Telegram Web
ንጹሕ ሆነን የረከሰ ምራቅን አለመጠየፍ እንዴት ይቻለናል? ያለ በደል የሚደረግ ውንጀላ እና ግፍንስ "በቃ" አለማለት እንዴት ይሆናልናል?

ያለ ጥፋት የሚመጣብንን ምን ያህል ጥፊዎች እንታገሳለን? ስንት ጅራፎችንስ እንቀበላለን? ስንት ውርደቶችንስ እንሸከማለን? መድኃኔዓለም ይህን ሁሉ ነገር የተቀበለው ስለ እኛ መዳን ነው።

እኔ ግን ስለ ራሴ መዳን በጀርባህ ላይ ካረፉት ጅራፎች የአንዲቱን ሰንበር ያህል እንኳን መከራ ለመቀበል ትዕግስቱ የለኝም።

"ተሰሃለኒ እግዚኦ በከመ ዕበየ ሳህልከ" - "አቤቱ እንደ ቸርነትህ መጠን ማረኝ" መዝ 50፥1

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
https://www.tgoop.com/Dnabel
ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ እና ዮሐንስ ዘደማስቆ ሐዋርያው ጴጥሮስ ጌታ በዐረገ በዓመቱ (34 ዓ.ም.) ቅዱሱን እሳት በመቃብሩ ስፍራ ማየቱን ጽፈዋል። ይህ ተአምር አሁን እስካለንበት ዘመን የቀጠለ ሲሆን፣ ሁል ጊዜም በትንሣኤ በዓል ዋዜማ ቅዳሜ ቀን ይታያል። ስለዚህ የሚያስደንቅ ተአምር ብዙ የማያምኑ ሰዎች በራሳቸው መንገድ ለማጣራት ሞክረዋል። እስኪ ከእነዚህ ውስጥ አንዱን ታሪክ ላጫውታችሁ።

በአንድ ወቅት እንዲህ ሆነ…

ዕለቱ ቅዳሜ ጠዋት 4 ሰዓት የትንሣኤ ዋዜማ ነው። የእስራኤል አይሁድ ፖሊሶች እና የከተማዋ ከንቲባ ይህ እሳት ይፈልቅበታል የተባለውን የጌታን መቃብር እውነትነት ማረጋገጥ ስለ ፈለጉ በውስጡ ለእሳቱ መነሣት ምክንያት የሚሆኑ ተቀጣጣይ ነገሮች ካሉ በሚል ለሁለት ሰዓታት ያህል ሦስት ጊዜ ጥብቅ ፍተሻ አደረጉ። ግን ምንም ሊያገኙ አልቻሉም። ቀጥሎም ሁለት መቃብሩን የሚጠብቁ ሙስሊሞችን በማምጣት ልክ የቀድሞዎቹ አይሁድ የጌታን መቃብር እንዳተሙ እነርሱም መቃብሩን ዘግተው በሰም እንዲያትሙት አደረጉ።

ይህንም ተከትሎ በቦታው የነበሩ አረብ ክርስቲያኖች ቱርክ እስራኤልን በተቆጣጠረችበት በ13ኛው ክፍለ ዘመን ከቤተ ክርስቲያን ውጭ በየትኛውም ቦታ ቢሆን እንዳይዘምሩ የተከለከሉትን ቆየት ያለ ዝማሬ በኅብረት ከፍ ባለ ድምፅ መዘመር ጀመሩ። መዝሙሩም:-

“እኛ ክርስቲያኖች ነን። ለብዙ መቶ ክፍለ ዘመናትም ክርስቲያኖች ነበርን። እስከ ዘላለምም እንዲሁ እንሆናለን፣ አሜን!” የሚል ነበር።

እኩለ ቀንም ሲሆን የግሪኩና የአርሜንያው ፓትርያርክ፣ የግብፁ ሜትሮፖሊታንት እንዲሁም ቀሳውስት እና ዲያቆናት ወደ ታተመው የክርስቶስ መቃብር መጡ። ከብዙ ጸሎት እና ምስጋናም በኋላ የታተመው የክርስቶስ መቃብር እንዲከፈት አደረጉ። ፓትርያርኩም ሞጣህቱን ብቻ አስቀርተው ከላይ የለበሱትን ልብሰ ተክህኖ በማውለቅ በክርስቶስ የዕድሜ ቁጥር ልክ ሦስት 33 ያልበሩ ሻማዎችን ይዘው ጨለማ ወደ ነበረው መቃብር ገቡ። ምእመናኑም ከውጭ ሆነው በአንድ ድምፅ ኪርዬሌይሶን (አቤቱ ይቅር በለን) እያሉ በመዘመር ይጠባበቁ ጀመር። ወደ ቅዱሱ መቃብር ገብተው የነበሩትም የግሪኩ ፓትርያርክ ያን በሰው ያልተቀጣጠለ እና የክርሰ‍ቶስን የትንሣኤ ብርሃን የሚያበሥረውን አምላካዊ እሳት ይዘው ብቅ አሉ። ይህን ጊዜ ጎልጎታ በእልልታ ተሞላች የቤተ ክርስቲያኑም ደወል በሐሴት ይደወል ጀመር።

ትንሣኤከ ለእለ አመነ
ብርሃነከ ፈኑ ዲቤነ

እንኳን አደረሰን!!!

https://youtu.be/OGyzCFZO0VY?si=2ptLkHV_WD5rYRvY

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
የእግዚአብሔር ሰው ሰሎሞን ለአምላኩ ሕንፃ መቅደስን ሊያንጽ በተነሣ ጊዜ ፤ "በጥበብና በማስተዋል በብልሃትም የተሞላ" የናሱን ሠራተኛ ኪራምን ከጢሮስ አስመጥቶ ነበር። ከዚህም ጥበበኛ ጋር ሆኖ እጅግ አስደናቂ የሆነውን መቅደስ በታላቅ ጥንቃቄ አንጿል። በእውነት ይህን ሰሎሞን ያሳነጸውን ውብ መቅደስ ማየት ምንኛ ያጓጓ ይሆን? በእርግጥም መቅደሱንና የመሥዋዕቱን ሥርዓት የተመለከተች ንግሥተ አዜብ ማክዳ "ነፍስ አልቀረላትም" ነበር (1ኛ ነገ 10:5)።

ሆኖም ግን እግዚአብሔር በነቢዩ ኢሳይያስ አድሮ "ሰማይ ዙፋኔ ነው ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት፤ ለእኔ ምን ዓይነት ቤት ትሠራላችሁ?" ብሎ መጠየቁ አልቀረም (ኢሳ 66:48)። ለጊዜው በረድኤት የሚያድርበትን መቅደስ ንጉሥ ሰሎሞን ውብ አድርጎ ቢያንጽለትም ፤ በኋላ ግን የሰውን ልጆች ለመቤዠት በአካል የሚያድርበትን ሕያው መቅደስ ማንም ማዘጋጀት አልቻለም ነበር። ስለዚህም "ልዑል የሰው እጅ በሠራችው አይኖርም" ተብሎ ተጻፈ (ሐዋ 7:50)። በመሆኑም መቅደሱን ላነጹ ለሰሎሞን እና ለኪራም ጥበብን የሰጠው ጥበበኛ "ለራሱን ቤት ሊሠራ ፣ሰባት ምሰሶዎችንም ሊያቆም" ፈቃዱ ሆነ። የመቅደሱንም መሠረት እንቁ አደረገ። ቤቱንም እጅግ በከበሩ ድንጊያዎች አነጸ።

ይህች በአምላክ እጅ የታነጸች ፣እግዚአብሔር በረድኤት ሳይሆን በአካል የሚያድርባት ሕያው መቅደሱ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት። የተመሠረተችባቸውም አዕናቁ (እንቁዎች) ቅዱሳን ቤተሰቦቿ ናቸው። የታነጸችበትም የከበሩ ድንጊያዎች ንጽሕና ፣ቅድስና ናቸው።

"ይህች ዓለም አይቶ የማያውቃት በተስፋ ትጠበቅ የነበረችው ድንቅ አማናዊት መቅደስ ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህች ምድር ላይ የታየችው በዛሬው ቀን ነበር"

ኪራም ያነጸው የሰሎሞንን መቅደስ መጎብኘት "ነፍስ የማያስቀር" ፣ልብን በሐሴት የሚሞላ ከሆነ ፤ በእግዚአብሔር እጅ የታነጸች ፣የአምላክ ጥበብ የፈሰሰባት እውነተኛ መቅደሱን የእመቤታችንን መወለድ የማየትና የመስማት የደስታ ጥጉ ምን ያህል ይሆን?

እንኳን ደስታን ወደ ዓለም ይዞ ለመጣ ተናፋቂው ለድንግል ማርያም ልደት አደረሳችሁ!!!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
https://www.tgoop.com/Dnabel
ጫካው ቢመነምንም፣
ዛፎች መጥረቢያውን መምረጥ አላቆሙም፤
ራሴን ተውና እየው እጀታዬን፣
በምን እለያለሁ አሁን ከአንተ ወገን፤
እያለ በመስበክ ሲያውቅ የኋላውን፣
ምሳሩም ጎበዝ ነው እጹን በማሳመን፤

ዲያቆን አቤል ካሳሁን

(መነሻ Paulo coelho)
ቅዱስ ጴጥሮስ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” የሚለውን የትንሣኤውን ጌታ ድምጽ ከሰማ ፣ የተጠራጠረው ቶማስ እጁን በጎኖቹ አግብቶ “ጌታዬ አምላኬ” ብሎ ሲያምን ከተመለከተ በኋላ “ዓሣ ላጠምድ እሄዳለሁ” ብሎ ሲናገር እናገኘዋለን።(ዮሐ 21፥3) ክርስቶስ ተላልፎ በተሰጠበት በሐሙስ ምሽት ከእሳት ዳር ተቀምጦ ያደረገውን ሊረሳውና ራሱን ይቅር ሊል ስላልቻለ፣ ጌታው ቀድሞ የሰጠውን የወንጌል መረብ ተወና የዓሣውን መረብ ጨብጦ ወደ ገሊላ ባሕር ሮጠ።(ማቴ 4፥19) በኃጢአት ምክንያት የተሰማው ኃፍረትና መሸማቀቅ ሐዋርያነቱን ትቶ በድሮ ማንነቱ ውስጥ ራሱን እንዲደብቅ አደረገው። የካደን ማን ለምስክርነት ይፈልገዋል በሚል ዓይነት ስሜት ለወንድሞቹ “ዓሣ ላጠምድ እሄዳለሁ” አላቸው።

ደስ የሚለው ነገር ግን ይህን አስቀድሞ የሚያውቅ ይቅር ባይ አምላኩ ጴጥሮስን “በገሊላ ቀድሞት ነበር”። በበደሉ ተሸማቆ የተወውን ሐዋርያነት ሥልጣን በፍቅሩ መማለጃነት መልሶ ሊሰጠው፣ አይገባኝም ብሎ ያስቀመጠውን የወንጌል መረብ ዳግመኛ ሊያሲዘው በገሊላ ባሕር ዳር ቀደመው። እኛም አንድ ኃጢአት ይኖረናል። መርሳት ያልቻልነው፣ ንስሐ እንኳን ብንገባበት ራሳችንን ይቅር ለማለት የተቸገርንበት፣ “ከዚህ በኋላማ...” እያሰኘ የድሮ መረብ አስይዞ ወደ ገሊላ የሚመልስ አንድ በደል ይኖረናል። ነገር ግን ጌታ ለቅዱስ ጴጥሮስ እንዳደረገው ለእኛም እንዲሁ ያደርጋል። ከባሕሩ ዳር ይጠብቀናል፣ “ትወደኛለህ” ብሎ ይጠይቀናል፣ ከዚያ በማይለወጥ ፍቅሩ ወልውሎ ሰንግሎ አፍረን ወደ ሸሸነው መንፈሳዊነት ይመልሰናል።

+++ ጌታችን በገሊላ ይቀድመናል! +++

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
አዲስ አበባ
ከመላእክት ጋር አብረን የምንዘምርበትን የዜማ ሥርዓት ለሠራልን፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ የወረደውን የምስጋና ማዕድ ለእኛ እንደሚገባ አድርጎ ላደረሰ ታማኝ መጋቢ፣ ለዘማሪው፣ ለተርጓሚው፣ ለባለ ቅኔው ለቅዱስ ያሬድ ማኅሌታይ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሰን።

-የአንደበት አመጽ ጸጋን አስገፍፎ እንዴት የመልአክነትን ክብር እንደሚያሳጣ በሳጥናኤል አየን!

-የአንደበት ፍሬ እንዴት እንደሚያከብር እና ምድራዊ መልአክ እንደሚያደርግ ደግሞ በቅዱስ ያሬድ ማኅሌታይ ተመለከትን!

አቤቱ የያሬድን ልሳን ስጠኝ!

ዲያቆን አቤል ካሣሁን
[email protected]
https://www.tgoop.com/Dnabel
የፊታችን ረቡዕ ሌሊት 11፡00 ሰዓት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ትምህርት ስለምንጀምር በየትኛውም ዓለም የምትኖሩ እና መማር ፈቃዳችሁ የሆነ ሁሉ ከታች የተቀመጠውን የZoom link በመጠቀም ልትቀላቀሉን ትችላላችሁ::

“ብዙ ምርኮ እንዳገኘ በቃልህ ደስ አለኝ” መዝ 119:162

https://us02web.zoom.us/j/81873667259?pwd=R2ZGVWVEamhLZU5aVk1PeXhxcGFrdz09
አጭር ግን ቶሎ እጅ የሚያሰበስብ ቃል ነው። ቅዳሴ ላይ በሰማሁት ቁጥር ሁሌ “እንዴት ሆኜ አይቶኝ ይሆን?” እንድል የሚያደርገኝ ጉልበታም ንግግር ነው።

“እግዚአብሔር ያያል!”
ረቡዕ ግንቦት 21 ሌሊት 11 ሰዓት (በኢ/ያ አቆጣጠር) ሁለተኛ ክፍል ትምህርታችንን እንቀጥላለን። ትምህርቱ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ላላችሁ ሁሉ ክፍት ነው። ባለፈው ሳምንት ያሳያችሁን ሰዓት አጠባበቅ እና ትጋት በዚህም ሳምንት አይለይዎ!

“እንዲህም የተወደደው ወንድማችን ጳውሎስ ደግሞ እንደ ተሰጠው ጥበብ መጠን ጻፈላችሁ” 2ኛ ጴጥ3:15

https://us02web.zoom.us/j/81873667259?pwd=R2ZGVWVEamhLZU5aVk1PeXhxcGFrdz09
የቅዱስ ኤፍሬም ድርሳናት ፍሬ

በትውልድ እንግሊዛዊው እና ለብዙ ዘመናት የፕሮቴስታንቲዝም አንዱ ቅርንጫፍ በሆነው የአንግሊካን እምነት ውስጥ የቆየው ዕውቁ ሊቅ ሰባስትያን ብሮክ ቅዳሜ ግንቦት 18 (May 25) በሶርያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥምቀተ ክርስትና ተፈጽሞለት በቅብዓ ሜሮን ከብሮ ዋለ።

ሰባስትያን በኦርቶዶክሱ ዓለም በሶርያ የሚገኙ ጥንታዊ የሆኑ የነ ቅዱስ ኤፍሬም ድርሳናትን ከጥልቅ ሐተታዎች ጋር በመተርጎም እና የሶርያን ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ሕይወት በማጥናት በሰፊው ይታወቃል። በዚህ ዙሪያ የሠራቸው እና ያሳተማቸው የጥናት እንዲሁም ትርጉም መጻሕፍት ዝርዝር ብቻ ወደ ሠላሳ ገጽ ይሆናሉ። የሶርያም ቤተ ክርስቲያንም ለዚህ ድካሙ የቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ሜዳልያ (Medal of St. Ephrem the Syrian) የተባለውን በክብር አበርክታለታለች።

እነዚያን ወርቅ የሆኑ አጥንት ድረስ ዘልቀው የሚወጉ የማር ኤፍሬምን ድርሳናት ከውጭ (በሃይማኖት) ሆኖ መተርጎሙ ሁሌ ያሳዝነኝ ነበር። ታምሞ ግን የሚድንበትን መድኃኒት ተሸክሞ እንደሚቸገር ምስኪን ሰው አድርጌም አስበው ነበር። ድርሳናቱ መቼ ነው ወደሚድንበት መርከብ እየመሩ የሚያስገቡት ብዬ ብዙ ጊዜ እጠይቅ ነበር።

ያለፈው ቅዳሜ ግን ይህን ኀዘን የሚሽር የምሥራች ሰማሁ። ለካስ ቅዱሱ የቀጠረለት ቀን ነበር?! ይኸው የኤፍሬም ቀለም የበላውን (ያቃጠለውን) ምሁር ከኦርቶዶክሳዊው ካህን ስር በትሕትና በርከክ ብሎ አየሁት።

ይህ መመለስ የቅዱሱ ምልጃ እና በቅዱስ ኤፍሬም ድርሳን ያለቀሱ የብዙ የዋሃን ምእመናን እንባ ውጤት ነው።

የአበው ድርሳን አሁንም በሥራ ላይ ነው!!!

ዲያቆን አቤል ካሣሁን
[email protected]
"አርእይኒ ገጸ ዚአኪ ማርያም ምእረ፤ ዘኢይሰምዖ ካልዕ እንግርኪ ነገረ"
"ማርያም ሆይ፣ ለሌላው የማልነግረውን ነገር እነግርሽ ዘንድ አንድ ጊዜ ፊትሽን አሳይኝ"

መልክአ ማርያም

እንኳን ለበዓለ ደብረ ምጥማቅ በሰላም አደረሳችሁ!
2024/06/01 20:01:18
Back to Top
HTML Embed Code:


Fatal error: Uncaught Error: Call to undefined function pop() in /var/www/tgoop/chat.php:243 Stack trace: #0 /var/www/tgoop/route.php(43): include_once() #1 {main} thrown in /var/www/tgoop/chat.php on line 243