሽ መለስሽላት፡፡


እህትሽ ገና በአግባቡ ሳታውቀኝ እንደዚህ ብላ ብታንቋሽሸኝም፣ አንቺም ለጊዜው እንጂ ለእስከወዲያኛው እንዳልፈለግሽኝ በግልጽ ብትናገሪም ልሂድ አላልኩም፤ ቆየሁ።




----
ቀኖቹ ወደ ሳምንታት ሲሸጋገሩ በጣም፣ እጅግ በጣም ተላመድን፡፡
አንቺም ካሰብሽው በላይ እንደወደድሽኝ አሳበቀብሽ፡፡



ሁሉም ቦታ አብረን ነው የምንሄደው - ምኒሊክ ሆስፒታል የሀሞት ከረጢት ቀዶ ጥገና ተደርጎላቸው የተኙት አባትሽን ለማየት፣ ሃዲድ ገበያ ቦንዳ ልብስ ለመግዛት ፣ ሴንቸሪ ሞል ሲኒማ ቤት ፊልም ለማየት፣ ሾላ ገበያ አዳዲስ የሻይ ብርጭቆና እና መሶበወርቅ ለመግዛት ፣ ከበደ ገብረወልድ ስጋ ቤት ከጓደኞችሽ ጋር ጥሬ ስጋ ለመብላት ፣ስዊት ወርልድ ከአክስትሽ ልጅ ጋር ኬክ በማኪያቶ ለመብላት
….ያልሄድንበት የለም፡፡



ዝናብ ሆነ ጸሃይ፣ ሙቀት ይሁን ቆፈን ሰው እስኪታዘበን ድረስ ሁሉም ቦታ አብረን ታየን፡፡ አንለያይ አልን፡፡


በዚህ የተገረሙ ጓደኞችሽ፣ የሔዋንን ‹‹ከምኔው ከምኔው›› በማሾፍ እየዘፈኑ ‹‹ምነው እሱ ላይ ብቻ ሙጭጭ አልሽሳ?›› ሲሉሽ እንኳን
‹‹እኔን ከተመቸኝ ምን አገባችሁ?› ›› ትያቸው ነበር፡፡


ከዚያ ግን ነገር ተሳከረ፡፡


ካለ እኔ ወጣ ወጣ ማለት ጀመርሽ፡፡
እኔን ተራምደሽ መሄድ ለመድሽ፡፡
በፊት እንደምትነካኪኝ አትነካኪኝም፤ በፊት እንደምትነከባከቢኝ አትንከባከቢኝም፡፡
ይባስ ብለሽ ለአንደኛዋ የስራ ባልደረባሽ ሰርግ አይኔ እያየ፣ እኔ እያለሁ ከሌላ ጋር ሄድሽ፡፡


የዚያን ቀን መሽቶ ከሰርጉ ስትመለሺ ተጎሳቁለሽ ገባሽና በጥፋተኝነት ስሜት አየሽኝ፤ የተጎዳው ስሜቴን ግን አላከምሽውም፡፡



አንዱን ቅዳሜ ግን ከመሬት ተነስተሸ በፊት ታይኝ እንደነበረው አየሽኝ፡፡
ችላ ብለሽኝ እንዳልከረምሽ ሁሉ በስስት ተጠጋሽኝና ወክ ለማድረግ ወጣን፡፡

ከፊጋ ሲኤምሲ ያለውን መንገድ አርዝመን ከፈጨን በኋላ ወደ ቤት ስንመለስ መንገድ ላይ የብርሃኑ ዘሪሁንን አሮጌ መጽሐፍ ገዛሽ፡፡ ፊትሽ ላይ የነበረው ደስታ ተጋባብኝ፡፡

እፎይታ አገኘሁ። የቀድሞ ፍቅራችን ተመለሰ ብዬ መንፈሴ ተረጋጋ፡፡




---
ከጥቂት ቀናት በኋላ ግን ያልጠበቅኩት ሆነ፡፡
በሰላም ቤትሽ ተቀምጠን እያለ ድንገት ተነሳሽና ተመላላሽ ሰራተኛችሁን ዘሪቱን ጮክ ብለሽና ደጋግመሽ ጠርተሸ እንደዋዛ-


‹‹እንኪ ውሰጂው›› ብለሽ ሰጠሽኝ።

ዘሪቱ ደጋግማ ‹‹እግዜር ይስጥልኝ›› አለችሽና እንደመስገድ አደረጋት።





አሁን ከዘሪቱ የእንጨት አልጋ ስር አቧራ እየጠጣሁ ተቀምጫለሁ።
ዘሪቱ ቤቷ አዲስ ሰው በመጣ ቁጥር ሳብ አድርጋ ታወጣኝና፣

‹‹እዩትማ….! ዳጊዬ እኮ ይሄን የመሰለ ትንሽ ብቻ ያደረገችውን ስኒከር ጫማ ነው የሰጠችኝ…ጥሩ ሴት አይደለች…›› ትላለች፡፡

ያ ደግሞ በዝምታና በጨለማ አብረን ባለን ጊዜ ስላሳለፍነው ደስታ እያሰብኩ አቧራ ከመቃሙ በላይ ያበሳጨኛል፡፡
‹‹መልስ››
----
ጥምቢራው እስኪዞር፣ እስኪንበዛበዝ ይሰክራል።
ጫት በየቀኑ ይቅማል።
የሚጨሰውን ሁሉ ያጨሳል።
ባገኘው ነገር ይቆምራል።
ሌላ ሴት ጋር ይሄዳል።


ሚስቱ ሳትታክት፣ ሳትሰለች " እግዜር ልቡን እንዲመልሰው፣ መረጋጋት እንዲያድለው›› ትጸልይለታለች፡፡

ለአንድ ወር ሁሉን ነገር እርግፍ አድርጎ ይተዋል፡፡
ከዚያ ግን መልሶ
ጥምብራው እስኪዞር፣ እስኪንበዛበዝ ይሰክራል።
ጫት በየቀኑ ይቅማል። የሚጨሰውን ሁሉ ያጨሳል። ባገኘው ነገር ይቆምራል።
ሌላ ሴት ጋር ይሄዳል።

ጓደኞቿ፣ ‹እስከመቼ ይሄን ሁሉ ችግር በጸሎት ታባርሪያለሽ…?›› ሲሏት፣
‹‹ሁሉም ነገር አንድ ቀን ይስተካከላል…አሁን ላይ እግዜር በእሱ ጉዳይ እየፈተነኝ ነው ›› ብላ ትመልሳለች፡፡

በማያልቀው ትእግስቷ እየተደነቁ፣ አንገታቸውን በስምምነት እየነቀነቁ በልባቸው ግን ፣
‹‹አንቺ አልገባ አለሽ እንጂ እግዜርማ በዚህ ሰውዬ ጉዳይ እየፈተንሽ ሳይሆን መልስ እየሰጠሽ ነው ›› ብለው ያስባሉ፡፡
እፈልጋለሁ…
-----

በስድስት ዓመቴ…
እሁድ በመጣ ቁጥር እናቴ ጉልበቶች መሃከል ተሰንጌ ጸጉሬ እየተጎተተና እየተነጨ፣ እያመመኝና ‹‹እስቲ ቀጥ ብለሽ ተቀመጭ›› ተብዬ እየተቆጣሁ ከማለቅስ እንደ እናቴ የውበት ሳሎን ሄድ ብዬ ጸጉሬን መተኮስ እንድችል ቶሎ ማደግ ፈለግኩ ፡፡


በስምንት ዓመቴ…
የአክስቴ አይነት ታኮ ጫማ አድረጌ በየሄድኩበት ሁሉ ቀጭ ቋ እያልኩ አላፊ አግዳሚውን እንዳስገርም ቶሎ ማደግ ፈለግኩ ፡፡


በዘጠኝ ዓመቴ…
ባሰኘኝ ሰአት ሚሪንዳ እንድጠጣ እና አቡወለድ እንድበላ ፣ ቁርስ፣ ምሳ፣ መክሰስና እራቴን ብስኩት በለስላሳ እንዳጣጥም፣ ጦር ማስቲካ ነፍቼ ጮክ አድርጌ እንዳፈነዳ ቶሎ ማደግ ፈለግኩ፡፡


በአስር ዓመቴ…
ታላቅ እህቴን የሚያብለጨልጭ ቻፒስቲኳን ቀቢኝ ስላት፣
"ልጅ አይቀባም" ስትለኝ አድጌ እንደዚህ አይነቱን ቻፒስቲክ ከንፈሬን ለመለቅለቅ ስል ቶሎ ማደግ ፈለግኩ፡፡


በአስራ ሁለት ዓመቴ..
ዝናብ እየዘነበ ወጥቼ ልጫወት ስል፣
‹‹በኋላ ብርድ ይመታሻል፤ አርፈሽ ቤት ተቀመጪ›› እንዳልባል
ጓደኛዬ ቤት ሄጄ የፈለግኩትን ያህል እንድቆይ ቶሎ ማደግ ፈለግኩ፡፡


በአስራ አራት ዓመቴ…
ጓደኛዬ ጋር ለመሄድ፣ ከእሷ ጋር ስጫወት ለመቆየት፣ ዘመድ ጥየቃ ሄደን ወደቤታችን መሄድ ስፈልግ እንሂድ ብዬ እሺ ለመባል ቶሎ ማደግ ፈለግኩ፡፡


በአስራ አምስት ዓመቴ..
አክስቴ የምትቀባውን ደማቅ ቀይ ሊፕስቲክ ተቀብቼ ሳላስለቅቅ ለመዋልና ለማደር፣ ስፖንጅ ያለው ጡት መያዣን ለማድረግ ቶሎ ማደግ ፈለግኩ፡፡
እናቴ ይሄን ይሄን ስትሰማ..
‹‹ አይ ለማደግ መንቀዥቀዥ…! ትልቅ ሰው መሆን ዋዛና ፈዛዛ - እንደ ልብ መኖር ብቻ መስሎሻል›› አለችኝ፡፡
አዎ…መስሎኛል፡፡ ይመስለኛል፡፡


ከቁም መስተዋቱ ፊት ለፊት ተገትሬ ነበር፡፡
እናቴ እንደምትቆመው ለመቆም ሞከርኩ፡፡ ቦርሳዋን እንደምታነግበው አነገብኩ፡፡ የጆሮ ጉትቻዎቿን አደረግኩ፡፡

እናቴ ስታየኝ፣
‹‹አንቺ ልጅ በቃ የእኔን እቃ መጫወቻ አደረግሽው አይደል…ምን እንዲህ አስቸኮለሽ…ትደርሺበት የለ›› ብላ ተቆጣችኝ፡፡
እንደራሴ የምቆምበት፣ የራሴን ቦርሳ የማንጠለጥልበት፣ የመረጥኩትን የጆሮ ጌጥ የማደርግበት ጊዜ እየናፈቀኝ በሆዴ እንዲህ አልኩ፤
‹‹አዎ እስካድግ ቸኩያለሁ››



በአስራ ስምንት ዓመቴ…
እንዳሰኘኝ ፣ በፈለግኩት ሰአት ያለ ቁጥጥር፣ ግልምጫና ቁጣ ለመግባትና ለመውጣት
ወይ ደግሞ አልጋዬ ላይ ተጋድሜ ለማርፈድ
ወይ ደግሞ የምወደውን ልጅ ቀጥሬ ለማግኘት፣ ወይ ደግሞ ከእሱ ጋር ሁሌም፣ ቀንና ሌሊቱን ለማሳለፍ ቶሎ ማደግ ፈለግኩ፡፡

--------
በሃያ አምስት ዓመቴ…


አሁን አድጌያለሁ፡፡
ስራ ይዣለሁ፡፡
ጸጉሬን እንዳሻኝ እተኮሳለሁ፡፡
ግን ቶሎ ቶሎ የውበት ሳሎን መመላለስ ጠልቻለሁ፡፡
ውድ ነው፡፡ አሰልቺ ነው፡፡
ስለዚህ በመተኮስ ፈንታ ጸጉሬን እታጠብና ወደ ኋላ ሙልጭ አድርጌ አስረዋለሁ፤ ወይ ደግሞ እንደ ተንጨበረረ እተወዋለሁ፡፡


ፍላት ጫማ አዘወትራለሁ፡፡
ሂል ጫማ ከሩቅ እዩኝ እዩኝ ለማለት የምፈልግ ያስመስለኛል፡፡ በዚያ ላይ አማረብኝ ብዬ ስወላገድ መዋል ታከተኝ፡፡ ህመሙስ!
ሚሪንዳና አቡወለድ ማብዛቴ ቅጥነቴን እየተፈታተነው ነው፡፡
------

በሃያ ሰባት ዓመቴ…

ከስራ በኋላ ንትብ ብዬ እደክማለሁ፡፡
የማይረባ ምግብ አፌ አደርጋለሁ፡፡
ሊፕስቲክ እቀባለሁ፤ ግን ከንፈሮቼን አይቶ የሚያደንቃቸው የለም፡፡
የራሴ ገንዘብ አለኝ ግን ገና እጄ ገባ ስል ብርር ብሎ ይጠፋል፡፡

-----
በሃያ ዘጠኝ ዓመቴ..

‹‹ለጋብቻ ዝግጁ አይደለሁም›› አለኝ፡፡
‹‹አጣደፍሽኝ እኮ›› ብሎ ከሰሰኝ፡፡
‹‹ምናልባት ወደፊት..አንድ አምስት አመት ስጪኝ›› ብሎ አላገጠብኝ፡፡

የምለው ጠፍቶኝ ጥዬው ሄድኩ፡፡
በውጪ ልብሴ ተኛሁ፡፡
አፒታይቴ ጠፋ፡፡
በማፈቅረው ሰው የልቤ መሰበር ፊቴ ላይ ተጽፎ ለሰው ሁሉ እስኪታይ ተጎዳሁ፡፡
----

ዛሬ እሁድ ነው፡፡
ያገባኛል፣ አገባዋለሁ ካልኩት ሰው ሳልወድ ከተለየሁ ሶስት ቀናት አለፉ፡፡
ጸጉሬ ተንጨፍርሯል፡፡
ስልኬ ተዘግቷል፡፡
ምግብ አልበላሁም፤ ሚሪንዳም አልጠጣሁም፡፡

እግሮቼን አነባብሬ መሬት ላይ ተቀምጫለሁ፡፡
እዚሁ…መንፈሴ እንክትክት ብሎ በተቀመጥኩበት…ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲህ ብዬ ተመኘሁ…

‹‹ድጋሚ ልጅ መሆን እፈልጋለሁ››
‹‹ትንሽ ቅና››
-------

መሽቷል፡፡ ጥንዶቹ ሳሎናቸው ሶፋ ላይ ተቀምጠው ያወጋሉ፡፡

–ውይ ዳኒዬ…ሳልነግርህ ረስቼው…ነገ ማታ ከኤልያስ ጋር እራት ቀጠሮ አለኝ፡፡

– ኤልያስ ኤልያስ?

–የዩኒቨርስቲ ጓደኛዬ ኤልያስ? ሁሌ አነሳው የለ…ረሳኸው እንዴ..? ለትንሽ ቀን አዲሳባ መጥቷል፡፡

– እሺ

– እሺ?

–አዎ …ትንሽ ፈታ በይ፡፡

–እራቱን ሌላ ማን ይመጣል ብለህ አትጠይቀኝም እንዴ?

–ለምን እንደዚያ ብዬ እጠይቅሻለሁ?

– እኔንጃ…ለማወቅ?

–እውነቱን ንገረኝ ካልሽኝ ስለእሱ ግድ የለኝም፡፡

–እሺ..ቢያንስ ግን እራቱን የት ነው የምትበሉት ብለህስ አትጠይቀኝም?

– እሺ…የት ልትበሉ አሰባችሁ?
–ቤላ ፓስታ ፡፡

–አሪፍ…እዚያ ቤት ምግባቸው ያበደ ነው፡፡

–ሆ እሺ…ታመሻለሽ ምናምንስ አትለኝም?

–አልልሽም…አምንሻለሁ ፍኖትዬ፡፡

–ግን ላመሽ እችላለሁ… አዲስባ ከመጣ ሁለት አመት አልፎታል…ግርግሩ ምናምኑ ይናፍቀዋል መቼስ…ስለዚህ ከእራት በኋላ አንድ ሁለት እንበል ሊለኝ ይችላል፡፡

– እንደዚያ ካለሽ አንድ ሁለት ማለት ነዋ ታዲያ! ዘና ፈታ በይ አልኩሽ እኮ…የፈለግሽውን አድርጊ…አምንሻለሁ፡፡

–ግን እኮ አንድ ቀን እንኳን አግኝተኸው አታውቅም…

–ዌል…ሌላ ጊዜ እናመቻችና እንተዋወቃለና…

–በል ተወው እንደውም አልሄድም!

– አልሄድም ማለት?

–አልሄድም ማለት አልሄድም ማለት ነዋ!

–እንዴ…ጓደኛሽስ…ኤልያስስ?

–በቃ እደውልና የሆነ ያልተጠበቀ ነገር ስላጋጠመኝ አልችልም እለዋለሁ፡፡

–ምንድነው ያልተጠበቀ ያጋጠመሽ ነገር?

–እጮኛዬ ለእኔ ያለው ፍቅር እንደተሟጠጠ ማወቄ ነዋ!

–አቤት ጌታዬ…ምኑን ከምኑ አገናኝተሽ ከምኔው እዚህ ጋር ደረስሽ…? ልዩ ችሎታ ነው ይሄ…

– አታሹፍ…በቃ ትንሽ እንድትቀና ፈልጌ ነው…ይሄን መፈለጌ ሃጥያት ነው? ተወው በቃ…ነገም ካንተ ጋር አመሻለሁ በቃ…ወይ አብረን እራት እንወጣለን፡፡

–ቆይ ቆይ…ቅናትን እዚህ ምን አመጣው? ለምንድነው እንድቀና የፈለግሽው..?

–እኔንጃ…በቃ…እንደምታፈቅረኝ ለማወቅ …

–ማፍቀሩንማ ልቤ እስኪጠፋ አፈቅርሻለሁ…

–እሱንማ አውቃለሁ ግን ትንሽ የቀናህ ብትመስል ትሞታለህ…? ለእኔ ብለህ…እኔን ደስ እንዲለኝ?

–ገባኝ…እሺ …እንደዚያ ከሆነ ከመጀመሪያው እንጀምር…

–ማለት?

–በቃ አንቺን ደስ እንዲልሽ ስለ ነገሩ እንደ አዲስ እናውራና ሌላ አይነት መልስ ልስጥሻ…

–አታሹፍብኝ ዳኒ

– እውነቴን ነው ፍኖትዬ… እንደገና ጀምሪ…ምን ነበር ያልሽኝ ይሄን ወሬ ስንጀምር…?

–ሆሆ ዳኒ ይሄን ያህል እንኳን እብድ አታድርገኝ…ተወው…ያን ያህል በቅናት ስትንጨረጨር ማየት አላጓጓኝም …

–ተይ ተይ መጓጓትሽማ ያስታውቃል..ይልቅ አሁን እንደገና ጀምሪ…ምንድን ነበር ሳትነግሪኝ የረሳሽው?

–ኦኬ…እኔ የምልህ ዳኒዬ ሳልነግርህ ረስቼው…ነገ ማታ ከኤልያስ ጋር እራት ቀጠሮ አለኝ…
–ኤልያስ? ማናባቱ ነው ኤልያስ ደግሞ?

–ሃሃሃሃሃሃ

–ምን ያስቅሻል…? ማነው እሱ ኤልያስ?

–የዩኒቨርስቲ ጓደኛዬ ነዋ…ያ እንኳን ዶክተሩ? ወላይታ የሚሰራው? ስንቴ አውርቼልህ የለ ስለእሱ?

–ታዲያ እሱ ሶዶ አይደል እንዴ የሚኖረው? አዲሰባ ምን አባቱ ያደርጋል?

–ለኮንፈርንስና እረፍት መጥቶ ነው…

–ጥሩ ..አርፎ ኮንፍረንሱን ይሂድ ዝም ብሎ ይረፋ ታዲያ…ለምን አንቺን ማግኘት ፈለገ?

– ጓደኛሞች እኮ ነን ዳኒዬ…
–ቆይ ቆይ….ኤልያስ ማለት ያ ፌስቡክ ላይ ከለጠፍሻቸው የቀለበታችን ፎቶዎች መሃል እኔ የሌለሁበትን እየመረጠ ላቭ ሲል የነበረው ኤልያስ እንዳይሆን?

–አንተ በስመአብ! …ባንዴ አከረርከው እኮ ሃሃሃሃ..

–እሱ ነው ወይስ አይደለም?

–እሱ ነው ግን ያው ላገባህ እንደሆነ ያውቃል…ዝም ብለህ እንደ እብድ አትሁን…

–እኔ እብድ አይደለሁም ግን ነገሩ ደስ አላለኝም….ለመሆኑ ካንቺ ውጪ ማን ይሄዳል እራቱን?

–እኔንጃ…ግን እኔና እሱ ብቻ መሰለኝ የምንገናኘው..

–ምን?

–እንደዛ ቢሆን ችግር አለው?

–አዎ አለው! ገርልፍሬንድ አለው?

–እኔንጃ…በፊት ነበረችው፡፡

– አዲሳባ ነው የምትኖረው?

– አይደለም…

–አሄሄ…ፍኖትዬ…የግድ መሄድ አለብሽ?

–እንዴ አዎ…ጓደኛዬ እኮ ነው…ላገኘው እፈልጋለሁ…በዚያ ላይ አንዴ እሺ ብዬው የለ እንዴ?

–እንዲህ አይነት ነገር ላይ ከመወሰንሽ በፊት ከእኔ ጋር መመካከር የለብሽም? እ?

–ሃሃሃ በል ይበቃሃል…በቃ ዳኒዬ!

–ይሁና እንግዲህ…ራስሽን ጠብቂ ፍኖትዬ…ለመሆኑ እራቱን የት ነው ምትበሉት?

–ቤላ ፓስታ፡፡

–የምርሽን ነው? የእኔና ያንቺ ቤት ይዘሽው ልትሄጂ ነው? ፍኖትዬ…

–ዳኒ ደሞ! ሶስቴ የበላንበትን ሬስቶራንት ነው የእኛ ቤት የምትለው?

–ኦኬ ይሁንልሽ…ግን ብዙ እንዳታመሺ..እራትሽን በልተሽ ቀጥ ብለሽ ወደ ቤትሽ!

–እ…ከእራት በኋላ መጠጥ ምናምን እንጠጣ ሊለኝ ይችላል ዳኒ ስለዚህ ትንሽ ላመሽ እችላለሁ…
–መጠጥ ? ፍኖት የምርሽን ነው?

–. ሃሃሃሃሃ…ጎበዝ የኔ አንበሳ…ሃይለኛ ተዋናይ ወጥቶህ የለ እንዴ! ግሩም ኤርምያስ መች እንዳንተ ይተውናል ? ሃሃሃሃ…በል አሁን የምር ይበቃሃል! በቃ! በቃ !

---
(ሳቋ ሳያባራ ግንባሩ ላይ ሳም አደረገችውና ወደ መኝታ ቤታቸው አመራች)

ዳኒ ስልኩን አነሳና የሚከተለውን የጽሁፍ መልእክት ለልብ ጓደኛው ጽፎ ላከ፡፡


‹‹ብሮ ጉድ ሆኜልህ ነበር…! የነገው ወሳኝ ጨዋታ ሊያመልጠኝ ነበር…እንዴት በመከራ እንዳመለጥኩ! አስበኸዋል ይሄ ጌም ሲያመልጠኝ…? በል ነገ ሰው ሳይበዛ ቦታችን ላይ እንገናኝ፡፡ ለእነ ወንዴም እንደባለፈው እንዳታረፍዱ እራት እዚያው አለ በላቸው››
‹‹እማዬን ሳክል››
-----

አባት ከትንሽ ሴት ልጁ ጋር ቁጭ ብሎ ይጫወታል፡፡




o  አበባ፣ እኔም እንዳንተ እና እንደ እማዬ እንደዚህ አይነት የሚያምር ቤት የሚኖረኝ ይመስልሃል?

o  ምን ማለትሽ ነው? ቆንጆ ቤትማ አለሽ፡፡ ይሄስ ቤትሽ አይደለም እንዴ?

o  አይ ሳድግ… ትልቅ ስሆን…ከዚህ ቤት ወጥቼ ሌላ ቤት እሄድ የለ?

o  ለምን ሌላ ቤት ትሄጃለሽ?

o  እንዴ አባባ ደግሞ…ያኔ እማዬን ሳክል እኮ ነው የምልህ

o  እማዬን ሳክል ማለት ምን ማለት ነው?

o  ትልቅ ሰው ስሆን ነዋ!

o  እና ቢሆንስ ለምን ሌላ ቤት ትሄጂብኛለሽ…?

o  እማዬን ሳክል እሷ ያላት ነገር ይኖረኛላ…

o  እማዬ ምን አላት?

o  እንዴ አባባ? ….ባል ነዋ፡፡ እንደ አንተ አይነት ባል  ይኖረኛል…

o  ሃሃ…ወይ አንቺ ልጅ! ባልማ አይኖርሽም

o  አሁን እኮ አይደለም ትልቅ ስሆን ነው የምልህ…

o  ያኔም ቢሆን ልጄ እኮ ነሽ…

o  ግን እኮ እማዬን አክላለሁ..ስለዚህ ባል ይኖረኛል

o  ወይ ጉድ! እናያለና እንግዲህ!

o  አበባ?

o  ወዬ የእኔ ወርቅ…

o  ስለዚህ ትልቅ ስሆን የእኔም ቤት እንደዚህ ቆንጆ ይሆናል ብለህ ታስባለህ?

o  እንዲሆንልሽ ነው የምፈልገው የእኔ አበባ …

o  ባሌስ እንዳንተ አይነት የሚሆን ይመስልሃል…?

o  ወይ መከራዬ…እሱን በምን አውቃለሁ ልጄ?

o  አባባ እኔ ግን አንተን በጣም ስለምወድህ ባሌ ልክ እንዳንተ እንዲሆንልኝ ነው የምፈልገው…

o  ወይ አንቺ ጉደኛ ልጅ…ነይ እስቲ ልሳምሽ…



እምዋ!



o  አባባ ሌላ ጥያቄ አለኝ።

o  ያንቺ ጥያቄ ማለቂያ የለው…በይ እሺ ጠይቂኝ…

o  አንተ እማዬን እንደምትመታት የእኔም ባል እኔን የሚመታኝ ይመስልሃል?




ክፉኛ ደነገጠ፡፡
ሁለመናው ከውስጥ ሲደርቅ ተሰማው፡፡
አፉ አልከፈት፣ ምላሱ አልላወስ አለው፡፡

ልጁ የስሜት ለውጥ ሳታሳይ ብድግ ብላ አቀፈችውና በሩጫ ወደ ቤት ገባች፡፡

ሊከተላት ፈልጎ ነበር፤ ጉልበቱ ግን ላመበት፡፡
‹‹የጥሎሽ ትዝታ››
--------

የጥሎሽ ሥነ ሥርዓት የማይቀር የሰርግ አካል በነበረ ዘመን እኔ እድሜዬ ለጋብቻ አልደረሰም ነበር፡፡

ሙሽሪት የእናት አባቷን ቤት ትታ፣

‹‹አይዞሽ ሙሸሪት አይበልሽ ከፋ-
ሁሉም ይዳራል በየወረፋ››

እየተባለ ሳይዘፈንላት በፊት፣ የሆነ ሰውዬ ሚስት ከመሆኗ በፊት ጥሎሽ ሲላክላት፣ እኔ ለጋብቻ ወረፋም ሆነ ሚስት ለመሆን አልደረስኩም ነበር፡፡



ስለዚህ ጥሎሽን ሳላጣጥመው ቀርቷልና ይቆጨኛል፡፡
እኛ ልጆች ሆነን ጥሎሽ ትልቅ ነገር ነበር፡፡


እርግጥ ዛሬ ላይ ሆነው ሥርዓቱን ለሚተነትኑና ለሚመትሩ የሴት ልጅ መብት ተሟጋቾች ሊጎረብጥና ላይዋጥ ይችላል፡፡

‹‹ሴት ልጅ ከብት ናት እንዴ በቅራቅንቦ የምትገዛው?›› ብለው ጥሎሽን በደፈናው የሚያንቋሽሹ አይጠፉም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፣

‹‹ለእኔ የሚገባ ጥሎሽ ከሌለህ፣
እንደገመጀህ ትቀራታለህ›› ብለው የሚዘፍኑና ከዘፈኑት ጋር በስሜት አብረው የሚጨፍሩ ወጣት ሴቶች ዛሬም አሉ፡፡
የሆነው ሆኖ እኔ የማውራው ጥሎሽ እንጋባ ተባብለው በተስማሙ ሁለት አዋቂ ወንድና ሴት መሃከል ስለሚደረገው ነው፡፡ ህጻን ልጅን ቦርቃ ሳታበቃ ሚስት ካላደረግኩ ብሎ ቤተሰቧን በስጦታ ስለሚደልለው አያቷ የሚሆን ሽማግሌ አይደለም፡፡


----

ለመጨረሻ ጊዜ የታደምኩት የጥሎሽ ሥነ ሥርዓት ለጎረቤታችን እትዬ አስናቀች ልጅ ይፍቱስራ የተዘጋጀውን ነበር፡፡

ይፍቱሥራ ‹‹እጹብ ድንቅ የአምላክ ሥራ›› ቢሏት የማይበዛባት ቁንጅናዋ የሚያፈዝና የሚያደነዝዝ ውብ ሴት ነበረች፡፡ እንኳን ወንዱ ሴቱ የሚደመምበት ውበት ነበራት፡፡ ስለዚህ ለይፍቱሥራ የሚላከው ጥሎሽ ምንም ቢሆን ቢያንስባት እንጂ ሊበዛባት አይችልም፡፡


ያም ሆኖ ግን አንድ ልደብቃችሁ የማይገባ ሐቅ አለ፡፡

እኛ ሰፈር ለስም የሚጠራ ሃብታም አልነበረም፡፡ ሁሉም ሮጦ አዳሪ፣ ቧጥጦ ኗሪ ደሃ ነበር፡፡ የይፍቱ ቤተሰብም ያው እንደሌሎቻችን ፎከታም ነው፡፡


ይፍቱ ግን ምስጋና ለዚያ አፍ የሚያስከፍት ውበቷ (እና ሌሎች አጋዥ ተሰጥኦዎቿ) ይሁንና ይህንን የሚያማቅቅ ድህነት አንዱን የአየር መንገድ ሰራተኛ በፍቅር ጠብ አድርጋ አፍንጫህ ላስ አለችው፡፡


እንግዲህ ይሄ ሁሉ የሚሆነው በ80ዎቹ አጋማሽ እንደሆነ ልብ በሉ፡፡ ያ ጊዜ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኞች እንደ ንጉሳዊ ቤተሰብ ነበር የሚታዩት፡፡
ብር አላቸው፣ ክላስ አላቸው፡፡ እነሱም ይህን ስለሚያውቁ በሄዱበት ሁሉ ቁልል እና ቁንን ይሉ ነበር፡፡


አስታውሳለሁ፤ የሙሽራው ሚዜዎች ዘናጭ ሱፋቸውን ከነከራቫቱ ገድግደው፣ ደረታቸውን ነፍተው፣ ሶስት ከአቅማቸው በላይ እንደታጨቁ የሚያስታውቁ ሻንጣዎችን ይዘው ከቀይ ዲኤክሳቸው ሲወርዱ የሰፈር ኩታራዎች እንደ ትንግርት ስናያቸው፡፡

እንዴት አናፈጥባቸው!

ልብሳቸው ሰልቫጅ አይደለም፡፡
በስጦታ ያበጡ ቄንጠኛ ሻንጣዎች ተሸክመዋል፡፡
መኪና ይዘዋል፡፡


እነዚህ ሶስት ነገሮች ለሰፈራችን ፍጹም እንግዳ ነበሩና ብንገረም አይደንቅም፡፡


ከዚያ የአፍሪካ ቀንድን የድርቅ ችግር ለመፍታት ከመለስ ዜናዊ ጋር ስብሰባ ሊቀመጡ እንደመጡ ሁሉ ጥብርር እያሉ ወደ ትንሽዬዋ የእትዬ አስናቀች የቀበሌ ቤት ተግተልትለው ገቡ፡፡


የሰፈር ልጆች ቤት ውስጥ የሚሆነውን ለማየት እንደ ቡችላ ቱስ ቱስ እያልን ከበስተኋላቸው ተከተልናቸው፡፡



እኔና የልጅነት የልብ ጓደኛዬ መቅደስ ቤቱ ውስጥ ማንም አይቶ የማያባርረን መደበቂያ ቦታ ፈልገን አድፍጠን ተቀመጥን፡፡ ትእይንቱን ለመታደም፡፡

የሙሽሪት ቤተሰብ ከጋሽ ገብሬ ቤት በተውሶ ያመጡት ባለ ሶስት መቀመጨ ፎቴ ላይ አራት ሆነው፣ ግጥግጥ ብለው ተቀምጠዋል፡፡ ተጨናንቀው፡፡

ሁለቱ የይፍቱ አክስቶች፣አንደኛዋ የእትዬ አስናቀች የሰፈር ባልንጀራ ሲሆኑ አንደኛዋ ደግሞ ውፍረቷ ከሩቅ የሚታይ የይፍቱ የአጎት ልጅ አምሳለ ነበረች፡፡ አምሳለ ለሌላ ነገር ሳይሆን ለምግብ ብላ የመጣች ይመስል ገና ያልቀረበውን ከጨርቁ መጋረጃ ጀርባ- ጓዳ ያለውን ምግብ ደጋግማ ሰረቅ እያደረገች ስታይ አይቻታለሁ፡፡


የሙሽሪት አጎት ጋሽ በቀለ (አባቷ ከሞቱ ቆይተዋል) ከመከራ የተሰራ የሚመስል ፊታቸውን ይዘው ሌላ ወንበር ላይ ተቀምጠዋል፡፡ ጋሽ በቀለ ከምሽቱ አንድ ሰአት በፊት ሲስቁ አይተን አናውቅም፡፡ ያኔ፣ የደገፋ ጠጅ ቤት ጠጅ መልእክት ሲደርሳቸው ግን ሌላ ሰው ናቸው- ፍልቅልቅ፡፡


እትዬ አስናቀች ሌላኛው ወንበር ላይ ከጋሽ በቀለ አጠገብ በጋቢ ተጀቡና ተቀምጣለች፡፡ ቤቱ ከመጠን በላይ ሰው ይዞ ሙቀቱ አይጣል ነው፡፡ ስለምን ጋቢ ለበሰች?


ከዚያ ሁለት ምላሳቸውን ለወሬ የሳሉ የሙሽሪት ቀጫጭን ሚዜዎች በቆሙበት ሁለቱ ሻንጣዎች የጣውላው መሬት ላይ፣ አንዱ ሻንጣ ደግሞ የሰጠራው ክብ ጠረጴዛ ላይ ተቀመጠና ጥሎሹ ተጀመረ፡፡



እኔና መቅደስ በደስታ ጧ ልንል ደረስን፡፡


የመጀመሪያው ሻንጣ ተከፈተ፡፡

ከፋቹ ስሜ ፈቃዱ፣ የሙሽራው አንደኛ ሚዜ ነኝ ብሎ ያስተዋወቀ መመለጥ የጀመረ ሰውዬ ነበር፡፡


ፍቃዱ በሐገር ፍቅር መድረክ ላይ እንደሚተውን ሁሉ ጮክ ብሎ-

‹‹እንግዲህ ለቆንጆዋ ሙሽራችን ካመጣናቸው ምርጥ ስጦታዎች ሁሉ በላቀው የወርቅ----›› ብሎ ከመጀመሩ ከወሬው ጋር ደባልቆ ጎትቶ ያወጣውን ሃብል አንደኛዋ አክስት ነጠቀችው፡፡


እንዴ….ምን ነካት?

የነጠቀችውን ሃብል እንደያዘች፣

‹‹ብዙም አታንቆለጳጵሰው…እያየነው አይደል እንዴ?›› አለች፡፡

ከዚያ ልትገዛው እንዳሰበች ሁሉ አገላብጣ እያየችው ቆየችና፣

‹‹ምነው እንዲህ ቀጠነ ጃል?! ለመሆኑ እውነተኛ ወርቅ ነው ወይስ አርቴ?…›› አለች በሽሙጥ፡፡


ሴቶቹ በመንጫጫት ደገፏት፡፡


‹‹እኮ…ነፋስ ቢነካው ሳይበጠስ ይቀራል?››
‹‹ይሄማ አርቴ ነው…ነገ ይለቃል…››
‹‹ደረሰኙ የታለ?›››
‹‹አርቴ ነው አርቴ ነው››
እያሉ ፈቃዱና ጓደኞቹን አጣደፏቸው፡፡


አምሳለ እንኳን እንደአቅሚቲ፣
‹‹ምንድነው ይሄ ከዶሮ አጥንት የቀጠነ ነገር›› አለች፡፡ አላልኳችኹም ….ምሳሌዋ ሁሉ ምግብ ነክ ነው፡፡




ቀጥሎ የጆሮ ጉትቻዎቹን ወጡ፡፡
አሁንም ነገረኛዋና ቅልብልቧ የይፍቱ አክስት ተቀብላ እያየቻቸውና-
‹‹ወይ ዘንድሮ…! ይህችን ለመሰለች ልጅ ይሄን…? ደግሞ ማነሳቸው…ለሙሽሪት ነው ለሚወልዷት ልጅ…? ›› አለች በሹፈት፡፡


እሷ ልክ ይሄንን ስትል በሙቀቱና በሴቶቹ ልግጫ እንደተማረረ የሚያስታውቀው ሁለተኛው ሚዜ ቀስ ብሎ እንዲህ አለ፤
‹‹ልጃቸው.. ልጃቸው እንኳን አንድ ስድስት ወር ይቀራታል ለመወለድ..››



እኔና መቅደስ በድንጋጤ ተያየን፡፡

‹‹ምናልክ…? ›› አለችው ሌላኛዋ አክስት፡፡


ጉድ ፈላ! ሌላም ሰው ሰምቶት ኖሯል፡፡


‹‹ምንም…ለዚያ ያድርሳቸው.. ለልጃቸው ደግሞ ሌላ ይገዛል ነው ያልኩት›› አለ ጮክ ብሎ፡፡
ያን ጊዜ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁሉም ፈገግ አሉ፡፡
(ከላይ የቀጠለ)

ወደ ሽቶው ተሸጋገሩ፡፡
አንደኛዋ ሚዜ ሽቶውን ተቀብላ ከፈት አደረገች፡፡

አሸተተችው፡፡

ሁላችንም የምትለውን ለመስማት በጉጉት ጠበቅን፡፡

መጀመሪያ በረጅሙ ተነፈሰች፡፡ ከዚያ የሚመር ነገር እንደቀመሰች ሁሉ ፊቷን አጨማደደችና፣

‹‹ጭራሽ የሱዳን ሽቶ ይዛችሁ መጣችሁ…? ለይፍቱዬ ይሄ ነው የሚገባት…? ›› ብላ ጮኸች፡፡


ቤቱ በብዙ አይነት ድምጾች ተሞላ፡፡

‹‹እንዴ አይናለም! የፈረንሳይ ሽቶ ነው፡፡ ሙሽራው ራሱ ነው ሄዱ ያመጣው›› አለ ፍቃዱ ቶሎ ብሎ፡፡
‹‹እንዴ እኛ ሳንሰማ ሱዳን ፈረንሳይ ተባለች እንዴ…?›› ብላ ስትመልስለት ሁሉም ሰው ባንድነት ሳቀ፡፡


‹‹በእውነት ደስ አይልም..ልጃችን አንበሳ አውቶቢስ አንበሳ አውቶቢስ እንድትሸትማ አንፈቅድም…ይሄን አንቀበልም›› አለች አይናለም የልብ ልብ ተሰምቷት፡፡


ያን ጊዜ ነው እስካሁን ዝም ብላ የቆየችው የይፍቱሥራ ታላቅ እህት እታፈራሁ ስትናገር የሰማነው፡፡

‹‹እንደው ለመሆኑ ደህና ጫማ እንኳን አመጣችሁላት ወይስ? …›› አለች ቅዝዝ ብላ፡፡

ፈቃዱ ትእግስቱ እንዳለቀ በሚያሳብቅ ሁኔታ ግንባሩ ላይ ያቸፈፈ ላቡን በመሃረቡ ጠረገና፣

‹‹ገና እኮ ሁለት ያልከፈትናቸው ሻንጣዎች አሉ…ፋታ ስጡና…! › አለ የውሸት ፈገግ እያለ፡፡

---
ብዙ ሳይቆይ ሁለተኛውን ሻንጣ ከፍቶ ባለታኮ ጫማዎች አወጣ፡፡


በእርግጥ ያኔ ብዙ አልኖርኩም፤ ቢሆንም ግን ነሕይወቴ እንደዚህ የሚያምር ጫማ አይቼ አላውቅም፡፡


እታፈራሁ ያሳየችው ፊት ግን እድሜ ልኳን በባለ አስር ብሩ ነጠላ ጫማ ስትኳትን የኖረች አትመስልም፡፡


‹‹ጥቁር ጫማ… ልጃችን ሙሽራ እንጂ ሃዘንተኛ ናት እንዴ…?!›› አለች ፈጠን ብላ፡፡

እኔ ፈቃዱን ብሆን በንዴት ጫማዎቹን የምወረውርባት ይመስለኛል፡፡


አላበዙትም እንዴ…?
እሱ ግን በረጅሙ ተንፍሶ ከቬሎ ጋር የምትለብሰው ነጭ ጫማ ሌላኛው ሻንጣ ውስጥ እንዳለ አስረዳ፡፡ በመልሱ ብዙ የተደሰቱ አልመሰሉም፡፡



ቀጥሎ በደንበኛው የተጣጠፉ መአት አይነት ልብሶች እየወጡ መታየት ጀመሩ፡፡
ዘመናዊ፣ የሐገር ባህል፡፡

ያቺው ነገረኛ አክስት ግን አንዱን ከሩቅ የሚያብለጨልጭና ብሉኝ ብሉኝ የሚል ነጭ ኮትና ጉርድ ቀሚስ አነሳችና-
‹‹እንደው ይሄም ርካሽ ጨርቅ ነው…ደግሞ መሳሳቱ…›› አለች
አምሳለ ተቀበለቻትና፣ ‹‹እትዬ ልክ ናት.. ምንድነው ይሄ…አጎበር ነው ልብስ…?.›› አለች፡፡


ወንዶቹ እርስ በእርስ ተያያዩ፡፡


‹‹ምንም ያመጣችሁት ነገር ልጃችንን አይመጥንም፡፡ ጋሼ እምቢ ማለት አለበት ዛሬ፡፡ በዚህ ጥሎሽማ ሲያምረው ይቀራል እንጂ ልጃችን አትሄድም›› አለች ነገረኛዋ አክስት ጮክ ብላ፡፡


ሲተያዩ የነበሩት ወንድ ሚዜዎች ሳቃቸውን እንደማፈን ሲያደርጋቸው አየሁ፡፡
ከዚያ አንደኛው ወደ ፍቃዱ ጆሮ ቀስ ብሎ ተጠግቶ፣ ‹‹ ልጃቸው ያለችበትን ሁኔታ ቢያውቁ…›› ሲል ሰማሁ፡፡


እኔና መቅደስ ድጋሚ ተያየን፡፡


ከዚህ በኋላ ፈቃዱ የቀሩትን ጌጣጌጦችና ልብሶች አውጥቶ ማሳየት ጀመረ፡፡
የጸጉር ሻጤ፣ የጆሮ ጉትቻ፣ የአንገት ሃብል፣ የእጅ አምባር፣ የእግር አልቦ፡፡


‹‹እንግዲህ ዛሬ አዲሳባ አለ የተባለ ቡቲክ እንኳን ብትሄዱ ለሙሽሪት የመጣላት ያህል እቃ የላቸውም›› አለ አሳይቶ ሲጨርስ፡፡


‹‹ልጃችን ሲያንሳት ነው›› አሉ ሴቶቹ በመጨረሻ የተሸነፉ መስለው፡፡

እትዬ አስናቀች ፈገግ ስትል አየሁ፡፡


ትእይንቱ ሲያልቅ ቡና እና እራት ቀረበ፡፡

እኔና መቅደስም እንዳገባባችን ሹልክ ብለን ወጥተን ወደፊት ስለምናስመጣው ጥሎሽ በጋለ ስሜት ተጨዋወትን፡፡
ግን ምን ዋጋ አለው? እኛ ስናገባ ጥሎሽ ቀረ፡፡
‹‹ያላለቀ››
-------
ጸጥ ባለው ካፌ ተቀምጣ በዝምታ ተቆራጭ ኬኳን እየበላች ሲያፈጥባት ተሰማት፡፡

በአዘቦት ቀን ባለ ጥለት የሀበሻ ልብስ ቲሸርት ለብሷል፡፡
አርቲስት ነኝ ብሎ ከሩቅ የሚጮህ ባለ ባንዲራ ነጠላ አንገቱ ላይ ጠምጥሟል፡፡

ገጣሚ ነው ሰዓሊ?

አስባ ሳትጨርስ አጠገቧ መጣና፣

‹‹አንቺንማ መሳል አለብኝ” አላት።

ሰዓሊ።

“ያገኛሃትን ሴት ሁሉ ነው አይደል ልሳልሽ የምትለው?” አለችው።
“አይደለም፡፡ ቆንጆ ቆንጆዎቹን ብቻ እየመረጥኩ ነው›› አላት፡፡

ተሸኮረመመች፡፡
ሳቀች፡፡
ተቀመጠ፡፡
አወሩ፡፡

ከሶስት ቀናት በኋላ ካዛንቺስ ወደምትገኘው ትንሽዬ ስቱዲዮው ሄደች።
የተፋፈገና የተጨናነቀ የታፈነ አንድ ክፍል ቤት፡፡
ብዙ እንዳየ በሚያሳብቅ ሁኔታ የሚያቃስት በሩን ከፍቶላት ከመግባቷ ከብዙ ስእሎች ጋር ተፋጠጠች፡፡


የሴት መአት፡፡
ሴት፡፡ ሴት፡፡ ሴት፡፡ ደግሞ ሌላ ሴት፡፡
በሸራ ላይ። ፍሬም ውስጥ ባሉ ወረቀቶች ላይ። በክፍት ማስታወሻ ደብተሮች ላይ።


ጡቶች- ትላልቅ፡፡ የተጋለጡ ጭኖች፡፡የምትስቅ ሴት፡፡ ምታለቅስ ሴት፡፡ ምታዛጋ ሴት፡፡ ማንጎ የያዘች ሴት፡፡ ቢላዋ ይዛ ያፈጠጠች ሴት፡፡ ከንፈሯን ፊት ለፊቷ ያለን ሰው እንደመሳም ያሞጠሞጠች ሴት፡፡ እርቃኗን የተጋደመች ሴት፡፡ መለመሏን የቆመች ሴት፡፡ ራቁቷን በባለጌ አኳሃን ያፈነደደች ሴት፡፡

“በእየሱስ ስም ! የምታገኛቸውን ሴቶች ሁሉ ነው እንዴ የምትስለው?” አለችው።
“ስንገናኝ ነግሬሽ ነበር እኮ… ቆንጆ ሴቶችን ብቻ ነው የምስለው…ለፉንጋ ሸራና ቀለም አላባክንም” አላት ፈገግ ብሎ፡፡

መልስ ሳትሰጠው፣
ጸጉሯ በእሳት ከተያያዘ ሴት ስእል ፊት ለፊት ቆመችና፣
‹‹ምን ሆና ነው አናቷ ላይ እሳት የነደደው?›› አለችው፡፡
"ተያት ባክሽ እሷም ሕይወቴን እንዲህ አንድዳው ነው የሄደችው…ትንደድ " ብሎ መለሰላት፡፡

ሳቀች። ግራ እንደተጋባች የሚያሳብቅ ሳቅ።
ከዚያ ነው ቁጭ በይና ልሳልሽ ያላት፡፡


“ልብሴን ግን አላወልቅም አይደል?” ብላ ጠየቀችው።
"ጥበብን መዋሸት ከፈለግሽ ካላወለቅሽ ብዬ አላስገድድሽም" ብሎ መለሰላት።


የጆሮ ጌጥዋን በዝግታ አወለቀች።


ከዚያ ሸሚዟን፣ ጂንስ ሱሪዋን፣ ጫማዋ እንኳን ሳይቀር ሳታወልቅ፣
‹‹በላ…ሳለኛ?›› አለችው፡፡


ለአራተኛ ጊዜ ስቱዲዮው ሄዳ ስእሏን ሲቀጥል፣ ፍቅር ያዘው እንዴ ብላ ጠረጠረችው፡፡
ከእሷ ጋር አይደለም፤ ከማለዳ ብርሃን ጋር ከተዋሰበ ለስእል ከሚመች መልኳ፡፡
ሁልጊዜም እጅግ ማልዳ እንድትመጣ ይጠይቃታል።


በሚቀጥለው ስትመጣ ተቀምጣ እየተሳለች ሶሎሜ መጣች። ሶሎሜ የቀድሞ ፍቅረኛው ናት፡፡
ጉንጬ ላይ ስም አደረገችውና-

“እንዴት ነህልኝ የኔው?” ካለችው በኋላ እሷን በርጩማ ላይ እንደተቀመጠች ገርመም አድርጋት ስታበቃ፤

"ደግሞ ሌላ አመጣህ?" አለችው፡፡
"እሷ እንደ ሌሎቹ አይደለችም." ቶሎ መለሰ፡፡
"አንተ ሁሌ እንደዛ እንዳልክ ነው…ያቺ እንደ ውሻ የነከሰችህን ሳይቀር እንደሌሎቹ አይደለችም ብለኸኝ አልነበር?…"
"ምን ታድርግ…? ፍቅር እኮ ነው..ስማ አልወጣ ሲላት ነከሰችኝ …በቃ"

ሶሎሜ ከት ብላ ሳቀች፡፡

እሷ በተቀመጠችበት በሚያወሩት ነገር ግራ ተጋብታ አፈራርቃ አየቻቸው፡፡


ያን ምሽት እራት ልጋብዝሽ ብሏት አብረው አመሹ።
በጨዋታ መሃል ነከሰችው ስለተባለችው ሴት ጠየቀችው፡፡
‹‹ተይው የድሮ ታሪክ ነው…የእኔ ሃሳብ ሁሌም ወደፊት በምትነክሰኝ ሴት ላይ ነው…›› ብሎ አሳቃትና ነገሩን አድበሰበሰው፡፡


ያንን ምሽት ሊለያዩ ሲሉ፣


"አሁን ጨርሰናል አይደል? ያ በርጩማህ ቂጤን አደነዘዘው እኮ " አለችው፡፡
“እንዴ ገና ምኑ ተነካና… አሁንም እፈልግሻለሁ፣ ገና ያልሳልኩት ብዙ ነገር አለሽ” አላት።
"እንዴ…? ይሄን ሁሉ ቀን ምኔን ስትስል ከረምክና?…ልየው ብል አታሳይ ደግሞ "
"አንቺ ከስእል በላይ ነሽ… አደገኛ ሚውዜ ነሽ…ሚውዝ ታውቂያለሽ? …››
‹‹አላውቅም››
‹‹ሚውዝ ማለት ንሸጣ ማለት ነው…ባንቺ ሰበብ አንቺን ብቻ ሳይሆን ሌላም እንዳስብ፣ እንድስል ታነሳሺኛሽ ማለቴ ነው…ደግሞ ያንቺ ንሸጣ ከባድ ነው…››
‹‹ምንድነው ነው ክብደቱ…? ››
‹‹ ሐቀኛ እንድሆን ያስገድደኛል…እውነቱን …እቅጩን እቅጩን ብቻ እንድስል…ያስፈራኛል››
"ሐቀኛ መሆን ለምን ትፈራለህ?"

መልስ ለመስጠት የፈራ መሰለ፡፡


--
ከዚያ ቀን በኋላ እልም ብላ ጠፋችበት፡፡
ይደውላል፤ ትዘጋዋለች፡፡
ቴክስት ይልካል፡፡ ሳትመልስ ትተዋለች፡፡
ስለዚህ ከትዝታው እየቀዳ፣ በትውስታው እየታገዘ ስሎ ጨረሳት።

ስእሏን ‹‹ያላለቀ›› ብሎ ሰየመውና ስቱዲዮው ውስጥ ሰቀለው።
እሷን ደግሞ ከናካቴው ረሳት፡፡

-----

ከወራት በኋላ ወደ ስቱዲዮው ተመለሰች።
በሕይወት መሰላቸቷን ለመበረዝ ይሆን የስእሏን መጨረሻ ለማወቅ ጓጉታ…?
ማን ያውቃል?
ብቻ ተመለሰች፡፡


ወደ ስቱዲዮ ገባች።
በስነስርአት እንኳን ሰላም ሳትለው በሩ ፊት ለፊት የሰቀለውን ስእል አየች፡፡
የእሷ ነው፡፡
ጠባብ ዳሌ፡፡ብይ የሚያክሉ ጡቶች፡፡ ሰላላ እግሮች፡፡
ፊቷ ብቻ የእሷን ይመስላል።


መጀመሪያ ስእሏ ላይ ከእዚያ ደግሞ እሱ ላይ አይኗ እስኪጎለጎል አፈጠጠች፡፡


"አንተ አይንህ አያይም እንዴ? አሁን ይቺ እኔ ናት ልትል ነው? …እይ እስቲ…እኔ እኮ ስለምሸፋፈን ነው እንጂ ምን የመሰለ የኮራ የደራ ዳሌ አለኝ…ሰፊ ሱሪ እንኳን የሚያስጨንቁ ጭኖች አሉኝ:: ጡቶቼን እንዲህ ያሳነስካቸው ለምንድነው…? እዚህ ከተማ የሚሆነኝ ጡት መያዣ እንደማላገኝ ታውቃለህ…? ታሾፋለህ እንዴ…ይህችማ ከፊቴ በስተቀር እኔ አይደለሁም…እንዴ! "

በንዴት ተንገበገበች፡፡ ጨሰች፡፡

"እንግዲህ ትውስታዬ ደካማ ነው ማለት ነው" አላት ረጋ ብሎ፡፡
"ስትጠፊብኝ አማራጭ አጣሁ፡፡ ከማስታውስሽ መሳል ነበረብኝ።"


መልስ አልሰጠችውም፡፡

ልብሶቿን ማወላለቅ ጀመረች፡፡

በዝግታ አይደለም፡፡ በጥድፊያ፡፡ በብስጭት፡፡ በእልህ፡፡ በተቃውሞ፡፡

እርቃኗን እስኪያያት ድረስ አላስችል እንዳላት ሁሉ ተዋክባ አወላልቃ ያለ ምንም ሃፍረት ፊት ለፊቱ ቆመችና አሁንም ንዴት ባሸነፈው ድምጽዋ፣

‹‹በል…ሳለኝ…አሁን እውነቱን እያየህ ሳለኝ…በደንብ..እያየህ….በደንብ…›› አለችው፡፡

አዲስ ሸራ አዘጋጀ፡፡
አዲስ ብሩሽ አነሳ፡፡
ቀለም አጠቀሰ፡፡
ፈገግ አለ፡፡
መሳል ጀመረ፡፡


ከሳላቸው ሴቶች ውስጥ አንዷንም ለምኖ እርቃኗን አልሳላትም፡፡
ሁልጊዜ የሚለምኑት እነሱው ናቸው፡፡
እንደዚህ አይነት መላ ዘይዶ ስለ ራሳቸው ያላቸውን አመለካከት ቆንጠጥ ሲያደርገው፣

‹‹ማን መሰልኩህ አንተ… ? እኔ እኮ ሙሉ ሴት…ውብ እንስት ነኝ…ካላመንክ እይማ›› ብለው ፊት ለፊቱ ራቁታቸውን ይቆማሉ፡፡
‹‹ያላለቀ ›› መባልን ስለሚፈሩ በፈለገው መንገድ እንዲጨርሳቸው፣ በገላቸው እንዲያዝ ተማፅነው ሙሉ ፈቃዳቸውን ይሰጣሉ፡፡
ደህና ናችሁ?

እንግዲህ ፣ "ምነው ቀድመሽ ብትነግሪን ኖሮ" እንዳትሉ ቀድሜ ልንገራችሁ ።


የዛሬ ሳምንት ዓርብ ( ሰኔ 13) ካመቻችሁ ኑ እና ቡና ጠጡ፤ ፓስቲ ብሉ፤ ወግ ጠርቁ፤ (ከፈለጋችሁ)በአስር ዓመት የፃፍኩና ያሳተምኳቸውን አምስቱንም መጽሐፎቼን ግዙ።



ግብዣው ለሁሉም ሰው፣መግቢያው በነፃ ነው።


ዝርዝሩን ፓስተሩ ላይ ታገኙታላችሁ።

የእዚያ ሰው ይበለን።
2025/06/13 18:53:22
Back to Top
HTML Embed Code: